በደቡብ ኢጣሊያ የላምፔዱሳ ቁምስና ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ መልካም ምሳሌ ሆኖ ተገኘ።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት መንበር የሰዎች ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ክቡር አባ ሚካኤል ዠርኒ፣ በደቡብ ኢጣሊያ የላመፔዱሳ ቁምስና ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድና ወደ ማሕበራዊ ኑሮ ውስጥ በማስገባት፣ እንደዚሁም በድህነት የሚቸገረውን የአካባቢውን ሕዝብ እንዲቋቋም ለማድረግ የተጠቀመበት መንገድ የተመረጠ በመሆኑ በሌሎች አካባቢዎችም ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቻል ገለጹ።
ክቡር አባ ሚካኤል ዠርኒ በደቡብ ኢጣሊያ ግዛት በሆነው በላምፔዱሳ ቅዱስ ጀርላንዶ ቁምስና ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደተገነዘቡት ቁምስናው ስደተኞችን በማስተናገድ እያስመዘገበ ያለው ውጤት መልካም እንደሆነ ገልጸዋል። በቁምስናው የሚተዳደረውን ከፍተኛ የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት በጎበኙበት ጊዜ እንደገለጹት ቁምስናው ከሚያገኘው እርዳታ መካከል 50 በመቶ ወደ ደሴቲቱ ለሚመጡ ስደተኞች መቋቋሚያ ሲውል የተቀረው 50 በመቶ ደግሞ ለአካባቢው ደሃ ቤተሰብ እንደሚውል ገልጸዋል። ይህ የዕርዳታ ማከፋፈል ዘዴ ዕርዳታ በሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል ልዩነትን ሳያሳይ የሚከናወን በመሆኑ ውጤታማ እንደሆነና ዘላቂነት ያለው እንደሆነ አስረድተዋል። ስደት በዓለማችን ዋና መነጋገሪያ ርዕስ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ሚካኤል፣ የስደተኞች ጉዳይ ለቤተክርስቲያንም ቀዳሚ ርዕስ መሆኑን ተናግረዋል። ክቡር አባ ሚካኤል በማከልም የስደተኞች ጉዳይ የቤተክርስቲያናችን ቀዳሚ ርዕስ እንደመሆኑ ለስደተኞች የሚቀርቡ መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች በሙሉ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚመሩ ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያን ለስደተኞች የምትሰጠው አገልግሎት በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች የተዋቀረ እንደሆነ የተናገሩት ክቡር አባ ሚካኤል፣ ይሁን እንጂ የዘመናችን ያልተስተካከለ የባሕልና የኤኮኖሚ ሁኔታዎች ችግሮችን እያባባሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ያስተላለፉትን ምልዕክት በማስታወስ፣ በተግባር ሊተረጎሙ የሚያስፈልጉ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እነርሱም ለስደተኞች መልካም አቀባበልን፣ ጥበቃን፣ ስደተኞች የሚኖሩበት ማሕበረሰብ ስደተኞችን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግንና ስደተኞች ከሕብረተሰቡ ጋር አብረው የመኖር ባሕልን ማሳደግ እንደሆኑ አስረድተዋል። እነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች ቤተ ክርስቲያን ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የምታቀርበውን ድጋፍ ፍሬያማ ለማድረግ እንደሚያግዙ አባ ሚካኤል አስረድተው በማከልም ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከሁሉ አስቀድሞ ለኑሮአቸው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንደ መጠለያ ምግባን ልብስ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ መናገራቸውን ሲር የተሰኘ የቤተክርስቲያን የዜና ወኪል ገልጿል። ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ ትክክል አለመሆኑን የገለጹት አባ ሚካኤል፣ በስደተኞች ሊደርስ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት መከላከል እንደሚያስፈልግና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተዘረጉ ውጥኖችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሕግ ከለላን ሳይጠይቁ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሕግ ዘንድ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በደረሱበት አገር በሕጋዊ መንገድ ለሚኖሩት ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የተለያዩ የሞያ ስልጠናዎችን በመስጠት የሚቋቋሙበትንና የመኖሪያ ፈቃድን በቀላሉ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ክቡር አባ ሚካኤል አሳስበዋል።