ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ክርስቲያናዊ ቤተሰቦች የግለሰባዊ ባሕልን እንደሚቃወሙ ገለጹ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ ግርማቸው ተስፋዬ - ቫቲካን
በቫቲካን ከተማ የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከመስከረም 13 እስከ 16 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ. በኪሲናኑ ሞልዶቫ ስለቤተሰብ በተመለከተው በዓለም ኣቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። በዚህም ስብሰባ ወቅት ካርዲናሉ ኣንድ ግንባታ ለማካሄድ ሽክላ ወይም ጡብ ዋና ግብአት እንደሆነ ሁሉ ኣንድን ማኅበረሰብ ለመገንባት ቤተሰቦች ሁሉ ልክ እንድ ሸክላ የአንድ ማኅበረሰብ የጀርባ ኣጥንት ናቸው ብለው በዚህም ጉዳይ ዙሪያ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ሁልጊዜም ቤተሰቦችን ለማበረታታትና ለማገዝ መንፈሳዊ ጥንካሬም እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚሰሩና ከጎናቸው እንድሚቆሙ ማስታወቃቸውን የቫቲካን ከተማ የሬዲዮ ኣገልግሎት ባልደረባ ማርኮ ጉዌራን ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል።
እግዚኣብሔር በምድር ላይ ከሠራቸው ነገሮችህ ውስጥ እጅግ ከፍተኛውን ቦታ የያዘው ቤተሰብ መሆኑን በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። እግዚኣብሔር ሰውን ወንድና ሴት ኣድርጎ ፈጠራቸው በምድር ላይ ያለዉን ነገር ሁሉ በበላይነት እንዲመሩ ኣደራ ሰጣቸው። እግዚኣብሔር በራሱ ኣምሳያ የፈጠራቸውን ሰዎች በምድር ላይ ኑሩ እደጉ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት በመሬቷም ኣርሳችሁ ተጠቀሙ ምድርም እንድታድግና መልካም ፍሬም እንድታፈራ ተንከባከቡ ምድር በምታፈራዉም ፍሬ ተደሰቱ ምድሪቱንም ኣሳድጉ ብሎ ኣደራ እንደሰጣቸው እብራርተዋል።
በቫቲካን ከተማ የቅድስት መንበር ዋና ጸሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ይህ በዓለም ኣቀፍ ደረጃ በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. እ.አ.አ. በኣሜሪካ ፊላደልፊያ በተደረገው የዓለም ኣቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ዋዜማ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በስብሰባው ስለ ቤተሰብ በተደረገው ጸሎት ላይ ስለ ቤተሰባዊ ውበትና ቤተሰብ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ በሚል ሓሳብ የተናገሩትን ኣስታውሰዋል።
ቤተሰቦች የተስፋ ብርሃን
እኚሁ ካርዲናል ፓሮሊን በቅርቡ በነሓሴ ወር 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ. በአየር ላንድ ዱብሊን የተካሄደዉን የዓለም አቀፍ ካቶሊክ ቤተሰቦች ስብሰባ በማንሳት በዚህ ስብሰባ የተነሱት ሓሳቦች የተሰጡት ኣስተያየቶች በብዙ መልኩ ጠቃሚነታቸው የጎላ መሆኑንና ተጨባጭ በሆነ መልኩ በቤተሰብ መካከል በተለይም በኣንድ ወንድና ሴት ተጋቢዎች መካከል ስለሚኖረው የፍቅር ውበትና እግዚኣብሔር በቤተሰብ ላይ ያለው የደኅንነት ዕቅድ በሰፊው ያመላከተና ግንዛቤ ያስስጨበጠ መሆኑን ኣብራርተዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን ቤተሰቦች ሁሉ እንደ ቤተሰብ በሚኖሩበት ጊዜ በጣም ከበድ ያሉና ጫና የሚፈጥሩ ነገሮች ሊከሰቱ እንድሚችሉ ኣንስተው በዚህ ጊዜ ቤተሰቦች ሁሉ መጫወት ያለባቸውን ሚና ምን መምሰል እንደሚገባው ተንትነዋል። መሠረቱ ከእግዚኣብሔር የኣንድነቱ ምንጭ ፍቅር የጥሪው ምንጭ ፍቅር የሆነው ቤተሰብ ብለን የምንጠራው ምናልባትም ከመቼውም ጊዜ በላይ ኣሁን ባለንበት ዘመን በዓለም ላይ የተስፋ
ብርሃን በመሆን እንዲያንፀባርቅና እንዲያበራ ያስፈልጋል ብለው ሁልጊዜም ቢሆን የጋብቻና የቤተሰብ እውነታ ገደብ የሌለው ዘላቂነት ያለው መሆኑንና ይህም እውነታ ሁልጊዜ መታወጅና መሰበክ እንዳለበት ኣስረድተዋል።
ቤተሰብ የኅብረተሰብ ሁሉ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ነው
እንደ ካርዲናል ፓሮሊን ኣገላለጽ ቤተሰብ የኅብረተሰብ ሁሉ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ነው። ምክንያቱም በቤተሰብ ውስጥ የጋራ የሆነን ስብእና የምንላበስበት ነው። በተለይም ይላሉ ካርዲናሉ እጅግ በጣም ብዙ ቤተሰቦች ክርስቲያናዊ እሴቶችን በቤተሰባቸው ውስጥ እንዲያድግና እንዲጎለብት ይደርጋሉ። ይህም ክርስቲያናዊ ጥበብና ጉልበት ያላብሳቸዋል ይህ ደግሞ በቤተሰብም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለሚከሰቱት ማንኛዉም ዓይነት ችግሮችና ክፍተቶች በተገቢና ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ እንዲያፈቁና እንዲፈቱት ያስችላቸዋል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት በቫቲካን መንግሥት የቅድስት መንበር ዋና ፀሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፓሮሊን በተለያዩ ሀገራት ቤተሰቦችን ለማገዝ በመደረግ ላይ ያለው ተነሳሽነት እርካታ እንደሰጣቸውና ይህም ሁኔታ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንድሚያስፈልግ ገልፀው በተለያዩ የሃይማኖት እና የሲቪል ማህበራት የቤተሰብን ህይወት እና እሴቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ የሆኑትን ማህበራት ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል። እሳቸዉም በዚህ ስብሰባ ላይ መካፈላቸው በውስጣቸው ትልቅ ደስታን እንደፈጠረና ራሳቸውንም እድለኛ ኣድርገው እንድሚቆጥሩና ይህ ስብሰባ ለጋብቻ እና ለቤተሰብ ልዩ እና ጠቃሚ ድጋፍ የሚሰጥና ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል ኣጋጣሚ ነው ብለዋል።
በቀጠልም ካርዲናሉ ይህ በዓለም ደረጃ ቤተሰቦችን የማበረታታትና የማገዝ ሁኔታ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በልባቸው ያለና ይህንንም በተመለከተ ኣሞሪስ ሌቲዚአ (Amoris Laetitia) ከፍቅር የሚገኝ ደስታ በሚል የተተረጎመው የቅዱስ ኣባታችን ፍራንቼስኮስን ሓዋርያዊ ምክር የያዘውን ሰነድ ኣስታውሰዋል። እንደሚታወቀው ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በዚሁ ሓዋርያዊ ምክራቸው ውስጥ በቤተሰብና በጋብቻ ውስጥ ስለሚገኝ ደስታ በቤተሰብና በጋብቻ ውስጥ ስለሚከሰቱ የተለያዩ ፈተናዎች ላይ ጥናት በመድረግና በጉዳዩም ላይ በማተኮር እያንዳንዱ ቤተሰብ ድጋፍ መመሪያ እንዲሁም እገዛ ማድረግ እንደሚያስፈግ መናገራቸው ይታወሳል።
በግል ባሕል ውስጥ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶች
ካርዲናል ፓሮሊን ኣያይዘውም የዛሬው ቤተሰቦች በአንድ መልኩ የሚገጥሟቸው ከባድ ችግሮች ከተለያዩ ግላዊ እና ተለዋዋጭ ከሆኑ ባህል የሚመጡ ሲሆኑ በሌላ መልኩ ደግሞ ይህ ግለሰባዊ ባህል በመገናኛ ብዙኃን በፋይናንስ እና በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ ቢኖረዉም ቅሉ በመጨረሻ ግን ልክ እንደ ኣንድ ኣማራጭ እንጂ ወሳኝና መሠረታዊ ነገር ሆኖ ኣይወሰድም ብለዋል ። በመቀጠልም በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም የተደራጁ ሃይማኖቶች ውስጥ ይህ ግለኝነትን በተመለከተ ያለው ጽንሰ ሐሳብ የተወሰነና ሁል ጊዜም በዙሁ ዙሪያ ላይ ብጫ የሚያጠነጥን መሆን ኣይገባዉም በማለት ሓሳባቸውን ኣጋርተዋል።
እያንዳንዱን ግንኙነት የማመዛዘን ዘይቤ
በቫቲካን መንግሥት የቅድስት መንበር ዋና ፀሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፓሮሊን ሁሉንም ግንኙነቶች በኣንድ ደረጃ ላይ ማስቀመጥና በኣንድ ዓይን መመልከት በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ብቻ ማተኮሩ በቀጥታ ወደ የግል ሥነ-ምግባር ላይ ብቻ የሚያተኩር የሞራል ስብዕና እይታ ውስጥ ይከተዋል ብለው በአጭሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ ህብረተሰብን ለመገንባት የሚያስችል ጡብ ነው ምክንያቱም በፍቅር እና በደስታ የሚኖር ማህበረሰብ በየትኛውም ሰብዓዊ ልዩነቶች በጾታዎች እና በትውልዶች መካከል የጋራ እድገትና ልማት በሁሉም ረገድ እንዲኖር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ካርዲናሉ ቀጥለውም ሲያብራሩ ቤተሰብ ማኅበረሰብ እንዲያድግና እንዲጎለብት አስተዋፅኦ እንደሚያደርግና ኣሁንም ሁል ጊዜም አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ በግልፅ መግለጽ ይገባል።የአንድ ማህበረሰብ መዋቅር በቤተሰቡ አወቃቀር እና በእነዚህ ግንኙነቶች ላይ የተመሠረተ ነው ሲሉ ሓሳባቸውን ሰተዋል።
ቤተሰብ በዙሪያችን ባለው ዓለም ላይ ድልድይ ነች
ካርዲናል ፓሮሊን ሲናገሩ በተጨማሪም ኣሉ ቤተሰብን በዙሪያችን ባለው ዓለም ላይ ልክ እንደ ድልድይ ሆና ታገለግላለች። ክርስትያኖች ለዓለማችን የተስፋ ፏፏቴ የሆነውን የቤተሰብን ወንጌል ለማወጅ ደፋር እና ደስተኞች መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።
በመጨረሻም በቫቲካን መንግሥት የቅድስት መንበር ዋና ፀሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፓሮሊን በብሰባው ላይ ተሳታፊ ለነበሩቱ የር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ የቅርብ ክትትልና መንፈሳዊ ኣጋርነት ከእነርሱ ጋር አንደሚሆን በማስረዳት ቤተሰቦች ሁሉ ቤተክርስቲያንንና ህብረተሰቡን በኣንድነት ለማሳደግ በኣንድነት ለማነጽ እንድሚሠሩ ትልቅ እምነት እንዳላቸው በመግለጽ ሓሳባቸውን ደምድመዋል።
ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኃላ በቫቲካን መንግሥት የቅድስት መንበር ዋና ፀሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፓሮሊን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሞልዶቫ በይፋ የተመሠረተችበትን 25 ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን ሥርዐተ ቅዳሴ የመሩ ሲሆን ከሳቸዉም ጋር ኣብረው የኪሲናኑ ጳጳስ ሞንሲኞር ኣንቶ ኮሳ በማልዶቫ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሞንሲኞር ሚጉኤል ማኡሪ እንዲሁም ሌሎች ብጹኣን ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን በእሑዱም የቅድስት መንበር ዋና ፀሓፊ የሆኑት ካርዲናል ፓሮሊን በቲራስፖል ኣዲስ የተገነባዉን ቤተክርስቲያን መርቀው መክፈታቸው ታውቋል።