ፈልግ

2018.10.08 Briefing Sinodo 2018.10.08 Briefing Sinodo 

ቤተክርስቲያን ለፈጸመቻቸው በደሎች ፍትሃዊ ፍርድን ለመስጠት እውነትን መፈለግ ያስፈልጋል።

ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ ቤተክርስቲያን ለፈጸመቻቸው በደሎች ፍትሃዊ ፍርድን ለመስጠት እውነትን መፈለግ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ትናንት  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ ቤተክርስቲያን ለፈጸመቻቸው በደሎች ፍትሃዊ ፍርድን ለመስጠት እውነትን መፈለግ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ። አሁን በመካሄድ ላይ ያለውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስንና ሌሎችንም ርዕሠ ጉዳዮች በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያን የሰጡት የማልታ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ሺኩሉና እንዳስረዱት የቤተክርስቲያንን ደካማ ጎን ብቻ መመልከት ሳይሆን የሐዋርያዊ አገልግሎቷ መልካም ፍሬዎችንም መመልከት ያስፈልጋል ብለው፣ በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው መካከል የወጣቶችን ሕይወት በመከታተል ድጋፍን የሚሰጡ ምስጉን ካሕናት መኖራቸውን አስታውሰዋል።

የማልታ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በመወከል በቫቲካን በመካሄድ ላይ ያለውን 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሚካፈሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቻርልስ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መወያያ ርዕስ በሆነው ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን እንዲገነዘቡ በሚለው ርዕሥ ዙሪያ ሰፋ ያለ መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳሱ በዚህ የመወያያ ርዕስ ስር በቁጥር 66 ላይ የተጠቀሰውና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ በወጣቶች ላይ የተፈጸሙ ስሕተቶችና በደሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ በማከልም ለተፈጸሙት በደሎች ፍትሃዊ ፍርድን ለመስጠት ረጅም ጊዜን መውሰድ አስፈላጊ አይደለም ብለዋል። በፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ በራዘም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንዳልተደሰቱ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ቻርልስ ሁላችንም ምሕረት ያስፈልገናል ብለው ምሕረትም እውነትንና ፍትህን ያልተከተለ እንደሆነ ዋጋ አይኖረውም ብለዋል። ከየካቲት 14 – 17 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ሊካሄድ የታቀደ ስብሰባ እንዳለይ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ፣ የስብሰባው ዓላማ በሕጻናት ላይ ስለሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ዋና ምክንያቶችንና መከላከያ መንገዶችን የሚፈልግ እንደሚሆን ገልጸው ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቶችን መስጠት እንጂ ስልጣንን ለሌላ ሕገ ወጥ ተግባር መጠቀሚያ ማድረግ ተገቢ አይደለም ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ቻርልስ በመግለጫቸው ማጠቃለያ እንደገለጹት በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሚያገለግሏቸው ምእመናን ታማኝና የተቀደሱ ካህናት ወይም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መኖራቸውን አስታውሰው ቅድስናም የሰው ልጅ ደካማነትና የእግዚአብሔር ምሕረት የሚገናኝበት ነው ብለዋል።

የወጣቶች ደስታን መሻት፣

በቫቲካን በመካሄድ ላይ ስላለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ማብራሪያን የሰጡት ሌላው የጉባኤው ተካፋይ የሆኑት፣ የፈረንሳይ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን የወከሉት የሊዮን ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አማኑኤል ጎቢሊያርድ፣ ጉባኤው ከተወያየባቸው ርዕሶች መካከል በትውልዶች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ውስጥ ሴቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ፣ ስደት፣ ወጣቶች ሊኖራቸ የሚገባ የስነ ጾታ እውቀትና የወጣቶች ቅድስና የሚሉ እንደሚገኙበት ተናግረዋል። ብጹዕ አቡነ አማኑኤል በበኩላቸው  በበኩላቸው እንዳብራሩት እያንዳንዱ ወጣት ለእውነተኛ ደስታ፣ ለቅድስናና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኝ ተጠርቷል ብለው በማከልም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ማሳሰቢያ በማስታወስ የሰው ልጅ ምንም ዓይነት መገለል ሳይደርስበት በማንነቱ ከነሙሉ ድክመቱ መወሰድ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ለወጣቶች የቀረበ ተገቢ ምላሽ፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤን በመካፈል ላይ የሚገኝ ሌላው ተሳታፊ አቶ ቶማስ ሌዎንቺኒ፣ ብጹዓን ጳጳሳት በሚወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የተሰማውን እርካታ ገልጾ፣ ቤተክርስቲያን በወጣቶች ጉዳይ ላይ ትኩረትን በመስጠት ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እጅግ እንዳስደሰተው ገልጿል። አቶ ቶማስ በማከልም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ትኩረቱ ያደረገው በካቶሊክ ወጣቶች ሕይወት ብቻ ሳይሆን እምነት በሌላችውና በጥርጣሬ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ሕይወት የወደ ፊት ተስፋ በዚህ ባልተረጋጋ ማሕበረሰብ መካከል ምን ሊሆን ይችላል በማለት እንደሚወያይ አብራርቶአል።

09 October 2018, 17:53