ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር እርቅን ለመፍጠር ጽኑ ምኞት አላቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ቅድስት መንበር ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ ጋር ስላደረገችው ጊዜያዊ ስምምነት ዓላማ በዝርዝር መናገራቸው ታውቋል።  ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው ጊዜያዊ ስምምነቱ በቻይና ከዚህ በፊትም ሆነ በሚቀጥሉ ዓመታት የሚሰየሙት ብጹዓን ጳጳሳት የቅድስት መንበርን እውቅና እንደሚኖራቸው ገልጸው ይህም በቻይና ለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሕይወት እጅግ አስፈላጊ፣ ከቻይና ሕዝባዊ ሪፓብሊክ ጋር ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግና አሁን በዓለማችን የሚታየው ውጥረት ረግቦ ሰላም እንዲወርድ ስለሚረዳ ነው ብለዋል።

የቅድስት መንበር ቀዳሚ ዓላማ ሐዋርያዊ አገልግሎትን የሚመለከት ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ቅድስት መንበር ሐዋርያዊ አገልግሎትዋን ለቻይና ሕዝብ በሚገባ ለማዳረስ እንድትችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ነጻነት እንዲኖራት ማድረግ፣ በምዕመናኖችዋና ማሕበራዊ ተቋማቶችዋ ዘንድ የራሷን የአስተዳደር መንገዶችን መዘርጋት እንደሆነ አስረድተው ይህን በማድረግ የወንጌል ስርጭት ተልዕኮዋን በብቃት ለመወጣት፣ ለቻይና ሕዝብ ሰላማዊ ግንኙነት መጎልበት፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎቶችን ያለ እንቅፋት ማሟላት እንዲቻል ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

በቻይና የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐዋርያዊት ቅድስት መንበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ጋር እንዲሁም ወደ ፊት ከሚሰየሙት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዲኖር መደረጉን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም እንደ ሌሎች ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳደረጉት ሁሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ለቻይና ሕዝብ ልዩ ፍቅርና አክብሮት አላቸው ብለዋል። አሁን የሚጠበቀው ከሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ሕጋዊ ከሆኑ የመንግሥት ባለስልጣናት ዕውቅናን ያገኙ መልካም ሐዋርያዊ አገልጋዮች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ሙሉ አንድነትና መተማመን እንዲኖር ማድረግና እንደሚያስፈልግ ገልጸው በሁለቱ ወገኖች የተደረሰው ስምምነት እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት እንደ መሣሪያነት እንደሚያገለግሉ ያላቸውን እምነት ገልጸው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሌሎችም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለመላው የቻይና ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያንና ገዳማዊያት እንዲሁም ምዕመናን በሙሉ፣ በመካከላቸው የቆዩትንና የአሁኖችን አለመግባባቶችንና ውጥረቶችን አስወግደው ወንድማዊ ስምምነትንና እርቅን እንዲያደርጉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጽኑ ፍላጎት ነው ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በማከልም እያንዳንዱ አገልጋይ የበኩሉን አስተዋጽዖን በማበርከት የተሰማራበትን የወንጌል አገልግሎት በብቃት ሊያከናውን፣ በተመሳሳይ መንገድ ለአገሩ መንፈሳዊና ቁሳዊ እድገትን፣ በመላው ዓለም ሰላምና እርቅ እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።       

27 September 2018, 16:52