ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔር ምሕረት የቤተ ክርስቲያን ዋና ማዕከል ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “24 ሰዓት ለእግዚአብሔር እንስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ሮም ውስጥ በሚገኝ ቅዱስ ፒዮስ 5ኛ ቁምስና የተዘጋጀ የምሕረት ጸሎትን መርተዋል። ዘንድሮ ለአሥራ አንደኛ ጊዜ የተዘጋጀውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመሩበት ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ የንስሐ ምስጢር በጥምቀት ምስጢር የጀመርነውን የአዲስ ሕይወት ጉዞን እንደገና እንድንጀምር ያስችለናል ሲሉ ዓርብ የካቲት 29/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተካሄደው የንስሐ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሮም በሚገኝ ቅዱስ ፒዮስ አምስተኛው ቁምስና ውስጥ የተካሄደው ዓመታዊ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ፥ “24 ሰዓት ለእግዚአብሔር እንስጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በዐቢይ ጾም ወቅት እንዲቀርብ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስጀመሩት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያናት በራቸውን ክፍት በማድረግ ኑዛዜ መግባት እና ጸሎት ማቅረብ ለሚፈልጉ ምዕመናን ዕድሎችን ለማዘጋጀት ነው ተብሏል።

"በአዲስ ሕይወት መራመድ"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በአዲስ ሕይወት መመላለስ” በሚለው በዘንድሮው መሪ ርዕሥ ላይ ትኩረት በማድረግ ቃለ ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ብዙውን ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን የአዲስ ሕይወት ውበት እይታን ልናጣው እንችላለን ብለው፥ ይህም ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊጎዳ ይችላል በማለት አስገንዝበዋል።

“በመንገዳችን ጸንተን ብንቆይም፣ ነገር ግን በምስጢረ ጥምቀት የጀመርነውን መንገድ፣ የመጀመሪያ ውበታችንን እና ወደ ፊት የመጓዝ ስሜትን እንደገና ለማግኘት የሚያግዘንን አዲስ ምልክት መፈለግ ይኖርብናል” ብለዋል።

“ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ወደ አዲስ ሕይወት እንደገና የምንመለስበት መንገድ የእግዚአብሔር የይቅርታ መንገድ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የእግዚአብሔር ይቅርታ ውስጣችንን በማጽዳት ወደ አንድነት ጎዳና በመመለስ ወደ ምስጢረ ጥምቀት ሕይወት ዳግም ይመልሰናል” ብለዋል።

ነገር ግን የተከፈተ እና የተዋረደ ልብ ሊኖረን እንደሚገባ፣ የራሳችን ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ እኛን የሚያውቀን እና ልባችንን ሊፈውስ እና ከክፉም ሊያድናት የሚችል እግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ፥ እንደ ለምጻሙ ሰው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርበን፥ “ከፈለግህ ልታነጻኝ ትችላለህ” ልንል ይገባል ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያደርግልን የሚፈልገው ይህን ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንድንታደስ፣ ነፃ እንድንወጣ፣ ደስተኞች እንድንሆን እና በአዲሱ የሕይወት ጎዳና ልንጓዝ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ቅዱሳት ምስጢራት የክርስቲያናዊ ሕልውና መሠረት ናቸው

ከእግዚአብሔር ይቅርታ ጋር መገናኘትን ማቋረጥ የለብንም ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እግራችንን ወደ ትክክለኛው መንገድ የምንመልስ ከሆነ ኃጢአትን አሸንፈን ለዘላለም ከላያችን መጣል እንችላለን ብለዋል።

“ንስሐ መግባት የአምልኮ ልምምድ ብቻ ሳይሆን የክርስቲያን ሕልውና መሠረት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የንስሐ ምስጢር የሚመሩ ካኅናት የእግዚአብሔርን ምሕረት የቤተ ክርስቲያን ማዕከል እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ካህናት ይቅርታን ለሚለምኑት ዘወትር ይቅርታን እንዲያደርጉ፥ ምናልባት ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ የሚፈሩትን ለማገዝ፣ የፈውስ እና የደስታ ምስጢራትን ለማደል በልበ ሙሉነት እንዲቀርቡ አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ ዓይነት ስህተቶች ሊያነጻን እንደሚችል በማስታወስ፥ “ኢየሱስ ሆይ! አንተ ልታነጻኝ እንደምትችል እና ያንተ ምሕረት እንደሚያስፈልገኝ አምናለሁ፤ ወደ አዲስ ሕይወት ዳግም እንድመለስ እርዳኝ” በማለት በጸሎት ወደ ምስጢረ ንስሐ እንዲቀርቡ ምእመናንን ጋብዘዋል።

 

09 March 2024, 17:33