ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላትን በቫቲካን ሲቀበሏቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አባላትን በቫቲካን ሲቀበሏቸው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በሥራዎቹ መካከል ጸሎትን እንዲያዘወትር አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓመታዊ ንግደታቸውን በሮም ያደረጉ የሰሜን አሜሪካ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለዋቸዋል። የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ልዑካን ቡድንን ዓርብ ሚያዝያ 4/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፋውንዴሽኑ ቅድስት መንበር የምታበረክተውን የበጎ አድራጎት ተግባር ለማገዝ የሚያደርገው ልግስና ያለውን መንፈሳዊ ጠቀሜታ አብራርዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ምኞትን መሠረት በማድረግ በሰሜን አሜሪካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1988 ዓ. ም. የተመሠረተው ጳጳስ ፋውንዴሽኑ ላለፉት 36 ዓመታት በዓለም ዙሪያ በተለይም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተለይተው ለታወቁት እና ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ለሚጠይቁት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጎ አድራጎት ዕቅዶች የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ታውቋል።

የኢየሱስን ፍቅር ወደ ተቸገሩ ሰዎች ዘንድ ማምጣት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓመታዊ መንፈሳዊ ንግደታቸውን በሮም በማድረግ ላይ የሚገኙ 140 የሚደርሱ የፋውንዴሽኑ አባላትን በቫቲካን በመቀበል ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ፋውንዴሽኑ ድሆችን፣ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በአሁኑ ወቅት በጦርነት እና በዓመፅ የተጎዱትን ጨምሮ ለልዩ ልዩ ትምህርታዊ፣ የበጎ አድራጎት እና ሐዋርያዊ ዕቅዶች ማስፈጸሚያ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፋውንዴሽኑ በተጨማሪም በሮም በሚገኙ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙት ምእመናን፣ ገዳማውያን፣ ገዳማውያት እና የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እንዲሁም ከታዳጊ አገሮች ለሚመጡት ካህናት የሚሰጠውን የነፃ ትምህርት ዕድል ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ፋውንዴሽኑ በልዩ ልዩ ተግባራት አማካኝነት፥ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ድሆችን በመንከባከብ እና በመርዳት እንዲሁም በርካታ ቤተ ክርስቲያናትን በማነጽ ላይ የሚገኙ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪዎችን መርዳት መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

እምነትን ማሳደግ

የፋውንዴሽኑ ተግባር እና ተነሳሽነት ምንጩ የካቶሊክ እምነት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ አባላት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ምስጢራት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ፣ በተለይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. ለኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በጸሎት እና በስግደት እምነታቸውን እንዲመግቡ አሳስበዋል።

ይህ መንፈሳዊ ገጽታ ከተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና አካባቢዎች ተወጣጥተው እና ዕርዳታን ከሚቀበሉ ሰዎች ጋር ወንድማማችነትን የሚያጎለብት በመሆኑ ለጥረታቸው ጠቃሚ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ለጋስ አገልግሎታቸው ከሁሉም በላይ በራስ ወዳድነት እና በግዴለሽነት ተለይቶ በሚታወቅ ዘመናችን መካከል አስፈላጊ ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በ36 ዓመታት ውስጥ ከ2,400 በላይ ፕሮጀክቶች ታግዘዋል

በፋውንዴሽኑ ድረ-ገጹ ላይ በሠፈረው መረጃ መሠረት ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1988 ዓ. ም. ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተመረጡ ከ2,400 በላይ ፕሮጀክቶችን እና የነጻ ትምህርት ዕድሎችን ለማገዝ ከ225 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል።

ፋውንዴሽኑ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ለተመረጡ ፕሮጄክቶች 9,921,000 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አቅዷል።

13 April 2024, 16:52