ፈልግ

የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9”  የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9”   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባን በመምራት ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት አዲሱ የካርዲናሎች “C9” ስብሰባ ከሰኞ ጥር 27/2016 ጀምሮ በቫቲካን እየተካሄደ መሆኑ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቆ፥ “C-9” እየተባለ የሚጠራው የካርዲናሎች ምክር ቤት አባላት ቡድን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በስብሰባው መገናኘቱን አስታውቋል። የመጨረሻው የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቅድስት ማርታ የብጹዓን ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ከኅዳር 24-25/2016 ዓ. ም. መካሄዱ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፈው ኅዳር ወር የተካሄደው የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ ዋና ጭብጥ "የሴቶች ሚና በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ" የሚል እንደ ነበር ሲታወስ፥ በስብሰባው ንግግር ያደረጉትን መምህራን እና የነገረ መለኮት ሊቃውንት የሆኑትን እህት ሊንዳ ፖቸርን፣ እህት ሉቺያ ቫንቲኒን እና አባ ሉቃስ ካስቲሊዮንን ምክር ቤቱ አመስግኖአቸዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ እንደገለጸው፥ በወቅቱ ከሁሉም በላይ በእያንዳንዱ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአንስታይ ገጽታን ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ እና ይህም ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያበርክቱትን የማይተካ የማሰላሰል እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን በድጋሚ ለመገንዘብ ማስቻሉ ተነግሯል።

የወቅቱ ስብሰባ ዋና ትኩረት በዩክሬን እና በቅድስት ሀገር በተፈጠሩ ግጭቶች፣ በዱባይ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ “COP28” ተግባርን እና እንዲሁም ለአካለ መጠን ባልደረሱ ህጻናት እና ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ነበር ይታወሳል።

ለሁለት ቀናት የተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ፥ በጥቅምት ወር በተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ በተነሱት ጉዳዮች እና በካቶሊክ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ በሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ውስጥ “ወንጌልን ስበኩ” የሚለው የሐዋርያዊ ደንብ አተገባበር ላይ ለመወያየት ዕድል የሰጠ እንደ ነበር ይታወሳል።

አዲሱ ከፍተኛ የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናሎች ምክር ቤትን የካቲት 28/2015 ዓ. ም. በአዲስ መልክ ማቋቋማቸው የሚታወስ ሲሆን፥ አባላቱም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የቫቲካን ከተማ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝደንት እና የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ርዕሠ መስተዳድር ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ቬርጌዝ አልዛጋ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በሕንድ የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ፣ በሰሜን አሜሪካ የቦስተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴያን ፓትሪክ ኦማሌይ፣ በስፔን የባርሴሎና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሁዋን ሆሴ ኦሜላ ኦሜላ፣ በካናዳ የኪቤክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጄራልድ ላክሮክስ፣ በአውሮፓ የሉክሰምበርግ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ በብራዚል የሳን ሳልቫዶር ደ ባሂያ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ እንደሆኑ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በጣሊያን የክሬሲማ ጳጳስ ሞንሲኞር ማርኮ ሜሊኖ እንደሆኑ ይታወቃል። ይህ አዲሱ ምክር ቤት “C9” የመጀመሪያ ስብሰባውን ሰኞ ሚያዝያ 16/2015 ዓ. ም. ማካሄዱ ይታወሳል።

የካርዲናሎች ምክር ቤት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ መስከረም 18/2006 ዓ. ም. በዓለማቀፉ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ እንዲያግዟቸው እና በሮም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙትን የከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችን ለማሻሻል የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድ ምክር ቤቱን ማቋቋማቸው ሲታወስ፥ በኋላም “ወንጌልን ስበኩ” በሚል ርዕሥ በመጋቢት 10/2014 ዓ. ም. የታተመውን አዲሱን ሐዋርያዊ ደንብ መመሪያው በማድረግ የመጀመሪያውን የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9” ስብሰባን መስከረም 21/2006 ዓ. ም. ማካሄዱ ይታወሳል።

 

06 February 2024, 16:04