ፈልግ

2018.10.25 Briefing Sinodo Giovani 2018 2018.10.25 Briefing Sinodo Giovani 2018 

ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ወጣቶች የመንፈስ ቅዱስ ሃይል መሆናቸውን ገለጹ።

ከወጣቶች ጋር በሕብረት መጓዝ፣ በሕብረት መሥራት ምን ያህል አስደሳችና ውበት ያለው መሆኑን በጳጳሳቱ ጉባኤ ወቅት ተገንዝበናል ብለዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ እንዲያውቁት ወይም እንዲገነዘቡት ለማድረግ በሚል ርዕስ፣ በቫቲካን ከተማ እየተካሄደ ያለው 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ የአንድነት መንፈስ የታየበት፣ ከተለያዩ ባሕሎችና የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር ተገናኝተው የተወያዩበት አጋጣሚ እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲየሮ ባሴቲ ገልጸዋል። በዚህ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ ወጣቶች በመገኘታቸው የመንፈስ ቅዱስን ደራሽነት እንድናይ አድርጎናል ብለዋል። በኢጣሊያ የፔሩጃ ሊቀ ጳጳስና የኢጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲየሮ ባሴቲ ትናንት ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስገነዘቡት፣ በጳጳሳቱ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ወጣቶች በርካታ ተጨባጭነት ያላቸውን ሃሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በማቅረባቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ወጣቶች ልባቸውን የሚያነቃቃና አብሮአቸው የሚሆን ደጋፊ ሃይል ይፈልጋሉ ብለው ከወጣቶች ጋር በሕብረት መጓዝ፣ በሕብረት መሥራት ምን ያህል አስደሳችና ውበት ያለው መሆኑን በጳጳሳቱ ጉባኤ ወቅት ተገንዝበናል ብለዋል።

እጆችዋን ዘርግታ የምትጠብቅ ቤተክርስቲያን፣

15ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በመከታተል ላይ ካሉት ብጹዓን ጳጳሳት መካከል በካፖ ቨርዴ የሳንቲያጎ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አርሊንዶ ጎመዝ ፉርታዶ፣ በቫቲካን የሕትመት ክፍል ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳስገነዘቡት ክርስቲያኖች አንድነትንና ሕብረትን ለማጠናከር ተጠርተዋል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ጎመዝ በማከልም በ15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ወቅት የቀሰሙት ልምድ፣ ከሌሎች በርካታ አገሮች ከመጡት ብጹዓን ጳጳሳትና ወጣቶች ጋር ሆነው በሕብረት ያደረጓቸው ውይይቶች ለወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎትና ለቤተክርስቲያን እድገት እጅግ ጠቃሚ ሆነው ማግኘታቸውን ገልጸዋል። አቡነ ጎመዝ በማከልም እያንዳንዱ ምዕመን ወይም የቁምስና ማሕበራት የአንድ ቤተሰብ አባል በመሆን በሕብረት ሆነው የመሥራትንና የመተጋገዝን ባሕል ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የቤተክርስቲያንን አንድነት ያመላክታል ያሉት የፔሩ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንትና የትሪዩሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሄክቶር ሚጉዌል በበኩላቸው ቤተክርስቲያን በሰዎች መካከል ልዩነት ሳታደርግ ሁሉንም ለመቀበ እጆቿን ዘርግታ የምትጠብቅ ናት ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ሚጉዌል የ15ኛው ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ፣ የሃሳብና የባሕል ልውውጥ የታየበት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ መሆኑን አስረድተዋል።

26 October 2018, 15:22