ፈልግ

በእስራኤል ጥቃት ከወደሙት የጋዛ አካባቢዎች መካከል አንዱ በእስራኤል ጥቃት ከወደሙት የጋዛ አካባቢዎች መካከል አንዱ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መሪዎች ሰላምን የማስፈን አቅም እንዲኖራቸው ጸሎት አቀርቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መጋቢት 29/2016 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ በጋራ ወደ እመቤታችን የሰማይ ንግሥት ዘንድ ጸሎት ለማቅረብ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ም ዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው በዩክሬን፣ በፍልስጤም እና በእስራኤል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በድርድር መፍትሄ እንዲያግኝ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በማያያዝም የፖለቲካ መሪዎች ቆም ብለው በድርድር ሰላም ሊገኝ በሚችልበት መንገድ ላይ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክትም፥ በጦርነት ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች በተለይም በዩክሬን፣ በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ የሚያቀርቡትን ጸሎት እንዲቀጥሉ ምዕመናንን አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በስልጣን ላይ የሚገኙት የፖለቲካ መሪዎች ግጭቶችን ለማስቆም የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ በማለት የሚያቀርቡትን ያላሰለሰ ጥሪ በመድገም፥ ፖለቲካዊ መፍትሄን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ላይ የተሰማሩት ሰዎች ልብ እንዲበራላቸው እና እንዲደግፋቸው ወደ ትንሣኤው ጌታ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

በማከልም “በአገራት ውስጥ ያሉ ውጥረቶችን ለመቀነስ የሚሠሩትን በሙሉ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲደግፋቸው እና ለመደራደር በሚያደርጉት ጥረት ብርታትን እንዲሰጣቸው” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። የፖለቲካ መሪዎችን በማስታወስ ባቀረቡት ጸሎታቸው፥ ከሞት የተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሪዎቹ ቆም ብለው ለድርድር የማሰብ ችሎታን እንዲሰጣቸው ቅዱስነታቸው ጸልየዋል።

በድጋሚ የቀረበ ጥሪ

ቅዱስነታቸው በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሳይታክቱ በዓለማችን ውስጥ በጦርነት አደጋ ውስጥ ለወደቁት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች መካከል ሰላም እንዲወርድ ሲማጸኑ ቆይተዋል። በተለይም ሩሲያ በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ወረራን ካካሄደችበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት ወር 2022 ዓ. ም. እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ እና በእስራኤል ጦር ሠራዊት መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 7/2023 ዓ. ም. ግጭት ተቀስቅሶ፥ የሐማስ ታጣቂ ቡድን ከ1,300 በላይ ሰዎችን ገድሎ 250 ሰዎች ማገቱን ተከትሎ የእስራኤል ሠራዊት ለስድስት ወራት በተከታታይ በተኮሰው ቦምብ ከ33,000 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበት ጦርነት አብቅቶ ሰላም እንዲወርድ ምዕመናን እንዲጸልዩ ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

 

08 April 2024, 17:10