ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመጀመሪያው የዓለም የሕጻናት ቀን በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመጀመሪያው የዓለም የሕጻናት ቀን በተከበረበት ወቅት   (Vatican Media)

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ 'መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ አብሮን ይጓዛል' ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የሕፃናት ቀን በተከበረበት ወቅቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ “እግዚአብሔር ፈጠረን፣ ኢየሱስ አዳነን፣ መንፈስ ቅዱስም በሕይወታችን ሁሉ አብሮን ይጓዛል” ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

የመጀመሪያው የአለም ህፃናት ቀን የመጨረሻ ዝግጅት - ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በግንቦት 16/2016 ዓ.ም በሮም ኦሊምፒክ ስታዲየም ወደ 50,000 የሚጠጉ ወጣቶችን ያሳተፈ ዝግጅት ተካሂዶ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል እሁድ ግንቦት 17/2016 ዓ.ም  - በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በልዩ ዝግጅት ተጠናቋል።

እለተ ሰንበቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የክርስቲያን ማሕበረሰቦች ዘንድ የቅድስት ስላሴ በዓል የሚከበርበት እለተ ሰንበት ነበር፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱም በዓሉን በስብከተ ወንጌል አስተንትነዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ሥላሴ ውስጥ ያለውን ጥልቅ አንድነት እና ፍቅር አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን "ወደ እግዚአብሔር አብ፣ ወደ እግዚአብሔር ወልድ እና ወደ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንጸልያለን። ስንት 'አማልክ' አለ? ከሦስቱ አካላት አንድነት" ይገለጻሉ ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል የተሰበሰቡትን ልጆች "ወደ እግዚአብሔር አብ ስንጸልይ ሁላችንም የምንጸልየው ጸሎት ምንድን ነው?" እነሱም “አባታችን ሆይ” ብለው መለሱ፤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባታችን ሁላችንን ከፈጠረንና በጥልቅ ከሚወደን አብ ከእግዚአብሔር ዘንድ መመሪያ እንዲፈልጉ አበረታቷቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትኩረታቸውን ወደ ልጆች በማዞር ኢየሱስ በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው   አስፈላጊነት ተናገሩ። "ወደ ኢየሱስ የምንጸልየው እሱ ስለሚረዳን፣ ወደ እኛ ስለሚቀርብ፣ እና ምስጢረ ቁርባን ስንቀበል እንኳን ኢየሱስን እንቀበላለን እናም ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ይለናል" ብሏል። ከዚያም “ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ይቅር ይላል የሚለው እውነት ነው?” ሲሉ ጥያቄ ለልጆች አቅርበው ነበር። እናም ልጆቹ "አዎ!" ብለው መለሱ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል ስለ መንፈስ ቅዱስ የተናገሩ ሲሆን መንፈስ ቅዱስን መረዳት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አስረድቷል፣ መንፈስን በውስጣችን እንዳለ መለኮታዊ ህላዌ፣ በጥምቀት እና በቅዱስ ቁርባን የተቀበልነው ነው ያሉት ቅዱስነታቸው "መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ አብሮን የሚሄድ እርሱ ነው" በማለት ሕጻናቱን ይህንኑ ሐረግ አብረው እንዲደግሙ ያበረታቱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ መልካምን እንዲያደርጉ እንደሚመራቸው እና በአስቸጋሪ ጊዜያት መጽናናትን እና ጥንካሬን እንደሚሰጣቸው አስረድቷል።

በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን ልጆቹን ስለ ማርያም ነገሯቸው። "የሰማይ እናታችን ስም ማን ይባላል?" ብለው ቅዱስነታቸው ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን  ልጆቹም “ማርያም” ብለው መለሱላቸው። ጸጋ የሞላሽ የሚለውን ጸሎት ከልጆች ጋር አብረው መጸለያቸውም ተገልጿል።

ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወላጆቻቸው፣ ለአያቶቻቸው፣ ለታመሙ ህጻናት እንዲጸልዩ እና ለአለም ሰላም እንዲጸልዩ ሕጻናት ልጆችን ያበረታቱ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ሁላችንም ወደ ፊት እንድንሄድ ጸልዩልን" ብለዋል።

26 May 2024, 16:43