ፈልግ

Father And Son From Honduras Seeking Asylum In The U.S. Await The Court's Decision On Their Status Father And Son From Honduras Seeking Asylum In The U.S. Await The Court's Decision On Their Status 

ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምግቦች ግብይትና ፍጆታ እንዲቆም ማሳሰቢያ ተሰጠ።

ባደጉት አገሮች ይሁን በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ከተሞች የሚቀርቡ ፈጣን ምግቦች የሚባሉት ዋጋቸው እርካሽ ቢሆንም ጥራታቸው ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ሲካሄድ የቆየው የምሁራን ስብሰባ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምግቦች ግብይትና ፍጆታ እንዲቆም ማሳሰቢያ በመስጠት መጠናቀቁ ታውቋል። በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የሳይንስ አካደሚ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ከዓለም ዙሪያ የተወጣጡ ከአርባ ምሁራን በላይ መሳተፋቸው ታውቋል። በስብሰባቸው ማጠቃለያም ረሃብን በማስወገድ በቂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምግቦች ገበያ ላይ እንድይውሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና እህል ሸማቾች ድርጅቶችን የሚወክሉ ምሁራን በቫቲካን በሚገኘው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ አራተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሁለት ቀን ስብሰባቸውን ትናንት ማጠቃለላቸው ታውቋል። ምሁራኑን ተቀብለው ያስተናገዱት በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ክፍል ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገርና ፕሮፈሰር ዮአቄም ቮን ብራውን፣ በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የሳይንስ አካደሚ ፕሬዚዳንት መሆናቸው ታውቋል። በቂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ሁሉም ሰው ሊኖረው ከሚገባ የሰብዓዊ መብት ጋር እኩል ነው ያሉት በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ተጠሪ አቶ ሆሴ ግራሲያኖ ዳ ሲልባ አሁን በሥራ ላይ ያለው ዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ለተመጋቢው በቂና ለጤና ተመጣጣኝ የሆነ የምግብ ዓይነት እያቀረበ አይደለም ብለዋል።

በዓለም የሰዎች የክብደት መጠን መጨመር።

ተጠሪው በሪፖርታቸው እንደገለጹት በዓለማችን ወደ 2 ሚሊያርድ 6 መቶ ሺህ ሰዎች ከትክክለኛው የሰውነት ክብደት መጠን በላይ ሲኖራቸው ከእነዚህም መካከል 672 ሚሊዮን ሰዎች በአዋቂዎች የዕድሜ ክልል ያሉ እንደሆነ ታውቋል። በሌላ ወገን ሲታይ በዓለማችን ውስጥ 821  ሚሊዮን በረሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች መኖራቸውን ተጠሪው አስረድተዋል። የክብደት መጠን መጨመር እንዲቆም ካልተደረገ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው አሃዝ እንደሚጨምር አስረድተዋል። ተጠሪው በማከልም ለተመጋቢው ሕብረተሰብ በሸቀጥ ማስታወቂያዎች በኩል ገበያ ላይ የሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶች በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉና በተለይም የቅባት፣ የስኳርና የጨው መጠናቸው ከፍተኛ በመሆኑ የክብደት መጠን እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ ምግብ ዋጋው እርካሽ ነው።

ባደጉት አገሮች ይሁን በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ከተሞች የሚቀርቡ ፈጣን ምግቦች የሚባሉት ዋጋቸው እርካሽና ጥራታቸውም ዝቅተኛ እንደሆነ አስረድተው በዚህ መልክ ወደ ገበያ የሚቀርቡ የምግቦች ዓይነቶች የመክፈል አቅማቸው ዝቅተኛ የሆናቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች የመሳብ ዝንባሌ እንዳለው አስረድተው የምግብነት ይዘታቸው ተመጣጣኝ አለመሆኑን አስረድተዋል። በተመጋቢው ጤና ላይ የሚያስከትሉ ጉዳቶችም ከፍተኛ እንደሆነ፣ ለምሳሌ ለልብ ሕመም፣ ለስኳር በሽታና ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች እንደሚዳርጉ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ተጠሪ የሆኑት አቶ ሆሴ ግራሲያኖ ዳ ሲልባ አስረድተዋል። ተጠሪው እንዳስረዱት በኢንዱስትሪ የታሸጉ በርካታ የምግብ ዓይነቶች በአሁኑ ጊዜ በማደግ ላይ ወዳሉት አገሮች እንደሚገብና እነዚህ የምግብ ዓይነታቸው የጨው፣ የሶዲዬም፣ የስኳርና የቅባት መጠናቸው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በጤና ላይ ጉዳት እያስከተሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በባሕላዊ መንገድ የተመረቱ ምግቦችን መጠን ማሳደግ፣

በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ የሳይንስ አካደሚ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተሳተፉት ምሁራን፣ መንግሥታት በሃገሮቻቸው የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን እንዲከታተሉ የሃገር ውስጥ አምራቾችንም እንድያበረታቱ አሳስበዋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ተጠሪ የሆኑት አቶ ሆሴ ግራሲያኖ ዳ ሲልባ በበኩላቸው ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል ጤናማ ባልሆኑ ምርቶች ላይ ቀረጥ መጨመር፣ የምርት ውጤቶች ያላቸው የንጥረ ነገር መጠን ግልጽ ማድረግ፣ ለሕፃናት በሚቀርቡ ምግቦች ላይ ጥንቃቄን ማድረግ፣ የስኳርና የጨው መጠንን መቀነስና የቅባት መጠናቸው ከፍተኛ የሆናቸውን የምግብ ዓይነቶችን ከገበያ ላይ እስከ ማስወገድ የሚሉ ይገኝባቸዋል። አቶ ሆሴ ግራሲያኖ ዳ ሲልባ በማከልም መንግሥታት በአገሮቻቸው የሚመረቱ የምግብ ምርቶቻቸውን ዓይነት እንዲያሳድጉ ገበሬዎችን በማበረታታት፣ በትምሕርት ቤት ለተማሪዎች የሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶች በአካባቢው ገበሬዎች የተመረቱ ቢሆን፣ ለተመጋቢዎች ከሚሰጡት ጥቅም በተጨማሪ ለአገር ውስጥ የኤኮኖሚ እድገት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብለዋል። ይህም ጥራቱን ያልጠበቀ የምርት ዓይነት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ለመቆጣተር ያስችላል ብለው በምግብ ዓይነቶችና ጥራታቸውንም በተመለከተ በትምህርት ቤቶች ሊሰጥ የሚገባውን ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መዘንጋት የለበትም ብለዋል።

በአዲስ አበባና በጀኔቭ መጭው ዓመት ሁለት ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፣

በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ተጠሪ የሆኑት አቶ ሆሴ ግራሲያኖ ዳ ሲልባ በመጭው የአውሮጳዊያኑ ዓመት 2919 ዓ. ም. በቂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምግቦች ግብይትን በተመለከተ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በጋራ ያዘጋጁት ሁለት ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች በአዲስ አበባና በጀኔቭ እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።                    

14 September 2018, 18:08