ፈልግ

በአርጄንቲና በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር በአርጄንቲና በዕፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በአርጄንቲና ጥቃት ለተፈጸመባቸው ዜጎች ያላቸውን ቅርበት ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አርጄንቲና ውስጥ ሮዛሪዮ በተባለ አካባቢ በሚኖሩት ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የወንጀል ጥቃት በማስታወስ የቪድዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው አርጄንቲና ውስጥ ለሚገኝ የሮዛሪዮ ማኅበረሰብ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፥ ጥቃቱ ለተፈጸመባቸው ዜጎች ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ. ም. በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፥ በአርጀንቲና ሮዛሪዮ ከተማ ውስጥ ከአሥር ዓመታት በላይ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከአደንዛዥ እፅ ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው ጥቃት እየጨመረ መሄዱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በዚያ አካባቢ የዓመፅ ማዕበል የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2013 ዓ. ም. ጀምሮ ሲሆን፥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ኮኬይን እና ሌሎች ዕጾች ወደ አውሮፓ ወይም ወደ አፍሪካ ከመላካቸው በፊት የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ወደሆነችው ሮዛሪዮ ደርሶ በፓራና ወንዝ ወደብ በኩል እንደሚላኩ ታውቋል።

የማኅበረሰብ አውታረ መረቦችን ማጠናከር

ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በህግ አስከባሪዎች በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ፈጣን ባይሆኑም በቂ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። “ማኅበረሰቡን ማጠናከር ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ማንም በጎ ፈቃድ ያለው ሰው የሮዛሪዮ ከተማ ሁሉም ሰው እንደ ወንድም በስምምነት የሚኖርባት ሥፍራ መሆኑን የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል” ብለዋል።

የሙስና መስፋፋት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአካባቢው የፖለቲካ እና የሕግ አስከባሪ አካላት መስፋፋት ሙስና እና አንዳንድ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ተቋማት ከዕፅ አዘዋዋሪዎች ጋር በመመሳጠር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ስለዚህም በእውነት ለጋራ ጥቅም የቆመ የተሻለ ፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የጋራ መግባባት እና ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።

“የጋራ ጥቅምን እስካልፈለገ ድረስ ፖለቲካን እንደ ከፍተኛ ጥሪ እና ከበጎ አድራጎት ዓይነቶች አንዱ ነው” ብሎ ማሰብ አይቻልም” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ለጋራ ጥቅም በመሥራት ሕይወታቸው ለአደጋ ለሚጋለጡ ሰዎች እውቅና በመስጠት፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር የተያያዙ ሙስና እና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ገለልተኛ የፍትህ አካል መኖር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተጨማሪም የግሉ ሴክተር በተለይም ሥራ ፈጣሪዎች የሚጫወቱትን ሚና በማጉላት ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር ተባብሮ እንዳይሠራ በማኅበራዊ ተሳትፎ እና በሥነ ምግባር የታነፀ የንግድ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወጣቶች የተሻለ የወደፊት ጊዜ መስጠት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ሮዛሪዮን የተሻለ የመኖሪያ ቦታ ለማድረግ ሁሉም ዘርፎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ዜጎች የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ለአደጋ የተጋለጡ ወጣቶች፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት፥ ሁላችንም መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊ እና የሃይማኖት ተቋማት የተሻለ ለመሥራት አንድ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን አስተዋጾ

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ ቤተ ክርስቲያን እንደ እናት እና እንደ ሳምራዊት” በአመጽ ከተጎዱት ቤተሰቦች ጋር በመሆን እና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞችን እና በከፍተኛ ተጋላጭነት ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች መደገፍ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። “በዚህ ጊዜ ፍቅር እና ልግስና ስጋት ውስጥ ለሚገኝ ማኅበረሰብ የወንጌል ምስክርነት መንገዶች ይሆናሉ” ሲሉ መልዕክታቸውን በማጠቃለል፥ ለከተማዋ ደህንነት የሮዛሪዮ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን ለምነዋል።

27 March 2024, 16:44