ፈልግ

2018.10.03 Apertura lavori Sinodo 2018.10.03 Apertura lavori Sinodo 

ወጣቶች ቤተክርስቲያንን ተረክበው ኢየሱስን ለማግኘት የሚያግዙ ብርሃን መሆናቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ፣ ወጣቶች፣ እምነትና ጥሪያቸውን በጥበብና በማስተዋል እንዲገነዘቡ ለማድረግ በሚል የመወያያ ርዕስ 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኝው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ጠዋት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፣ ወጣቶች ቤተክርስቲያንን ተረክበው ኢየሱስን ለማግኘት የሚያግዙ ብርሃን ናቸው መባሉ ታውቋል። 254 የሲኖዶሱን አባቶች የተሳተፉበት የትናንትናው ጉባኤ፣ የወጣቶች አዲስ ሐዋርያዊ ጉዞና የወንጌል ተልዕኮ ምርጫ በሚለው ርዕሥ መወያየቱ ታውቋል። በዚህ ጉባኤ ላይ በፈረንሳይ አገር በሉርድ ከተማ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት ስብሰባን ተካፍለው ከነበሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተጽፈው የተላኩ 1500 የሰላምታ ደብዳቤ ካርዶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደርሷቸዋል።

በፍቅር አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣

የትናንትናው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በአጽንዖት የተመለከተው ርዕስ፣ የወጣቶች ምርጫ የሚል እንደነበር ጉባኤውን በበላይነት የመሩት ብጹዕ ካርዲናል ላ ሮካ ተናግረዋል። ብጹዕ ሮካ የርዕሱን ትርጉም በአጭሩ ሲያስረዱ እንደተናገሩት ወጣቶች አዲስ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎችን ለመጀመር እንዲችሉ ልባቸውንና አእምሮአቸውን ማደስ እንደሚያስፈልግ ያሳስባል ብለዋል። ወጣቶች በጋራ ሆነው በፍቅር ወደ ፊት በመራመድ፣ ውጤታማ ቤተክርስቲያን በመሆን፣ ለዓለም በሙሉ መልካም ምሳሌ በመሆን፣ ሁሉን በሚጋብዝ መልኩ አስደሳች የወንጌል መልእክተኞች መሆን ይኖርባቸውል ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት፣ ብጹዕ ካዲናል ዳ ሮካ አስታውሰዋል።

ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን የመፈለጊያ ብርሃን እንዲሆኑ፣

የሕንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወጣቶችን በመወከል በዕለቱን በተከናወነው ጉባኤ ላይ የተገኘው ወጣት ፔርርሲቫል ሆልት እንዳስገነዘበው፣ ወጣቶች ኢየሱስ ክርስቶስን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት መካከል ብርሃን ሆነው መመስከር እንደሚችሉ እሙን ነው። ነገር ግን የዘመናችን ወጣት ምስክርነትን ለመስጠት አሁን ያለበት ደረጃ አስቸጋሪ ነው ብሎ፣ የዘመኑ ወጣት ለሕይወቱ መሪ የሚሆን ክርስቶስን ይፈልጋሉ፣ እንዲያውም እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ የማዕዘን ድንጋይ ሊሆን ይችላል ብሏል።

የቤተክርስቲያን መሪ ለመሆን ብቃት ያስፈልጋል፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የትናንትና ውሎ የቤተክርስቲያን ሃላፊነትን ተረክቦ በብቃት ሊመራ የሚችል የሰው ሃይል ባስቸኳይ ማዘጋጀትን የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም የቤተክርስቲያንን አደራ የሚቀበሉት ሌሎችን የሚያዳምጡ፣ ስለ ፍትህ የሚመሰክር፣ በሙስና ያልተበከለ ትክክለኛ ሕብረተሰብን ማፍራት የሚችል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ስለዚህም ለወጣቶች የሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በማጠናከርና ጥራትን በማሳደግ፣ ለሃላፊነት የሚበቃ ወጣትን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጉባኤው አሳስቧል። በዚህ ሃሳብ የተስማሙት የሲኖዶሱ አባቶች እንደገለጹት በዚህ ዕቅድ ዉጤታማ ለመሆን ከተፈለገ በአንዳንድ አገሮች የሚታየው የትምሕርት ስርዓት ደካማ እየሆነ በመምጣቱ ቤተክርስቲያን ይህን በመገንዘብ፣ ማሕበራዊ እድገትን ለማምጣት፣ ትክክለኛ ውሳኔን ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ፣ እውነትና ፍትህ ያለበትን መልዕክት ለሚጠብቅ ወጣት ጥራት ያለውን የትምህርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም ትምህርት ቤት ምንም እንኳን የሚፈልጉት በሙሉ የሚገኝበት ባይሆንም በተጓዳኝ ቤተክርስቲያን ወጣቶች በሕይወታቸው ወስጥ ለሚመላለሱ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስን የሚያገኙባት አስተማማኝ ስፍራ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የወደ ፊት ወጣት ትውልድ ዕዳ አለበት፣

ዛሬ ፍቅር ቀዝቅዟል፣ በሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው አንድነት ተዳክሟል፣ ፍትህም ተዛብቷል ያሉት የብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶስ አባቶች፣ የሰው ልጅ ማሕበራዊ ሕይወት ወደ ፍጆታ አዘንብሏል፣ ወጣቶችም የወደፊት ሕይወታቸው ዕጣ ፈንታን በሃላፊነት መውሰድ ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በድህነት ላይ ወድቀዋል። ይህ ሁሉ ቢሆንም በሕዝቦች መካከል እውነተኛ ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት ካለ ማሕበራዊ ተቋማትና የፖለቲካ ባለስልጣናት በአዲስ መልክ ተደራጅተው ለማሕበራዊ ሕይወት የሚጠቅም ስርዓትን ማቋቋም ይቻላል። ይህን ለማድረግ ቤተክርስቲያን ለወጣቶች አስፈላጊውን እገዛን በማድረግ፣ ከወጣቶችም ጋር በመወያየት ለሃላፊነት ማዘጋጀት ትችላለች ብለዋል። የሲኖዶሱ አባቶች በማከልም ወጣቶች ምስክርነትን በመስጠት እምነታቸውን ለማሳደግ ዕድልን የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የበጎ ሥራ አገልግሎት ዘርፍ እንዲከፈትና በመላው ዓለም ካሉት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር ግንኙነትን እንዲኖር በማለት ሃሳብ አቅርበዋል። 

ስደትና የአብያተ ክርስቲያናት ውይይቶች፣

የወጣቶችን መሰደድ አስመልክተው የተወያዩት የሲኖዶሱ አባቶች፣ ለስደተኛ ወጣቶች መልካም አቀባበል፣ ከለላና በደረሱበት አገር ራሳቸውን ለመቋቋም የሚችሉበት የስልጠናና የሥራ ዕድል ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሚሰደዱ ወጣቶች የአገራቸው ትልቅ ሃብት የሆነውን ባሕልና መንፈሳዊነት ይዘው ስለሚሰደዱ ይህም ለሚሄዱበት አገር ተጨማኣሪ ሃብት ስለሚሆን እነዚህ ወጣቶች ማንነታቸውን ጠብቀው፣ ለሚኖሩበት አገርም ባሕላዊ እሴት ሆነው እንዲገኙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በስደት ጉዞ ወቅት በሜዲተራኒያን ባሕር ሰጥመው የሚቀሩ በርካታ ስደተኛ ወጣቶችን ያስታወሱት የሲኖዶሱ አባቶች፣ እያንዳንዱ ስደተኛ ወጣት የራሱ ማንነትና ስም እንዳለው አስታውሰው በዋዛ ተረስቶ መቅረት የለበትም ብለዋል። ብጹዓን የጉባኤው ጳጳሳት ከስደት በተጨማሪ በሐይማኖቶች መካከል ሊኖር ስለሚገባው መቀራረብና ውይይት በመወያየት ሃይማኖት በሰዎች እምነት ጣልቃ ሳይገቡ፣ የሰዎችን የእምነት ነጻነትን በማክበር፣ እግዚአብሔር ባዘጋጀው የተለያዩ መንገዶች በመጓዝ ለድነት የሚበቁበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ቁምስናዎችን ማዋቀር፣ ሕዝባዊ እርቅን ማድረግ፣

ቤተክርስቲያን እውነተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ለማበርከት የሚስችላትን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስና ለወጣቶች  ፍቅር ስትል አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ይኖርባታል። ወጣቶች ከቤተክርስቲያን አባቶች በኩል የሚቀርብ ምስክርነትን የሚመለከቱ ከሆነ፣ ለማሕበራዊ አገልግሎት ራሳቸውን በማዘጋጀት፣ ወደ ድሆችና ከሕብረተሰቡ ወደተገለሉ ሰዎች መካከል ለመርዳት ፍላጎትና ድፍረት ሊኖራቸው ይችላል። ይህ በመሆኑ ቁምስናዎች ሐዋሪያዊ የአገልግሎት ዘርፎችን በማሳደግና በማሻሻል፣ ወጣቶች የፍቅር ሥራን ማበርከት የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ ምክሮችንና የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮች የሚቀስሙበትን መንገዶች ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበው በሀገረ ስብከቶች ዘንድ የወጣቶችን ጉዳይ የሚከታተል ምክር ቤት ማቋቋም እንደሚገባ አሳስበዋል።

መዝሙር ለወንጌል ስርጭት አገልግሎት ጠቃሚ መሣሪያ ነው፣

የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያለው የመዝሙር አገልግሎት፣ ለወንጌል አገልግሎት ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለወጣቶች ደስታን በመጨመር፣ እምነታቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ እንዲዘጋጅ የመዝሙር አገልግሎት እንዲጠናከር አሳስበዋል። በመዝሙር አገልግሎት በኩል ለወጣቶች የወንጌልን መልዕክት ማዳረስ እንደሚቻል፣ በዚህም የተነሳ ወጣቶች የእምነታቸውን ውበት መመልከት ይችላሉ በማለት ብጹዓን ጳጳሳቱ አስተያየታቸውን ሰጠተዋል።                        

17 October 2018, 18:36