ፈልግ

Giovani pre sinodo Giovani pre sinodo 

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቤተክርስቲያንና ወጣቶች የጋራ ውይይት እንዲያካሂዱ እድል ይሰጣል ተባለ።

ቤተክርስቲያን የመላው ዓለም ወጣቶች ማሕበራዊ ሕይወት የሚገኙበትን ደረጃ በዝርዝር በመመልከት ለዘመናችን ወጣቶች የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር ተጠርታለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. የተጀመረው 15ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት መደበኛ ሲኖዶስን በማስመልከት፣ የሲኖዶሱ ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ፋበነ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቤተክርስቲያንና በወጣቶች መካከል ግልጽ ውይይት ለማካሄድ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. የተጀመረው 15ኛው ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት መደበኛ ሲኖዶስ እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. እንደሚቆይ ታውቋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በጉባኤው ወቅት የሚወያይበት ርዕስ ወጣቶች፣ እምነታቸውና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በታከለበት አኳኋን በትክክል እንዲገነዘቡ የሚል እንደሆነም ታውቋል።

የጳጳሳቱ ሲኖዶስ ለርዕሱ ሰፋ ያለ ጊዜን በመስጠት፣ ቤተክርስቲያን የወንጌልን መልካም ዜና ለወጣቶች በብቃትና በፍሬያማነት የምታስተላልፍበትን መንገድ ከወጣቶች ጋር በሕብረት ሆና የምትፈልግበት አጋጣሚ እንደሚሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ጉባኤው ቤተክርስቲያን ለወጣቶች የሕይወትን ውበት ለማስተማር ጥሩ እድልን እንደምታገኝና ወጣቶችም በኑሮአቸው መካከል ሕይወትን በሙላትና በፍቅር መኖር የሚችሉበትን መንገድ የሚማሩበት አጋጣሚ እንደሚሆን ብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ፋበነ ለቫቲካን ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

ይህ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት የሚዳስስ በመሆኑ ለቤተክርስቲያን ትልቅ የሃላፊነት ድርሻን የሚሰጥ ይሆናል። ለውይይት የሚቀርቡ ርዕሶችም ከረጅም ውይይትና ጥናት እንዲሁም የመላውን ወጣቶች ፍላጎትና ጥያቄን ያካተተ በመሆኑና በመቀጠልም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተቀባይነትን ያገኘ መሆኑን ብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ገልጸዋል። ቤተክርስቲያን የመላውን ዓለም ወጣቶች ማሕበራዊ ሕይወትና የሚገኙበትን ሁኔታ በዝርዝር መመልከት ትፈልጋለች ያሉት አቡነ ፋቢዮ፣ ይህን ለማከናወን፣ ከወጣቶች ጋር አንድ ላይ ሆነን በመጓዝ በዘመናችን የወንጌልን መልካም ዜና ለወጣቶች ለማድረስ ተጠርተናል ብለዋል። በማከልም ወደዚህ የጉባኤ ዕለት ከመድረሳችን በፊት በተደረጉት የመዘጋጃ ጊዜያት ወጣቶች ለመንፈሳዊነትና የወንጌልን መልካም ዜናን ለመስማት ትልቅ ፍላጎት እንዳደረባቸው ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ፋበነ፣ ዛሬ የተከፈተው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አንድ ዓመት ያህል የፈጀ ውይይትና ዝግጅት የተደረገበት እንደሆነ ገልጸው፣ ይህን ለማድረግ የተዘጋጁ ጥያቄዎች በማሕበራዊ መገናኛ ሚዲያዎች በኩል በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች መላካቸውን ገልጸው በመቀጠልም 300 ወጣቶች የተሳተፉበት ስብሰባ በቫቲካን መካሄዱን አስረድተዋል። በዚህ መልኩ መላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የጳጳሳቱ ሲኖዶስ የመወያያ ርዕስ ምን መሆኑንና በምን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ለመረዳት ችሏል ብለዋል።

የአንዲት ቤተክርስቲያን ጳጳሳዊ ሲኖዶስ፣

ባለፈው መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት “Episcopalis communio” ወይም የኤጲስ ቆጶሳት አንድነት በሚለው ሰነድ ውስጥ የጠቀሱት መሠረትዊና እጅግ ጠቃሚ ሐዋርያዊ ሕግ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስን የቤተክርስቲያን ሙሉ አካል መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ብጹዕ አቡነ ፋበነ አስረድተዋል። ይህም የብጹዓን ጳጳሳት ጉዞን አንድ በአንድ በመከታተል በቅድሚያ የጉባኤውን አወቃቀር በመመርመር ቀጥሎም የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችንና ጳጳሳትን ለማገዝና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል የሚደርሳቸውን መመሪያውችንና ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መንገድን አመቻችቷል ብለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያጸደቁት አዲስ ሐዋርያዊ ድንጋጌ መላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በማሳተፍና በመካከላቸው የውይይት አድማስን በማስፋት፣ የሲኖዶሱ አባቶች ለጉባኤው ያወጡትን የመጨረሻ ሰነድ በስፋት እንዲመለከቱት ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ፋበነ በመጨረሻም በቅድመ ሲኖዶስ ወቅት በእርግጥም ወጣቶች ከቤተክርስቲያን ርቀው ከሆነ ወይም ቤተክርስቲያን ከወጣቶች ርቃ ከሆነ ተብሎ በቀረበው የውይይት መድረክ፣ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ምንም ዓይነት ቅራኔ እንደሌላቸው መግለጻቸውን ተናግረው በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወጣቶች የብቸኝነት ስሜት እንዳለባቸውና ቤተክርስቲያንም አሁን ከደረስንበት ዘመን ሁኔታ ወደ ኋላ የቀረች መሆኗን መግለጻቸውን አስረድተዋል።    

ዛሬ በሮም የተከፈተውን 15ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት መደበኛ ሲኖዶስ የሚካፈሉት፣ ብጹዓን ካርዲናሎችን፣ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ ክቡራን ካህናትን፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ከምዕመናን ወገን የመጡ ምሑራንን ጨምሮ ወደ 300 የሚጠጉ የጉባኤው አባላት መገኘታቸው ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በተለይም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ እ. አ. አ. በ1965 ዓ. ም. ያቋቋሙት እንደሆነ ታውቋል።

03 October 2018, 18:05