ፈልግ

PAROLIN CONFERENZA PAROLIN CONFERENZA 

“ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ አይርላንድ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተስፋን የሚሰንቅ ነው”።

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በዓለም ውስጥ ደስታን ለማምጣት በብቸኝነትና በሌሎች ችግሮች ውስጥ ለሚገኝ ዓለማችን ፍቅርን መመስከር ያስፈልጋል፤ በዓለም ሁሉ ፍቅር፣ አንድነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲነግስ የማድረግ ተልዕኮና ሚና አለበት።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አይርላንድ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተስፋን የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጉዞ ከመጀመራቸው ከጥቂት ቀናት በፊት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት ንግግር አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል በአይርላንድና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተፈጸሙትን ወሲባዊ ጥቃቶች፣ በሕብረተሰብ መካከል የቤተሰብ አስፈላጊነት እና ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያበረክቱት ሚና የሚሉ ይገኝባቸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን በመካሄድ ላይ ያለው ዓለም የቤተሰብ ስብሰባ ከጳጳሳት ሲኖዶስ በኋላ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ስብሰባ ምን መጠበቅ እንችላለን ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ ከሁሉ አስቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንዳስገነዘቡት ቤተሰብ የወንጌል የምስራች ዜና መሆናቸውንና የጳጳሳትም ሲኖዶስ ቤተሰብን በተመለከተ የሚያሳስበን ይህን ነው ብለዋል። የቤተሰብ መልካም ዜና መሆን ሲባል፣ ቤተሰብ በሚኖርበት ሕብረተሰብ መካከልና በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚናን ይመለከታል። ቤተሰብ ባለበት አካባቢ የሚወጣውን የፍቅር እና የታማኝነት እንዲሁም ልጆቻቸውን በወግና በስርዓት የማሳደግ ተልዕኮን በፍሬያማነት ማከናወን እንዲችል ድጋፍ መስጠት ማለት ነው። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓላማም ቤተሰብ በሚኖርበት ሕብረተሰብ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ በመሆን እያንዳድንዱ ሰው የሚመኘውን የደስታ ሕይወት እንዲኖር የሚያደርግ ፍቅርን እንዲያመጡ ማገዝ ያስፈልጋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለቤተክርስቲያንና ከእምነት ለራቁት ሁሉ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽዖ ምን እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቤተሰብ ወደ ሌሎች ዘንድ ለመድረስ ያላቸውን ችሎታ በማሳደግ ከወንጌል የሚገኘውን ደስታ መመስከር መቻል ያስፈልጋል። ቤተሰብ በዓለም ውስጥ ደስታን ለማምጣት ከፈለገ በብቸኝነት፣ በመለያየትና በሌሎች ችግሮች ውስጥ ለሚገኝ ዓለማችን ፍቅርን መመስከር ያስፈልጋል። ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ፍቅርን፣ አንድነትንና ሰብዓዊ ክብርን በዓለም ሁሉ እንዲነግስ የማድረግ ተልዕኮና ሚና አለበት ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በአንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ ስደት፣ ቤተሰብን በሚያጋጥም ቀውስ እና ግብረ ሰዶማዊነትን በተመለከተ የቤተክርስቲያን አቋም ምን እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቤተክርስቲያን የወንጌልን መልካም ዜና በምታውጅበት ጊዜ ለሰው ልጅ ሊሰጥ የሚገባው ክብር እንዳይጓደል ጥንቃቄ ማድረግን ትቀጥልበታለች ብለው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህን በማድረግ ለሌሎችም መልካም ምሳሌ ሆና መገኘት ያስፈልጋል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐዋርያዊ የቅድስት መንበር ስልጣን ጀምሮ በመልዕክታቸው የሰውን ልጅ በሚገኝበት ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያን ተቀብሎ አስፈላጊውን እንክብካቤና መንፈሳዊ አገልግሎት ማበርከት ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰው መንፈሳዊም ሆነ ማሕበራዊ አገልግሎትን ለማበርከት በቅድሚያ ሰዎችን ማዳመጥ፣ ውይይቶችንም ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ ዕድል አለ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስቀድመው እንደተናገሩት ቤተሰብን ከሚደርስበት አደጋ ለመታደግ ማህበራዊ ተቋማትን ማጠናከር፣ ሁለንተናዊ እድገታቸውን የሚያረጋግጡ መመሪያዎችን ማውጣት እና ተግባራዊነታቸውን መከታተል ያስፈልጋል ያሉትን ያስታወሱት ብጹዕ ካዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ይህ ጥረት ከግለሰብ ጀምሮ ወደ ቤተሰብ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል። በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ቤተሰብን ለማፍራት፣ በቤተክርስቲያን ሚስጢራት የታገዘ ቅድመ ዝግጅት መኖር ያስፈልጋል ብለዋል። ስለዚህ ወጣቶች የቤተክርስቲያን ምስጢራት አስፈላጊነትን በተለይም የምስጢረ ተክሊልን ትርጉም በሚገባ እንዲያውቁ ማስተማርና ክትትል ማድረግ፣ በቤተሰብ መካከል አለመግባባት ሲፈጠርም ከጎናቸው በመሆን ወደ ትክክለኛው መንገድ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው የፍቅር ምሳሌነት ነው ብለዋል። በእውነተኛ ፍቅር የተገነባ ቤተሰብን ለማዘጋጀት ቤተክስቲያን ብዙ የጣረች መሆኑ ቢታወቅም ገና ብዙ ይቀራል ብለው፣ ከዚህ ጎን የፖለቲካ መሪዎች፣ በማሕበረሰብ ዙሪያ የተሰማሩ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት የማሕበራዊ ኑሮን፣ በተለይም የቤተሰብን እድገት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽዖን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ዘንድሮ ዘጠነኛውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባን በማስተናገድ ላይ ያለች አይርላንድ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከጎበኟት ከ1971 ዓ. ም. ወዲህ በቤተክህነት በኩል የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በርካታ ችግሮች እንደተፈራረቁባት የገለጹት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ የተከሰተው ችግር ቀላል እንዳልሆነ፣ ቤተክርስቲያንንና መላውን ማሕበረሰብ እጅግ እንደጎዳና በመጉዳት ላይም እንዳለ ገልጸው፣ ይህ ቤተክርስቲያን ለዓለም በትሰጠው የወንጌል ምስክርነት እንቅፋት ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚና አሁንም በማስተላለፍ ላይ የሚገኙትን መልዕክት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ሰዎች አስፈላጊውን እንክብካቤ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የአይርላንድ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ድክመቶችዋን በመረዳት ያለፈው ስሕተት ወደ ፊት እንዳይደገም እርምጃዎችን ወስዳለች ብለዋል። ስሕተቶች እንደተፈጸሙ በማመን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን መለመን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አይርላንድ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ለአይርላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና ለመላው ምዕመናኖችዋ የተስፋ ጉብኝት እንደሆነ በማሰብ፣ ለአይርላንድን ሕዝብ እድገትና ደህንነት እንዲሁም ቤተክርስቲያን የምታቀርበውን አገልግሎት በሙሉ እንደ ቅዱስ ወንጌል ፈቃድ እንድታቀርብ ያግዛል ብለዋል።   

23 August 2018, 16:41