ፈልግ

"ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር አምሳያዎች ናቸው" በሚል ለተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም "ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር አምሳያዎች ናቸው" በሚል ለተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሥርዓተ-ፆታ ርዕዮተ ዓለም የዘመናችን አስከፊ አደጋ እንደሆነ ገለጹ

ሥርዓተ-ፆታን በማስመልከት በቫቲካን ከየካቲት 22-23/2016 ዓ. ም. ለተካሄደው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት አስተላለፉ። "ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር አምሳያዎች ናቸው" በሚል ርዕሥ ለተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሥርዓተ-ፆታ ርዕዮተ ዓለም በመባል የሚታውቀው ሃሳብ በሰው ልጆች መካከል ያሉ ልዩነቶች የሚያጠፋ በመሆኑ የዘመናችን አደጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሲምፖዚዬሙ ተካፋዮች ዓርብ የካቲት 22/2016 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሥርዓተ-ፆታ ርዕዮተ ዓለም በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት ሁሉ የሚያጠፋ እና ይህን ልዩነት ማጥፋት ማለት ሰብዓዊነትን ማጥፋት ማለት እንደሆነ አስረድተው፥ ወንድና ሴት የሰው ልጆች በምትኩ በፍሬያማ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

ስለ ሲምፖዚዬሙ

ቅዱስነታቸው ይህን የገለጹት፥ "ወንድ እና ሴት የእግዚአብሔር አምሳያዎች ናቸው" በሚል ርዕሥ ስር የሰው ልጆች አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና የባህል ጥናት ጥሪ አስፈላጊነትን በማስመልከት ከየካቲት 22-23/2016 ዓ. ም. ለተካሄደው ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው እንደሆነ ታውቋል።

ሲምፖዝዬሙን ያስተባበሩት በቅድስት መንበር የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ዋና ሃላፊ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ማርክ ኦሌት፥ በቫቲካን የሰው ልጅ ጥናትና ምርምር ማዕከል (CRAV) ጋር በመተባበር ሲሆን፥ ክህነታዊ ሥነ-መለኮት በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ተካሂዶ የነበረው  ዓለም አቀፍ ሲምፖዚዬም ተከታይ እንደሆነ ታውቋል።

ለሲምፖዝዬሙ ያዘጋጁትን መልዕክት በጤናቸው መጓደል የተነሳ ማቅረብ ባይችሉም ረዳታቸው ሞንሲኞር ፊሊፖ ቻምፓኔሊ እንዲያነቡላቸው የጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዋናው የሲምፖዝዬሙ መሪ ሃሳብ ላይ በማትኮር ከሁሉ በላይ በሰው ልጅ ላይ የሚደረገውን ጥናት በማጉላት በእያንዳንዱ የጥሪ ገጽታ ላይ አስተንትነዋል።

የሰው ልጅ በራሱ ጥሪ ነው

እርስ በርስ የመዛመድ ጠባይ ያለው የሰው ልጅ ሕይወት በራሱ ጥሪ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “እኔ አሁን በሕየት ያለሁት እና የምኖረውም እኔን ከፈጠረኝ፣ ከእኔ በላይ ካለው እውነታ፣ የግል ተልዕኮዬን በደስታ እና በኃላፊነት እንድቀበል ከተጠራሁበት እና በዙሪያዬ ካለው ዓለም ጋር ግንኙነት ባለው መልኩ ነው” ብለዋል።

"እያንዳንዳችን በጥሪያችን መሠረት እራሳችንን እንገልፃለን፣ ሌሎችን በማዳመጥ እና ምላሽ በመስጠት እራስን በመገንዘብ ማንነታችንን እና ስጦታችንን ለሌሎች የጋራ ጥቅም እንዲውል እናካፍላለን" ብለዋል።

ይህ መሠረታዊ የሰው ልጅ ጥናታዊ እውነት በዛሬው የባሕል አውድ ውስጥ ወደ ቀዳሚ የቁሳዊ ፍላጎት ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ እየታየበት ችላ ይባላል ብለዋል። ነገር ግን የሰው ልጆች ከዚህ በላይ እንደሆኑ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ወንድ እና ሴት የሰው ልጆች እግዚአብሔር በልባቸው ያስቀመጠውን ዘላለምነት እና የደስታ ምኞትን የተሸከሙ እና በተሰጣቸው ልዩ ጥሪ አማካይነት በተግባር ሊፈጽሟቸውም የተጠሩ ናቸው ብለዋል።

"በዓለም ውስጥ መኖራችን እንዲሁ የአጋጣሚ ሳይሆን ነገር ግን የፍቅር ንድፍ አካል በመሆኑ ከራሳችን ወጥተን ለራሳችን እና ለሌሎች የሚሆን ነገር ለማድረግ ተጋብዘናል" ብለው፥ የተጠራነውም ለደስታ፣ ለሙሉ ሕይወት፣ እግዚአብሔር ላቀደልን ታላቅ ነገር ነው" በማለት አስረድተዋል።

ሁላችንም በቤተ ክርስቲያን እና በኅብረተሰብ ውስጥ ተልዕኮ አለን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናል ቅዱስ ጆን ሄንሪ ኒውማን አስተንትኖዎችን እና ጸሎቶችን በማስታወስ፥ “ሁላችንም ተልዕኮ የተሰጠን ብቻ ሳንሆን እያንዳንዳችን በራሳችን ተልዕኮዎች ነን” ሲሉ ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በሲምፖዚዬሙ በቀረቡት ርዕሦች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን በደስታ ተቀብለው፥ ርዕሦቹ እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጥሪ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረጋቸው በተጨማሪ በዘመናችን ተግዳሮቶች፣ በሰው ልጅ ጥናት ላይ እየደረሰ ባለው ቀውስ እና በክርስቲያናዊ ጥሪዎች አስላጊነት ላይ ለማሰላሰል ያግዛሉ ብለዋል።

በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉ የልዩ ልዩ ጥሪዎች ማለትም የምዕመናን ጥሪዎችን ጨምሮ፣ የክኅነት አገልግሎት ጥሪዎች እና የምንኩስና ሕይወት ጥሪዎች ይበልጥ ውጤታማ እና ቀጣይነታቸውንም ማሳደግ፥ በሞት ጥላ ውስጥ በሚገኝ ዓለም ተስፋን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

"ይህን ተስፋ በማፍለቅ፣ እራስን ለእግዚአብሔር መንግሥት አገልግሎት ክፍት ማድረግ እና ወንድማማችነት የተሞላ ዓለምን ለመገንባት መዘጋጀት በዘመናችን ውስጥ ለእያንዳንዱ ሴት እና ወንድ የተሰጠ ተልዕኮ ነው" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈለግ ድፍረትን ማግኘት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፉ ሲምፖዚዬም ላይ ለተገኙት ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ፥ የሲምፖዚዬሙ ተሳታፊዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈለግ በሥራቸው ከሚደርስባቸው ሥጋት ወደ ኃላ እንዳይሉ ብርታትን ተመኝተው፥ ሕያው እምነት በሙዚየም ውስጥ የተቀመጠ ቅርስ እንዳልሆነ እና መንፈስ ቅዱስ ታማኝነትን እንደሚጠይቅ፥ ታማኝነትም ብዙ ጊዜ በአደጋ ውስጥ በመጓዝ ወደ አደጋ የሚመራ መሆኑን አስታውሰዋል።

ቢሆንም በድፍረት ወደ ፊት መጓዝ እንደሚገባ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲፈልጉ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችን አስረድተዋል።

 

02 March 2024, 16:33