ፈልግ

የዳሪየን የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር የዳሪየን የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር   (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የስደተኞች ጉዳይ እንደ ክርስቲያን ይመለከተናል ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኮሎምቢያ እና ኮስታ ሪካ የድንበር ክልሎች ጳጳሳት ጋር በፓናማ እና በኮሎምቢያ መካከል ባለው የዳሪየን የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር ውስጥ በሚያልፉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዙሪያ ላይ የሚያሳዩትን ግድየለሽነት እንዲያጠፉ አሳስበዋል ።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ “ፋሲካን የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ብለው ለጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ ከኮሎምቢያ እና ከኮስታሪካ ድንበር የመጡ ጳጳሳት እና የፓናማ ጳጳሳት “በዳሪን [ክልል] ውስጥ፣ ከስደተኛ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መጋቢት 11/2016 ዓ.ም ለጳጳሳቱ ባስተላለፉት መልእክት፣ “ስደተኞቹ በአስቸ ጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እኛን እየጠበቁን ነው፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ጎልማሶችን እና ሕፃናትን ከተለያዩ አከባቢዎች የተውጣጡ ቢሆኑም አንድ በሚያደርጋቸው በእንባ እና በሞት ባህር ዳርቻ ውስጥ መኖራቸው ነው” ብለዋል።

የሦስቱ ሀገራት ጳጳሳት በፓናማ ተገናኝተው “ፋሲካ ከስደተኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር” በሚል ርዕስ በተለይ ቤተክርስቲያኒቱ የምታደርገውን ሐዋርያዊ አገልግሎት እጅግ አደገኛውን የ“ዳሪዬን መተላለፊያ” አቋርጠው ለመሻገር በሚሞክሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ላይ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል። በመካከለኛ እና ደቡብ አሜሪካ ክልሎች አቋርጠው የሚያልፉትን ስደተኞች ለመርዳት ያለመ ስብሰባ እንደሆነም ተገልጿል።

እ.አ.አ በ2023 ዓ.ም ከ500,000 በላይ ስደተኞች በኮሎምቢያ እና ፓናማ መካከል ያለውን የጫካ ኮሪደር አቋርጠዋል ተብሎ ይገመታል። እ.አ.አ 2024 ዓ.ም ተጨማሪ ስደተኞች አደገኛውን ጉዞ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኤጲስ ቆጶሳት ባስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያን በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን አገሮች የምታደርገውን ጥረት አጉልተው ገልጸው፣ ቤተክርስቲያን ድንበር የሌላት፣ የሁሉም እናት ለመሆን ምንጊዜም ትጥራለች ብለዋል።

ለክርስቲያኖች ተግዳሮት

“እያንዳንዱ የትውልድ አገሩን ጥሎ የሚሄድ ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂ ክርስቲያን እንደመሆናችን ይሞግተናል” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። በከተሞቻችን ውስጥ ካለው “እንግዳ ተቀባይ ወንድማማችነት” ጎን ለጎን ያለውን “ዳሪያንን የሚያደማ ግድየለሽነት” በማለት በምሬት ተናግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ይህንን ግድየለሽነት ለማጥፋት ሳትታክቱ እንድትሠሩ አበረታታችኋለሁ፣ ስለዚህም አንድ ስደተኛ ወንድም ወይም እህት ሲመጣ፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የፍርድ መንፈስ የማይሰማቸው፣ ነገር ግን የሚቀበላቸው ቦታ ያገኛሉ። ረሃብና ጥማታቸውን የሚያረኩበት፣ ተስፋም የሚያንሰራራበት ቦታ ሊሆን ይገባል ቤተክርስቲያን ሲሉ ተናግረዋል።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የስደተኞችን አገልግሎት ቸል እንዳይሉ አሳስበዋል፣ “የማይሰደዱበት መብት” ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከተቋም አሠራር አልፈው ለመሄድ ዝግጁ የሆኑ ቀሳውስት እና የሐዋርያዊ አገልግሎት የሥራ ባለሟሎች ከስደተኞች ጋር መቀራረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። መደበኛ መሰናክሎችን በማለፍ፣ ቤተክርስቲያንን እየመራ፣ ከስደተኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር፣ በተስፋ ጎዳናዎች ላይ መራመድ ያስፈልጋል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልእክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “ሁላችንም ያለ ልዩነትና ማንንም ሳንለይ ሁሉንም ለመቀበል፣ ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ እና ለማዋሃድ የተዘጋጀ ቤተ ክርስቲያን መስርተናል፣ እያንዳንዱም በሥራና በግላዊ ቁርጠኝነት የበኩሉን አስተዋጾ የማበርከት መብት እንዳለው ተገንዝበናል። ለሁሉም ጥቅም እና ለጋራ ቤታችን ጥበቃ ማድረግ ይገባል ካሉ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።

21 March 2024, 15:53