ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቬኒስ በከወጣቶች ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቬኒስ በከወጣቶች ጋር በተገናኙበት ወቅት   (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለወጣቶች ስልኮቻችሁን ገታ አድርጉና ለሌሎች ትኩረት ስጡ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ከተማ የሆንችውን ቬኒስን ሲጎበኙ፣ ብቻቸውን በመሆናችን ወይም ባለመረዳታችን ከማማረር ይልቅ ሌላውን በምንረዳበት መንገድ ላይ በማተኮር ወጣቶች ራሳቸውን ለሌሎች ሰዎች ስጦታ አድርገው እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ሚያዝያ 20/2016 ዓ.ም ጠዋት በቬኒስ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ስብሰባው በቬኒስ አርት ቢያናሌ በሰሜናዊ ጣሊያን ከተማ ቅዱስነታቸው ያደረጉት የአንድ ቀን የሐዋርያዊ ጉብኝት ሶስተኛው ክስተት ነበር።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለወጣቶች ሲናገሩ ሁላችንም የእግዚአብሔር ተወዳጅ ልጆች የመሆንን ታላቅ ስጦታ እንደተቀበልን እና ስለዚህም የእርሱን ደስታ ለሌሎች እንድናካፍል ተጠርተናል ብለዋል።

“እኛ ያለንበትን ውበት በጌታ መልሰን ለማግኘት እና ወጣቶችን የሚወድ እና ሁልጊዜም በሚያስደንቀን በወጣት አምላክ በኢየሱስ ስም ለመደሰት ዛሬ እዚህ መጥተናል” ብሏል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት እንደምትሆን በሰማች ጊዜ የፈጸመችውን ድርጊት የሚገልጹ “በፍጥነት ተነስታ ሄደች” በተሰኙት ሁለት ግሦች ላይ አስተንትኖ አድርገዋል።

እግዚአብሔር እኛን ለማንሳት እንደ ልጆቹ አድርጎ ያየናል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቬኒስ ለሚገኙ ወጣቶች “ተነሡ” ብለዋል። “የተፈጠርነው ለገነት ነውና ከመሬት ተነሱ። እይታችሁን ወደ ላይ ለማንሳት ከሀዘናችሁ ተነሱ። በህይወት ፊት ለመቆም ተነሱ ፣ ሶፋ ላይ ለመቀመጥ አይደለም፣ ተነሱ ወደ ፊት ሂዱ” ብለዋል ።

እያንዳንዳችን ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ ማድረግ ያለብን የመጀመሪያው ነገር ትንሽ ጸሎት በማድረግ ስለ ህይወታችን ስጦታ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው፡- “አምላኬ፣ ለህይወት አመሰግንሃለሁ። አምላኬ ሆይ በሕይወቴ እንድወድ አድርገኝ። አምላኬ አንተ ሕይወቴ ነህ” ማለት ይገባናል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወጣቶች ዓለማችንን ወደ ግራጫ ጥላዎች የሚቀይሩትን "ጨቋኝ ኃይል" መዋጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "በእርሱ የሚታመኑትን ፈጽሞ አያሳዝንም፣ ነገር ግን ሁልጊዜም ይቅር ስለሚል ጌታ በእጁ እንዲይዘን እንፍቀድ" ብለዋል።

ስንወድቅም ሆነ ስንሳሳት እግዚአብሔር እኛን እንደ አባት በእጁ ይዞ ሊወስደን በእዚያ ይገኛል፣ ምክንያቱም እኛን የሚመለከተን እንደ “የሚነሱ ልጆች እንጂ ክፉ አድራጊዎች ለመቅጣት አይደለም” በማለት ተናግረዋል።

ወደ ስማርትፎንዎ ሳይሆን ሌሎችን ይመልከቱ

ከእንቅልፋችን ወይም ከኃጢአታችን ከተነሳን በኋላ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ በጽናት በኢየሱስ “መቆየት” አለብን ያሉት ቅዱስነታቸው ክርስቲያኖች በፈጣን ስሜቶች እና ጊዜያዊ እርካታ ከመኖር ይልቅ በቅዳሴ ላይ በማህበረሰቡ ውስጥ በመጸለይ በእምነት እና በፍቅር አብረው እንዲጸኑ ተጠርተዋል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም “በእኔ ዙሪያ ያሉ ሁሉ፣ ሁሉም ሰው በሞባይል ስልካቸው፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና በቪዲዮ ጨዋታዎች ላይ ተጣብቆ ለብቻው ነው” ልትሉ ትችላላችሁ። “ነገር ግን፣ ያለ ፍርሃት የአሁኑን ሁኔታ መቃወም አለባችሁ፡ ህይወትን በእጃችሁ ያዙ፣ ተሳተፉ። ቴሌቪዥኑን ያጥፉ እና ቅዱስ ወንጌልን ክፈቱ፣ የሞባይል ስልኮቻችሁን አስቀምጣችሁ ከሰዎች ጋር ተገናኙ” ማለታቸው ተገልጿል።

ልክ እንደ ቬኒስ ቦይ እንደሚሽከረከሩት ጎንዶላዎች፣ ወጣቶች እግዚአብሔር እንዲረዳቸው በማድረግ የአሁኑን ጊዜ መቃወም አለባቸው ያሉት ሊቀ ጳጳሱ “መቅዘፍ መደበኛ መሆንን ይጠይቃል። "ነገር ግን መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም ጽናት ሽልማቶችን ያመጣል" ብለዋል።

ለሌሎች ስጦታ ነን

ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማርያም “ሄደች” ወደሚለው ሁለተኛው ግሥ ሐሳብቸውን ዘወር ያደረጉ ሲሆን “መነሳት ራስን እንደ ስጦታ መቀበል ከሆነ መሄድ ማለት ራስን ስጦታ ማድረግ ማለት ነው” ብሏል። "ሕይወት ስጦታ ከሆነች፣ ራሴን ለሌሎች አሳልፌ በመስጠት እንድኖር ተጠርቻለሁ"ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቬኒስ የተሰበሰቡ ወጣቶችን የእግዚአብሔርን በፍጥረቱ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያቀርበውን ጥሪውን እንዲቀበሉ ጋብዘዋል።

"ፍጥረት የእራሳችን የውበት ፈጣሪ እንድንሆን ይጋብዘናል፣ ከዚህ በፊት ያልነበረ ነገር እንድንፈጥር ይጋብዘናል" ብሏል። "ሕይወት ለመሰጠት እንጂ ለማስተዳደር አይጠይቅም፣ ነፍስን ከሚያደነዝዝ የማህበራዊ ሚዲያ የሰመመን ሕይወት አለም መውጣት አለብን።

የሕይወት ጎዳናዎችን በወንጌል ይሳሉ

በማጠቃለያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች ከልባቸው ቀለል ያለ ጸሎት እንዲፈጥሩ እና “መልስ ማግኘት ላልቻሉ ሰዎች የፍቅር መግለጫ” እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

“ልባችሁን ለእግዚአብሔር ክፈቱ፣ አመስግኑት፣ እናም ያላችሁትን ውበት ተቀበሉ። በሕይወታችሁ ውደዱ” ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭቷል። “ከዚያ ሂዱ! ውጡ እና ከሌሎች ጋር አብራችሁ ሂዱ፣ ብቻቸውን ያሉትን ፈልጉ፣ ዓለምን በፈጠራችሁት ቀለም ቀቧት፣ የሕይወት ጎዳናዎችን በወንጌል መዐዛ ቀቡ። ተነሥታችሁ ሂዱ” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው ንግግራቸውን አጠናቋል።

29 April 2024, 14:31