ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ምዕመናን የሴቶችን ሚና በጸሎት እንዲደግፉት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሚያዝያ ወር እንዲሆን ያዘጋጁትን የጸሎት ሐሳብ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ይፋ አድርገዋል። በዚህ የጸሎት ሃሳባቸው በማኅበራዊ እና መንፈሳዊው ዘርፍ በሚያበረክቱት አገልግሎት ሴቶችን በጸሎት መደገፍ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዛሬው ኅብረተሰብ ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን የጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሴቶች ሰብዓዊ ክብር በሁሉም ባሕሎች እንዲታወቅ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚደርስባቸው አድሎ እንዲያቆም፥ ለዚህም ክርስቲያኖች አብረዋቸው እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

ሴቶችን የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት የጸሎት ሐሳብ የቪዲዮ መልዕክት ጋር የተያያዙ ናቸው። ቅዱስነታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደነገጉ መርሆዎች እና በተጨባጭ አሠራር መካከል ያለውን ትልቅ ክፍተት ገሃድ ባደረጉበት መልዕክታቸው፥ በንድፈ ሃሳብ ወንዶች እና ሴቶች እኩል ሰብዓዊ ክብር እንዳላቸው ቢታወቅም ነገር ግን በተግባር እንደማይታይ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ አድሎአዊ ሕጎችን በመጥቀስ ተጨባጭ ምሳሌዎችን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቀጣይነት ያለውን የትምህርት ሂደት ማደናቀፍ፣ ለተለያዩ የሥራ ዕድሎች እርዳታን መከልከል እና በብዙ አገሮች የሴቶች ግርዛት ዛሬም ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን አስታውሰዋል።

በመሆኑም መንግሥታት ይህንን አድልዎ ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው እና የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። አደግን የሚሉ አገራትን ጨምሮ በብዙ የዓለም ክፍሎች ሴቶች የጥቃት እና እንግልት ሰለባ እንደሚሆኑ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሴቶችን የማናከብራቸው ከሆነ ማኅበረሰባችን እድገትን ሊያሳይ አይችልም ብለዋል።

በዓለማችን ውስጥ ቅራኔዎች እንዳልጠፉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በአንዳንድ አገሮች ሴቶች የትምህርት እና የሥራ ዕድል ሲኖራቸው፣ በንግድ ተቋማት እና በድርጅቶች ውስጥ የመሪነት ሚና ሲጫወቱ በሌሎች ብዙ አገራት ደግሞ የወንዶችን ያህል ተመሳሳይ ዕድሎች እንደማያገኙ ጠቅሰዋል። በሥራው ዓለም ከሁለት ሴቶች መካከል አንዷ 23% ከወንዶች ያነሰ ገቢ እንደምታገኝ እና በትምህርቱም ዓለምም እንዲሁ ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ ሴቶች ቁጥር አናሳ እንደሆነ ታውቋል።

ኒጀር ውስጥ የትምህርት ዕድል የሚያገኙት ሴቶች ብዛት 27% ብቻ እንደሆኑ እና ይህም ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ችግር እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2030 ዓ. ም. 8% ያህል ሴቶች እና ልጃገረዶች በአስከፊ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ እና 25% በቂ የዕለት ምግብ እንደማያገኙ ተገምቷል።

ወንዶች እና ሴቶች እኩል ሰባዓዊ ክብር አላቸው

ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት የተቀደሰ እና ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ የክርስትና እምነት ዋና መርህ ያሳስባል። (ዘፍ. 1፡26-27)። ባለፈው ዓመት በጥቅምት ወር በተካሄደው የብጹዓን ጳጳሳት 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሴቶችን ሚና የተመልከተ ሪፖርት መቅረቡ ይታወሳል።

በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው፥ ወንዶች እና ሴቶች በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ የፍጥረታትን አንድነት እና ልዩነት የሚገልጹ እንዲሁም ሴቶች እና ወንዶች በጥሪያቸው ሁለት የተለያዩ የመሆናቸው ልምዶች በሲኖዶሱ ወቅት መገለጹ ይታወሳል።

በጉባኤው ወቅት በሴቶች እና በወንዶች መካከል ስላለው የእርስ በርስ ግንኙነት አወንታዊ ተሞክሮ የተገኘበት እንደነበር ይታወሳል። በቀደሙት የሲኖዶሱ ሂደቶችም ቤተ ክርስቲያን ሴቶችን ከሐዋርያዊ አገልግሎት እና ከምስጢራት አኳያ ለመርዳት እና በኅብረት ለመጓዝ ቁርጠኝነትን ለማድረግ ጥሪ መቅረቡን የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በሠነዱ ላይ ገልጸዋል።

ሴቶች የሁል ጊዜ ብርቱዎች ናቸው

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ፣ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሴቶችን እንደ ደቀ መዛሙርት አድርጎ እንደተቀበላቸው ገልጸው፥ ይህ በጊዜው በነበረው ማኅበረሰብ ውስጥ አዲስ እንደ ነበር አስረድተዋል። ወንጌሎች እንደሚመሰክሩት፥ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በሐዋርያት እና በጥንቶቹ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የነበራት መሆኑንም አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ለሌሎች የማወጅ ተልዕኮ ለወንድሞቹ ለመግደላዊት ማርያም እንደሰጣቸውም አስታውሰዋል።

በታሪክ ውስጥ ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ አስተዋፅዖ ማበርከታቸው ያስታወሱት አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፥ የአቪላዋ ቅድስት ቴሬዛ ፣ የሲዬናዋ ቅድስት ካታሪና እና የሊሴዩስ ቅድስት ተሬዛ የቤተ ክርስቲያን ዶክተሮች እንደሆን እና ሌሎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቅዱሳት ሴቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ወር ጸሎት ሃሳባቸው እንዳሳሰቡን፥ “ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጠው የሴቶች ክብር በሁሉም ባሕሎች ዘንድ እንዲታወቅ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚደርስባቸው አድሎአዊ ድርጊቶች እንዲያቆም በጸሎት እንጠይቅ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ሴት ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች እና ለሚጫወቱት ሚና እውቅናን መስጠት እንደሚገባ የተናገሩት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ፥ ያለ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ እድገትን ማምጣት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

 

10 April 2024, 16:06