ፈልግ

2018.10.05 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 2018.10.05 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 

ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ “የዘመናችን ወጣት ቅዱሳንና ሰማዕታት ምስክርነት ያስፈልጋል”።

13ኛ ዙር ጉባኤን የተካፈሉት 251 የሲኖዶሱ አባቶች በውይይታቸው እንደገለጹት፣ ወጣቶቻችን ከሌሎች ወጣት ሰማዕታትና ቅዱሳን ብዙ መማር ይችላሉ ብለዋል። ቅድስና ተጨባጭ የሕይወት ምስክርነት እንጂ በቃል ብቻ የሚገለጥ አይደለም ያሉት የሲኖዶሱ አባቶች፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለይም ዝቅተኛ የክርስቲያን ቁጥር ባሉባቸው አገሮች ውስጥ ወጣቶች ስቃይ፣ ስደት እና መከራ እንደሚደርስባቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን በጥበብና በማስተዋል እንዲገነዘቡ ለማድረግ በሚል የመወያያ ርዕስ 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኝው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ይፋ ባደረገው የጠቅላላ ጉባኤ የውይይት ውጤቱ፣ በቤተክርስቲያን የዘመናችን ወጣት ቅዱሳንና ሰማዕታት የሕይወት ምስክርነት መታየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 13ኛ ዙር ጉባኤን የተካፈሉት 251 የሲኖዶሱ አባቶች በውይይታቸው እንደገለጹት፣ ወጣቶቻችን ከሌሎች ወጣት ሰማዕታትና ቅዱሳን ብዙ መማር ይችላሉ ብለዋል።

ቅድስና ተጨባጭ የሕይወት ምስክርነት እንጂ በቃል ብቻ የሚገለጥ አይደለም ያሉት የሲኖዶሱ አባቶች፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በተለይም ዝቅተኛ የክርስቲያን ቁጥር ባሉባቸው አገሮች ውስጥ ወጣቶች ስቃይ፣ ስደት እና መከራ እንደሚደርስባቸው አስታውሰዋል። በቅድሚያ በመካከለኛው የምስራቅ አገሮች ውስጥ በእምነታቸው ምክንያት በርካታ ምዕመናን እንደተገደሉ እንደዚሁም በሕንድ የክርስቲያን ማሕበረሰብ በሚበዛበት የዳሊት ጎሳ ላይም የሰብዓዊ መብት መረገጥ፣ መከራና ግድያና እንደሚፈጸምባቸው የሲኖዶሱ አባቶች አስታውሰዋል።

ክርስቲያናዊ ምሥክርነት አዳዲስ መለወጥን እያሳየ ይገኝእል፣

የአዳዲስ ወጣት ቅዱሳንና ሰማዕታት የሕይወት ምስክርነት፣ የወጣቶችን ሕይወት እየቀየረው ይገኛል ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት፣ እያንዳንዱ ወጣት እውነተኛ ምስክርነትን፣ ብጹዓን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የሚያሳዩት የጸሎት የሱባኤ ሕይወት እንደ ምስክርነት መመልከትን ይሻሉ ብለው በማከልም ወጣቶች በተግባር የታገዙ መልካም የወንጌል ምስክርነትን መመልከት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን በዓለም እንጂ የዓለም አይደለችም፣

ቤተክርስቲያን ለወጣቶች በቂ ጊዜን ጉልበትን በመስጠት እውነትንና ምሕረትን በፍቅር የሚመሰክር የቤተክርስቲያን አገልጋይ ማቅረብ አለባት ያሉት የሲኖዶሱ አባቶች፣ እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን እንደ ደካማነታችን የሚተወን ሳይሆን እንደማንነታችን ተቀብሎን ወደ አዲስ ሕይወት ያሸጋግረናል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን በመከራ ጊዜም ምስክርነቷን አታቋርጥም፣

የዘመናችንን ባሕል ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳት፣ አሁን የምንገኝበት ባሕል፣ ሐሰተኛ ምድራዊ ሃፍትን በማሳየት፣ በጊዜያዊ ደስታዎች በማታለል፣ ቤተሰብን በመለያየት፣ ከክርስቲያናዊ እሴቶች በማራቅ እግዚአብሔር ከሰዎች ልብ ውስጥ እንዲወጣ እያድረገ ይገኛል ብለዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም ይህ በሚሆንበት ጊዜ ቤተክርስቲያን በሞት ላይ ስልጣን ያለውን የኢሱስ ክርስቶስ ሃይል መመስከርን ማቋረጥ የለባትም በማለት ሃሳባቸውን ገልጸውል። የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወጣቶችን የሚያስደነግጥ ወይም የሚያስፈራራ ሳይሆን የበለጠ በርትተው የወንጌልን መልካም ዜና በይፋ የሚመሰክሩ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በመንፈሳዊ ሃይላት የታደለች ቤተክስቲያንን ለማፍራት ወጣቶች የመቁጠሪያ ጸሎትን ወደ እመቤታችን ዘንድ የሚያቀርቡ፣ የመስዋዕተ ቅዳሴን ምስጢር የሚካፈሉ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ስራ አጥነት እና ስደት የሚያስከትለው ችግር፣

በበርካታ ወጣቶች ዘንድ የሚታየውን የሥራ እጦትን ያስታወሱት የሲኖዶሱ አባቶች፣ ቤተክርስቲያን ሁሉን የምታቅፍ ቤተሰብ በመሆን፣ በስራ እጦት ምክንያት ችግር የሚደርስባቸውን ወጣቶች በልዩ ዓይን በመመልከት እገዛን ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል። ስራ ማጣት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለውን ስደት፣ የቤተሰብ መለያየትና ሌሎች ማሕበራዊ ችግሮችን ጉዳዩ ለሚመለከታችው መንግስታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ግልጽ በማድረግ የቤተክርስቲያን አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ብጹዓን ጳጳሳት አሳስበዋል። ወጣቶች በሁለገብ ማሕበራዊ እድገት ውስጥ ሰፊ አስተዋጽዖን ማበርከት ይችላሉ ያሉት ብጹዓን ጳጳሳት በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ወጣቶች ሃላፊነትን ተቀብለው ለማሕበራዊ እድገት በሚደረገው ጥረት በመሳተፍ፣ በተለይም ደጋፊ የሌላቸው ደሃ ቤተሰቦችን በመርዳት፣ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይም በመሳተፍ የሚችሉትን ሁሉ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን በክርስቲያንዊ ትምህርት አሰጣጥ ሂደት፣

የትምህርት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለወጣቶች የውይይት፣ የመተዋወቅ፣ የእውቀት፣ የመልካም ስነ ምግባር መቅሰሚያ ስፍራዎች እንደሆኑ በመገንዘብ ቤተክርስቲያን ለወጣቶች የመማር መብታቸው ተግባራዊነት የምታደርገውን ጥረት ማቋረጥ እንደሌለባት አሳስበዋል። በተጨማሪም ቤተክርስቲያን የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን ተንከባክባ በመጠበቅ  አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አደራ ብለው ቤተክርስቲያን በድህነት ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አቅም የሚያንሳቸው በርካታ ወላጆች መኖራቸውን በመገንዘብ፣ ለደሃ ቤተሰብ ልጆች ነጻ የትምህርት እድል መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ምስክርነት፣

የትናንትናውን 13ኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤን በተሳታፊነት የተካፈሉት አባላት በበኩላቸው እንደገለጹት፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኙት አዳዲስ እንቅስቃሴዎች በኩል የበርካታ ወጣቶች ሕይወት እየተለወጠ መሆኑን ገልጸው እነዚህ አዳዲስ መንፈሳዊ ማሕበራት ወይም እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ሃላፊነትን በመውሰድ የቤተሰብን፣ የሴቶችንና የወጣቶችን መንፈሳዊና ማሕበራዊ ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጥረት በማድረግ ላይ መኖራቸውን ገልጸዋል። ተሳታፊዎቹ በተጨማሪም የወንጌል አገልግሎት ስርጭትን ለማሳደግ ይረዳል ያሉትን የወጣቶች መኖሪያ መንደር ምስረታ አስፈላጊነት አስታውሰው እንደዚሁም የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶች መጎልበትንም በማስመልከት ገንቢ ሃሳቦችን አካፍለዋል።      

18 October 2018, 17:42