ፈልግ

ቅዱስነታቸው በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ  ቅዱስነታቸው በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ከምዕመናን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto) ርዕሰ አንቀጽ

“ዘወትር ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር መሆን”

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተመረጡበትን 11ኛ ዓመት መታሰቢያን እና መላው ዓለም የምሕረት እና የሰላም መንገድን እንዲከተል በየጊዜው የሚያቀርቡትን ጥሪ በማስመልከት የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅ አንድሬያ ቶርኔሊ የሚከተለውን ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅቷል።

“ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተሰሚነትን ባላገኘበት፣ የፖለቲካ ተነሳሽነት እና ሰላምን ለማምጣት የሚችል አመራር በጠፋበት፣ ‘የግሪንሃውስ’ ጋዝ ልቀቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ለሁሉም የምድራችን ነዋሪዎች መሠረታዊ የጤና አጠባበቅን ለማረጋገጥ የሚያስችል ገንዘብ በእጥፍ መድባ ዓለም ለአስከፊ ጦርነት መሽቀዳደም በጀመረችበት በዚህ ወቅት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጦር መሣሪያ ድምጽ ተዘግቶ የሰላም ጎዳናን ለመጓዝ ድፍረት እንዲኖር በማለት ዘወትር የሚያቀርቡትን ብቸኛ ድምጻቸውን ዛሬም በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ሀገር በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ በሐማስ አሸባሪዎች የተፈፀመውን ጭካኔያዊ ግድያን እና እገታን ተከትሎ በጋዛ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ እልቂት እንዲቆም እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚያቀርቡትን የሰላም ጥሪ ዛሬ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

እንደዚሁም በክርስቲያን አውሮፓ እምብርት በተቀሰቀሰው አሰቃቂ ጦርነት ወራሪው የሩሲያ ጦር ኃይል በዩክሬን ላይ የሚፈጽመውን የቦምብ ጥቃት፣ ውድመት እና የሕይወት መጥፋት ቆሞ የጦር መሣሪያዎች ድምጽም ጸጥ እንዲል ዛሬም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

ሊነገር በማይችል ሁከት ግጭቶች በሚታዩባቸው እና የተረሱት ጦርነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በሄዱባቸው ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ሰላም እንዲወርድ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ሹመት አሥራ ሁለተኛውን ዓመት የተጀመረው በጨለማው ሰዓት ላይ ነው። የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ በመሪዎች ችሎታ ማነስ የተነሳ ውሳኔያቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ለመገምገም ባለመቻላቸው ለጦርነት አይቀሬነት እጃቸውን የሰጡ ይመስላል።

‘አሁን እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ የሚያይ እና ለሕዝቡ የሚያስብ ማለትም፥ ለመደራደር ድፍረት ያለው ጠንካራ ሰው ብቻ ነው። ምክንያቱም ‘ድርድር’ የሚለው ቃል ሃፍረት የማይታይበት ደፋር ቃል ነው’ በማለት ቅዱስነታቸው በግልጽ እና በተጨባጭ መንገድ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርብም ሆነ በሩቅ ባሉት ሰዎች ላይ የሚታዩ አለመግባባቶችን በመቃወም የሕይወት ቅድስናን በትኩረት ማዕከል አድርገው ለንጹሃን ተጎጂዎች ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ፥ የጦርነቶች ግብዝነት ካባ የሚለብሱ የተበላሹ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሞችን ማውገዛቸውን ቀጥለዋል።

እነዚህን የመጨረሻዎቹ አሥራ አንድ ዓመታት ታሪኮችን በፍጥነት መመልከት የሐዋርያው ጴጥሮስ ድምጽ ትንቢታዊ ጠቀሜታን ግልጽ ያደርገዋል። የማንቂያ ድምጽ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ሲሆን፥ ይህም ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በአንዳንድ ቦታዎች በጥቂቱ መጀመሩን በመናገር ነበር።

እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ 2015 ይፋ የሆነው እና ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን!’ የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት፥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ስደት፣ ጦርነቶች እና የሚገድል ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓት እርስ በርስ የተሳሰሩ ክስተቶች እንደሆኑ እና በዓለም አቀፋዊ ዕይታ ብቻ ሊፈቱ እንደሚችሉ አሳይቷል።

በሰዎች ወንድማማችነት ላይ ያተኮረው ‘ሁላችንም ወንድማማቾች ነን’ የሚለው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2020 የፋ የሆነው ታላቁ ሐዋርያዊ መልዕክት፥ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ አዲስ ዓለምን ለመገንባት መንገድን አመላክቷል። እንደገናም ሽብርተኝነትን፣ ጥላቻን እና ዓመፅን ለማካሄድ ሲሉ የእግዚአብሔርን ስም አላግባብ ለመጠቀም የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት ሰበብ አስወግዷል። በተጨማሪም ምሕረትን በማስመልከት በሚያቀርቧቸው ሐዋርያዊ አስተምህሮች ውስጥ ሚስዮናዊ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነትን የሚገልጽ ጠቅላላ ምልክት አለ።

የተወሰኑ መሠረቶች በሌሉት ዓለማዊው ማኅበረሰብ ውስጥ ምንም ዓይነት ነገር እንደ ተራ ነገር ሊወሰድ አይችልም። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ‘የወንጌል ደስታ’ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ ‘የውንጌል ስርጭት መሠረታዊ ሚናን እንደገና አግኝተናል’ በማለት ያስተምራሉ።

የመጀመሪያ የወንጌል ስርጭት ‘ሁሉም የወንጌል አገልግሎቶች እና ጥረቶች ማዕከል መሆን ያለበት በቤተ ክርስቲያን መታደስ ላይ ነው’ የሚል ነው። በእኛ በኩል ሃይማኖታዊ ግዴታ ሳይኖርበት፣ እውነት ጫና ሳይደረግበት ነፃነት፣ ደስታ፣ ማበረታቻ እና ሕያውነት እርስ በርሱ የሚስማማና ሚዛናዊ መሆን አለበት። ይህ ሁሉ በወንጌላዊው በኩል የመልዕክቱ ግልጽነትን የሚያጎለብቱ አንዳንድ አስተሳሰቦችን እነርሱም፥ የመቅረብ ችሎታ፣ ለውይይት ዝግጁነት፣ ትዕግሥት እና የመልካም አቀባበል ፍላጎት እንዲኖር ይጠይቃል። ስለዚህ የምሕረት ምስክርነት ከሥነ ምግባራዊ እና ከሃይማኖታዊ ግዴታ በፊት የእግዚአብሔር የማዳን ፍቅር መሠረታዊ አካልን ይወክላል።

በሌላ አነጋገር የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር 2010 ዓ. ም. በግልጽ እንዳስተዋሉት፥ ከክርስቲያናዊው እውነታ ጋር ገና ያልተገናኙ፣ በክልከላዎች ላይ የሚደረግ ጽንፈኝነት፣ የደንቦች እና የሞራል ግዴታዎች ማረጋገጫዎች በኃጢያት ዝርዝሮች፣ በኩነኔዎች ወይም ባለፈው እሴት ላይ ናፍቆትን ማሳየታቸው ብዙም አይደነቁም።

መልካም አቀባበል ማድረግን፣ መቀራረብን፣ ርኅራኄን፣ አብሮነትን እና መደማመጥን በሚችል የክርስቲያን ማኅበረሰብን ሺህ ውስንነቶች እና ውድቀቶች ቢያጋጠሙት አሁንም ወደ ምሕረት የመመለስ ፍላጎት አለ።

በዚህ ዓይን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምልክቶች መመልከት ከተቻለ፥ አንድ ሰው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በኢየሱስ ክርስቶስ ምልክቶች የቀሰቀሱትን ተመሳሳይ እና አሳፋሪ የቁጣ ምላሾችን እንኳን በጥልቅ የወንጌል አገልግሎት እና የሚስዮናዊነት ኃይል ሊገነዘባቸው ይችላል” በማለት ርዕሠ አንቀጹ ይደመድማል።

ትርጉም በዮሐንስ መኰንን
 

14 March 2024, 19:03