ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የሮም ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ካፒቶሊን ሂል ውስጥ ሆነው የሮማን ፎረምን በቅርብ ርቀት እያዩ ሲያደንቁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የሮም ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ካፒቶሊን ሂል ውስጥ ሆነው የሮማን ፎረምን በቅርብ ርቀት እያዩ ሲያደንቁ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳጳሳቱ ሮም የኢዮቤልዩ በዓል በሚከበርበት ወቅት እንግዶቿን በክብር እንድትቀበል ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሮም ከተማ የጎረጎሳዊያኑን የ 2025 ዓ.ም. የኢዮቤልዩ በዓል ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ እያለች ለከተማዋ ከንቲባ እና አስተዳደር ባደረጉት ንግግር፥ የኢዮቤልዩ አከባበር እንዴት በህብረተሰቡ ውስጥ የአብሮነት መንፈስ እንደሚያጎለብት በማንሳት፣ በእስር ቤት ውስጥ ቅዱስ በር እንደሚከፍቱ አስታውቀዋል። ሆሊ ዶር ወይም ቅዱሱ በር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ወደ ድነት የሚወስደውን፣ እሱም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ለሰው ልጆች የተከፈተው አዲስ እና ዘላለማዊ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ይወክላል ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሮም ከተማ የመጪውን የኢዮቤልዩ ዓመትን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት የሮማው ከንቲባ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘የካፒቶሊን አሴምብሊን’ እንዲጎበኙ ያቀረቡላቸውን ግብዣ ከተቀበሉ በኋላ ሰኞ ማለዳ የቲበር ወንዝን ተሻግረዋል።

ይህ እንደ ጎረጎሳዊያኑ በ 2025 የሚከበረው የኢዩቤሊዩ ክብረ በዓል በታላቁ ኢዮቤልዩ መጨረሻ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያስተዋወቁት ሲሆን፥ ቀደም ብሎ የምህረት ኢዮቤልዩ ተብሎ ሲከበር ከነበረው የጎረጎሳዊያኑ የ2015–2016 ኢዩቤሊዩ ቀጣይ ክብረ በዓል ነው።

በ2025 የሚካሄደው ይህ በዓል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የተከበረ ሁለተኛው በዓል ይሆናል። ብዙዎች እንደሚያውቁት ኢዮቤልዩ ልዩ የጸጋ ዓመት ነው፣ በዚህ ጊዜ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን የምልአተ ፍትሃት ምኞት ማለትም ለራሳቸው ወይም ለሟች ዘመዶቻቸው የኃጢአት ስርየት እንዲደረግላቸው የመጠየቅ እድል የሚሰጥበት ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለከንቲባው እና አስተዳደራቸው ባደረጉት ንግግር በቅድስት መንበር እና በማዘጋጃ ቤቱ መካከል የላቀ ትብብር እንዲኖር ላደረጉት አስተዋጽዖ እና ከተማዋ መንፈሳዊ ነጋዲያንን በተቻለ መጠን በተሻለ መንገድ ለመቀበል እንድትችል ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

ሮም ዓለም አቀፋዊ መንፈስ ያላት ከተማ መሆኗን በመግለጽ፥ “ከተማዋ በተካነችው የበጎ አድራጎት አገልግሎት፣ የእንግዳ ተቀባይነት አገልግሎት እና ከመንፈሳዊ ነጋድያን እስከ ቱሪስት ያሉትን ብሎም ስደተኞችን፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉትን፣ ድሆችን፣ እስረኞችን፣ የተገለሉትን፣ ብቸኛ ሰዎችን እና ህሙማንን በአጠቃላይ የተለያዩ እንግዶችን ለመቀበል ያላት ቁርጠኝነት ልዩ ነው” ካሉ በኋላ፣ “እነዚህ ተግባራት የዚህ መንፈስ እውነተኛ ምስክሮች ናቸው” ብለዋል።

“ስልጣን ሁሉንም ሰው ሲያገለግል፣ ህጋዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ የዜጎችን፣ በተለይም ደካማ የሆኑትን ፍላጎት ለማሟላት ሲውል ያኔ ምሉዕ ይሆናል፥ ይህንንም መመስከር አለባቸው”

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተመሳሳይ ስም ያለው እና ኮረብታ ላይ በሚገኘው በሚካኤል አንጄሎ ወደ ተሰራ አስደናቂው የካፒቶሊን አደባባይ መድረሳቸው ለህዝቡ ከታወጀ በኋላ ‘የሰንደቅ ዓላማ አዳራሽ’ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ውስጥ ንግግር አድርገዋል።

ካፒቶሊን በሮም ውስጥ "ካምፒዶሊዮ" ተብሎ የሚጠራው የማዘጋጃ ቤት መቀመጫ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ከንቲባው ሮቤርቶ ጓልቲየሪ የክብር መዝገብ ላይ ከመፈረማቸው በፊት፣ የስጦታ መለዋወጥ እና ክብረ በዓሉ ከመጀመሩ በፊት ለአፍታ ቆይታ ያደረጉበት ሥፍራ ነው።

አስደናቂ የሆነው የሮማ ከተማ ታሪክ

ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የከተማዋን አስደናቂ ታሪክ በማጉላት፥ “ጥንታዊቷ ሮም በሕጋዊ እድገቷና ድርጅታዊ አቅሟ እንዲሁም ለዘመናት የቆዩ ጠንካራና ዘላቂ ተቋማት ግንባታ ብዙ ህዝቦች በእርጋታና እና ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚኖሩባት ከተማ ሆናለች” በማለት ተናግረዋል።

ብጹእነታቸው የጥንት ሮማውያን ባሕል ብዙ መልካም ባሕርያትን በማንሳት እና የእነዚህ እሴቶች ተጠናክረው መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት “ያለጥርጥር በርካታ መልካም እሴቶችን ያሳለፈው ይህ ጥንታዊ የሮማውያን ባሕል፥ ታላቅና ጥልቅ የሆነ ወንድማማችነትን፣ ፍቅርን፣ ተስፋን እና ነጻነትን ለመለማመድ ራሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ነበረበት” ብለዋል።

የክርስትና እሴቶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሮማውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የክርስትና መስፋፋት እንዴት በሰማዕታት ምስክርነት እና በጥንት የክርስቲያን ማህበረሰቦች መልካም ሥራ ተበረታቶ እንደ ነበር፤ ብሎም ክርስትና ለግለሰቦች ሥር ነቀል ተስፋ እና እንደ ባርነት የመሳሰሉ በአንድ ወቅት ተፈጥሯዊ እና የማይለወጥ ተደርገው ይታዩ የነበሩ ፈተናዎችን የሚጋፈጡ ተቋማትን አበርክቷል በማለት ጠቁመዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከሮም የቄሳር ሥርዓት ወደ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘመን ስለመቀየሯ ሲናገሩ፣ ለውጦች ቢደረጉም የሮማ ዓለም አቀፋዊ ጥሪ የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ተልእኮ የክርስቶስን መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማወጅ ከመልክአ ምድራዊ ድንበሮች በላይ ነው ብለዋል።

“ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፣ ነገር ግን የሮማ ዓለም አቀፋዊነት ጥሪ የተረጋገጠ እና ከፍ ያለ ነበር” ብለዋል።

የላተራን ስምምነቶች

ዘንድሮ የላተራን ስምምነቶች የተሻሻሉበትን 40ኛ ዓመት መከበሩን የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ “ስምምነቱ የኢጣልያን መንግሥት እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘እያንዳንዱ በራሱ ሥርዓት፣ ነፃና ሉዓላዊነት ያለው’ በግንኙነታቸው እና በጋራ ትብብራቸው ውስጥ ለሰው ልጅ እድገት እና ለሀገር ጥቅም እነዚህንም መርሆች ለማክበር ቃል የሚገባ ነው” ብለዋል።

የኢዮቤልዩ ዓመት አካታችነት

በመሆኑም ሮም ለጎረጎሳዊያኑ 2025 ዓ.ም. ኢዮቤልዩ በዓል እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ከተማዋ የሚጎርፉትን መንፈሳዊ ነጋዲያንን እና ቱሪስቶችን ለመቀበል ዝግጁ እንድትሆን ጥሪ በማቅረብ፥ በክልላዊ እና በብሔራዊ ባለስልጣናት መካከል ያለው ንቁ ትብብር ሁሉንም ሊጠቅም ይችላል ብለዋል።

መጪው የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በከተማው ገጽታ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው፣ የከተማዋን ውበት እንደሚያሻሽል እና የህዝብ አገልግሎቶችን ይበልጥ ቀልጣፋ እንደሚያደርግ ብሎም በማዕከሉ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመሃል እና በዳርቻዎች መካከል ያለውን መቀራረብ ያጎለብታል” ብለዋል።

ቅዱሱ በር

ድሆችን፣ ብቸኞችን፣ ህሙማንን፣ እስረኞችን እና የተገለሉትን ጨምሮ ለበጎ ተግባር፣ ለእንግዳ ተቀባይነት እና የተቸገሩትን ማገልገልን የመሳሰሉ የሮማን ሁለንተናዊ መንፈስ በመድገም ይህ የኢዮቤልዩ ዓመት በሮም እስር ቤቶች በአንዱ ቅዱስ በር ለመክፈት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

                           “በእስር ቤቶች ውስጥ ቅዱስ በር ለመክፈት ወስኛለሁ”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በመጨረሻም እንደተናገሩት፥ ሮም እውነተኛ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ክቡር ባህሪዋን በማሳየት እንድትቀጥል አበረታተዋል።

የኢዮቤልዩ ዓመት፡ ዕድል እና ኃላፊነት

ወደ ከተማዋ የሚጎርፉትን ጎብኝዎች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማንሳት፣ ይህም ለከተማዋ አዲስ አመለካከት እንደሚሰጥ ጠቁመው፥ የሮማ ግዙፍ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ለዜጎቿ እና ለመሪዎቿ ትልቅ መብት እና ኃላፊነት እንደሆነ አስረድተዋል።

“የሚገጥማት ችግር ሁሉ የታላቅነቷ 'ተገላቢጦሽ' ሲሆን አንዳንዴ የሚከሰቱት ቀውሶች ደግሞ የሲቪል፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የባህላዊ እድገት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል።

                            “አንዳንዴ የሚከሰቱ ችግሮች የእድገት እድል ሊሆኑ ይችላሉ”

‘ሳሉስ ፖፑሊ ሮማኒ’

በመጨረሻም የከተማውን የአስተዳዳሪነት ሚና ለማስጠበቅ በሁሉም የአስተዳደር አካላት መካከል ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበው፣ ለቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ፍቅር ‘ሳሉስ ፖፑሊ ሮማኒ’ በማለት አስታውሰዋል።

‘ሳሉስ ፖፑሊ ሮማኒ’ ማለት በሮም የሚገኘው ቅድስት ድንግል ማርያም ህፃኑ ኢየሱስን ተሸክማ፣ ህፃኑ ደግሞ በእጁ ወንጌል ይዞ ለሚያሳይ ምስል የተሰጠ ካቶሊካዊ ስያሜ ሲሆን፥ ምስሉም በቦርጌስ ቤተ መቅደስ ይገኛል።

ብጹእነታቸው በመጨረሻም “ወደ ሮም በመጣሁ ቁጥር ሳሉስ ፖፑሊ ሮማኒን እጎበኛለሁ እናም በጥረቴ እንድታግዘኝ እጠይቃታለሁ” ካሉ በኋላ፣ በረከቷን በመለመን “ከተማዋን እና የሮምን ህዝብ እንድትጠብቅ፣ ተስፋን እንድታሰርጽ እና በጎ አድራጎትን እንድታበረታታ እጸልያለሁ” ብለዋል።
 

12 June 2024, 16:41