ፈልግ

2024.02.08 Partecipanti alla Plenaria del Dicastero per il Culto Divino e la Disciplina dei Sacramenti

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡ ሥርዓተ አምልኮ ለሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆን አለበት ማለታቸው ተገለጸ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን የቅድስት መንበር መለኮታዊ ሥርዓተ አምልኮን እና ምስጢራት በሥርዓቱ መሰረት መፈጸማቸውን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ያለ የአምልኮ ሥርዓት ማሻሻያ እራሷ መታደስ እንደማትችል አስታውሰው ይህም ለሁሉም የእግዚአብሔር ሰዎች መሆን አለበት በማለት መናገራቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ዕለት ጥር 8/2016 ዓ.ም ላይ በቫቲካን የቅድስት መንበር መለኮታዊ ሥርዓተ አምልኮን እና ምስጢራት በሥርዓቱ መሰረት መፈጸማቸውን የሚመለከተው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አባላት ጋር መገናኘታቸው ተገልጿል።

በላቲን ቋንቋ “sacrosanctum Concilium” (ቅዱስ ጉባሄ) ይህ ሐዋርያዊ ቀኖና ስለ ቅዱስ ሥርዓተ አምልኮ የምያወሳ ሲሆን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ካወጣቸው ከአራቱ የሥርዓተ አምልኮ ቀኖናዎች ውስጥ አንዱ ነው። በ2158 የድጋፍ ድምፅ እና በ19 ተቃውሞ የፀደቀ ሲሆን እ.አ.አ በታኅሣሥ 4 ቀን 1963 ዓ.ም በወቅቱ በነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት  ጳውሎስ 6ኛ የታወጀ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በግንኙነቱ ወቅት ያደረጉትን ንግግር የጀመሩት “sacrosanctum Concilium” (ቅዱስ ጉባሄ) የተሰኘው የሁለተኛ የቫቲካን ጉባሄ ቀኖናዊ ሰነድ  መፅሐፍ ከታወጀ ከስልሳ ዓመታት በኋላም ቢሆን፣ አሁንም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በውስጡ የያዘው "ትክክለኛው ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን በመሠረታዊ ገጽታዎች ውስጥ ለማሻሻል፣ የምእመናን ክርስቲያናዊ ሕይወት በየቀኑ እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ፣ የጊዜያችን ፍላጎቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲለወጡ የሚያግዙ ተቋማትን ማስተካከል፣ በክርስቶስ ላሉት አማኞች ሁሉ አንድነት የሚያበረክተውን ማበረታታት፣ ሁሉንም ወደ ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ለመጥራት የሚያገለግለውን ማበረታታት” የሚመለከቱ ጠቃሚ እና ፍሬያማ ሰነዶች የተካተቱበት መሆኑን ቅዱስነታቸው አብራርተዋል።

ይህ ጥልቅ መንፈሳዊ፣ ሐዋርያዊ እንክብካቤ፣ ቤተ ክርስቲያን እና ሚስዮናውያን የመታደስ ሥራ ነው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ የጉባኤው አባቶች “ያለ ሥርዓተ አምልኮተ እድሳት ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ የላትም” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል የቤተክርስትያን ተሀድሶ የሚወሰነው ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ ባላት ፍቅር ልክ እንደ "የትዳር ጓደኛ ታማኝነት" ሙሉ በሙሉ ከእርሱ ጋር እስከመስማማት ድረስ ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያን እንደ ሴት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሴቶችን ሚና ሲናገሩ ቤተክርስቲያን ራሷ ሴት የመሆኗን አስፈላጊነት አሳስበዋል። "ለዛም ነው እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን ተሀድሶ ሁሌም የትዳር ጓደኛ ታማኝነት ጉዳይ ነው ያልኩት፣ ምክንያቱም እሷ [ቤተክርስቲያን] ሴት ናት" ሲሉ ተናግሯል።

የሥርዓተ አምልኮው ተሐድሶ ዓላማ - በቤተክርስቲያኒቱ መታደስ ሰፊ ማዕቀፍ ውስጥ - በትክክል "የምእመናንን የሕነጻ ትምህርት ለማምጣት እና ያንን የሥርዓተ አምልኮ ታድሶ ዋና ጉባኤ እና ምንጭ የሆነውን የእረኝነት ተግባር ለማስተዋወቅ ነው" ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በቅድስት መነበር ሥር የሚተዳደሩ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል ባለው ሲኖዶሳዊ ትብብር መንፈስ የተሾሙ አገልጋዮች የሥርዓተ አምልኮ ምስረታ ጥያቄ ከባህልና ትምህርት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና ከቅዱሳን ሕይወት ተቋማት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ እንዲስተናገድ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል። እናም የሐዋርያዊ ሕይወት ማኅበራት "እያንዳንዱ የራሱን ልዩ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት" ጋብዘዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የተቀቡ አገልጋዮች ቀጣይነት ያለው የሕነጻ ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የሥርዓተ መለኮት ጥናት ሥርዓተ-ትምህርት እና በዘረዐ ክህነት ተማሪዎች የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ፣ ሥርዓተ አምልኮ ትምህርት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ሁሉንም የእግዚአብሔርን ሰዎች አስቡ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ለአገልጋዮች አዲስ የሕመጻ ትምህርቶች መንገዶችን ስናዘጋጅ፣ “በተመሳሳይ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የታሰቡትን ማሰብ አለብን” ሲሉ አሳስበዋል። የመጀመርያዎቹ ተጨባጭ የሥርዓተ አምልኮ እድሎች እሑድ እና በቅዳሴ ዓመቱ የሚከበሩ የበዓላት ቀናት መሆናቸውን ቅዱስ አባታችን ገልጸዋል።

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተግባራቸው "ትልቅ እና የሚያምር" መሆኑን አሳስበዋል። ለዚህም "በጣም አመሰግናለሁ" እና "ከልቤ እባርካችዋለሁ" ካሉ በኋላ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

09 February 2024, 16:36