ፈልግ

ኢራን ወደ እስራኤል ካወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች መካከል ኢራን ወደ እስራኤል ካወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች መካከል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምሥራቅ ለውይይት እና ለሰላም ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ዓመፅ ለማስቆም እና ሁሉም አገራት ጋዛ ውስጥ የሚሰቃዩ ሰዎችን እየረዱ ለድርድር እና ለሰላም ጥረት እንዲያደርጉ በማለት ልባዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር በመሆን ወደ እመቤታችን ቅድስት ማርያም የሰማይ ንግሥት ዘንድ የጋራ ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባሰሙት ንግግር፥ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን አመጽ በማስታወስ፥ አመጽን የሚያቀጣጥሉ ድርጊቶች እንዲቆሙ በማለት ልባዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘረችበትን ዘገባ በጸሎት፣ በጭንቀት እና በሐዘን እንደሚከታተሉት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ ማንም ሰው የሌሎችን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል እንደማይገባ፣ በምትኩ ሁሉም ሀገራት ከሰላም ጎን ሊቆሙ እንደሚገባቸው ተናግረው፥ እስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ጎን ለጎን በሁለት ግዛቶች ውስጥ በሰላም እንዲኖሩ መርዳት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ሁለት ተጎራባች አገራት መኖር ጥልቅ እና ሕጋዊ ፍላጎታቸው እንዲሁም መብታቸው ነው! ሲሉ አክለዋል።

በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና የድርድር መንገድ በቁርጠኝነት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። በጋዛ ያለውን የሕዝቡን ስቃይ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሰብዓዊ እልቂት እየደረሰ በመሆኑ የሕዝቡን ስቃይ ለማቃለል የሚቻል ጥረት ሁሉ እንዲደረግ እና ከወራት በፊት በሐማስ ታጣቂዎች የታገቱት እስራኤላውያን እንዲፈቱ በጸሎት ጠይቀዋል። “በሕዝቦች ላይ የሚደርስ መከራ ብዙ ነው!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ከአሁን በኋላ ጦርነት፣ አመጽ እና ግፍ እንዳይኖር መወያየት እና ለሰላም መጸለይ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት መርዳት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በጦርነቶች የሚሰቃዩ ሕፃናትን በተለይም በዩክሬን፣ በፍልስጤም፣ በእስራኤልን እና በምያንማር ውስጥ የሚገኙትን ሕጻናት በጸሎታቸው በማስታወስ ምዕመናንም በዓለማችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን እንዲጸልዩ ጥሪ አቅርበዋል።

በጦርነት ምክንያት በሕጻናት ላይ ስለሚወድቅ ሸክም የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቤተ ክርስቲያን ከግንቦት 17-18/2016 ዓ. ም. ባለው ጊዜ የመጀመሪያውን ዓለም የሕፃናት ቀን እንደምታከብር ገልጸዋል። እሑድ ሚያዝያ 6/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ሕጻናት እና በመላው ዓለም ንግግራቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው፥ ዕለቱን ለማስተዋወቅ ጥረት ያደረጉትን በማመስገን፥ ወደ ዝግጅቱ ዕለት የሚያደርጉትን ጉዞ በጸሎት እንደሚደግፉት አረጋግጦላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ከመላው ዓለም ወደ ሮም የሚመጡ ሕጻናትን በደስታ እንደሚጠበቋቸው ተናግረው፥ ሰላም የሰፈነበት የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ለሚያደርጉት ጥረትም ብርታትን ተመኝተውላቸዋል

 

 

 

15 April 2024, 17:09