ፈልግ

2018.10.04 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 2018.10.04 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 

የጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ማሕበራዊ ሚዲያ ለወንጌል ስርጭት አገልግሎት መጠቀም እንደሚቻል አሳሰቡ።

በሦስት ሺህኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ መንገድን የተከተለ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴን ለመጠቀም ተጠርተናል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲኖዶሱ አባቶች እንደገለጹት ዘመኑ ባፈራቸው አዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በኩል የወንጌል ስርጭት አገልግሎትን ማበርከት የሚቻል መሆኑን ገልጸው፣ አጠቃቀማቸውም በነጻነትና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

በሦስት ሺህኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ መንገድን የተከተለ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴን ለመጠቀም ተጠርተናል ብለው፣ የዲጂታል አገልግሎትን የሚከታተል ልዩ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም ጠይቀዋል።  ከዚህም ጋር በማያያዝ ወንጌልንና ቤተክርስቲያንን በሚገባ ለማወቅ የሚረዱ ዲጂታል የኮምፒዩተር ፕሮግራሞችንም ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በሌላ ወገን፣ የሲኖዶሱ አባቶች፣ ወጣቶች ስማርት ፎን የሚባሉ ዘመናዊ ስልኮችንና ታብለቶችን እንደ ማሕበራዊ ሚዲያ በሚጠቀሙበት ወቅት፣ ለረጅም ሰዓታት በተከታታይ በመጠቀም ብዙ ጊዜን ስለሚያባክኑ ወደ ብቸኝነት ስሜት ውስጥ እንዳይገቡ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ቤተክርስቲያን፣ ወጣቶች የተለያዩ በዓላትን በማዘጋጀት እርስ በርስ ተገናኝተው የሚዝናኑበትንና የሚወያዩበትን አጋጣሚዎች ማሳደግ እንዳለባቸው ታስገነዝባለች ብለዋል።

የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም፣ ቤተክርስቲያንም ሆነ ሕብረተሰብ ወጣቶችን እንደሚፈልጓቸው ገልጸው የግለኝነት ስሜትን ለማስወገድ በሁሉም ዘንድ የመቀራረብ፣ የአንድነትና የመተጋገዝ መንፈስ እንዲያድግ አዲሱን ትውልድ ማስተማርና ግንዛቤን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን እቅድ ወይም ምኞት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ዘዴዎችን፣ ከእነዚህም መካከል የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮን ትምህርቶችን ወደ ወጣቱ ዘንድ ማዳረስ፣ ስለ ሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማስተማር፣ ሙስናን ስለ መዋጋት፣ ስለ መልካም አስተዳደርና በሕዝቦችና በሐይማኖቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባው መተጋገዝ ወጣቶችን ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።

የቤተሰብን ጥቅም ያስረዱት የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ልጆችን ወይም ወጣቶችን በማስተማር ሂደት ቤተሰብን የሚያህል ተቋም አይገኝም ብለው በትውልድ መካከል የሚደረገው ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ቤተሰብ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ሰፊ ነው ብለዋል። ቤተሰብ አንድን ሕብረተሰብ በእነዚህና በሌሎች በርካታ ማሕበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በመግባት ትልቅ እገዛን ማድረግ እንደሚችል ከታመነበት፣ የቤተሰብንን ሕልውና ማስጠበቅ የቤተክርስቲያን ሃላፊነት እንደሆነ የሲኖዶሱ አባቶች አስረድተዋል። ቤተሰብ የአዳዲስ ርዮተዓለሞች ተጠቂ በመሆን፣ ኤኮኖሚያዊ እርዳታን እናቀርብላችኋለን የሚሉ ሃያላን መንግሥታት በሚያስቀምጡ መስፈርቶች በመገደድ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ቤተሰቦች መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴታቸውን እንዲያጡ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ተገንዝባ ቤተክርስቲያን ጥበቃን እንድታደርግላቸው የሚል ጥሪ አቅርበዋል።    

22 October 2018, 17:09