ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በሚያፈቅረን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ለሌሎች ለመመስከር እንውጣ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት በኅብረት ለማድረስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች ቃለ ምዕዳንን አሰምተዋል። ከማር. 1: 29-39 ተወስዶ በተነበበው በዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ዘወትር በሚያፈቅረን እግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ለመመስከር መውጣት እንዳለብን አደራ ብለዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. ያሰሙትን ቃለ ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶች፣ እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ ባቀረብነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ በአገልግሎት ላይ መሆኑን ያሳየናል። በእርግጥም ኢየሱስ ስብከቱን እንደጨረሰ ከምኩራብ ከወጣ በኋላ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ቤት ሄዶ አማቱን ፈውሷል። በመሸም ጊዜም ወደ ከተማይቱ በሮች በመሄድ በዚያም ብዙ ድውያንንና በሽተኞችን አግኝቶ ፈውሷቸዋል። በማለዳም ተነስቶ ለጸሎት ወጥ ወዳለ ሥፍራ ሄደ። እንደገናም ወደ ገሊላ ማዶ ሄደ (ማር. 1፡29-39)። ስለ እግዚአብሔር አብ ጠቃሚ ነገር የሚነግረንን እና በእምነታችን እንድናሰላስል የሚያደርገንን፥ ቀጣይነት ያለውን የኢየሱስ ክርስቶስ እንቅስቃሴ እንመልከት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት ወደ ቆሰለው የሰው ልጅ ዘንድ በመሄድ እግዚአብሔር አብን ያሳየናል። ምናልባት በውስጣችን ከእምነት የራቅን፣ ለእግዚአብሔርም ደንታ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። በተቃራኒው ቅዱስ ወንጌል እንደሚናገረን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ካስተማረ በኋላ የሰበከው ቃል ሰዎችን እንዲደርሳችው፥ እንዲዳስሳቸው እና እንዲፈውሳቸው ለማድረግ መውጣቱን እንመለከታለን። ይህን በማድረጉ እግዚአብሔር ከእኛ የራቀ ሳይሆን ነገር ግን ከላይ ሆኖ የሚናገረን አምላክ እንደሆነ ገልጦልናል። እርሱ በፍቅር የተሞላ አባት፥ ራሱን ወደ እኛ የሚያቀርብ፣ የሚጎበኘን፣ የሚያድነን እና ነጻ የሚያወጣን፣ ከማንኛውም የአካል እና የመንፈስ ህመም የሚፈውሰን አባት ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ዘወትር ቅርብ ነው። እርሱ ለእኛ ያለን አመለካከት በሦስት ቃላት ሊገለጽ ይችላል። ቅርብ፣ ርኅሩኅ እና ለጋስ በሚሉት ቃላት መግለጽ እንችላለን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሊሆን፣ ርኅራኄውን ሊገልጥልን እና ይቅር ሊለን ቀረበን። እርሱ ለእኛ ያለንን የመቅረብ፣ የርኅራሄ እና የለጋስነት አመለካከት መርሳት የለብንም።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሳያቋርጥ ከቦታ ቦታ የሚያደርገው ጉዞ ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል። እግዚአብሔር የምህረት አባት እንደሆነ እናውቃለን? ወይንስ ለእኛ ግድ የሌለው የሩቅ አምላክ እንደሆነ እንመሰክራለን? በውስጣችን ያለው እምነት የማያቋርጥ ጉዞን እንድንጓዝ ያደርገናል ወይንስ ተጽናንተን እንድንረጋጋ ያደርገናል? ጸሎታችን የውስጥ ሰላም ለማግኘት ነው ወይንስ የምንሰማው እና የምንሰብከው ቃል የእግዚአብሔርን አጽናኝነት በመመስከር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛም ወደ ሌሎች እንድንሄድ ያደርገናል? እነዚህን ጥያቄዎች እራሳችንን ብንጠይቅ መልካም ነው።

እንግዲያውስ የኢየሱስ ክርስቶስን ጉዞ በመመልከት ማከናወን ያለብን የመጀመሪያው መንፈሳዊ ተግባራችን በቅዱስ ቃሉ ራሱን በገለጠልን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት በዕለት በመለወጥ፥ እግዚአብሔር አብ የፍቅር እና የርህራሄ አባት መሆኑን እናስተውል። እግዚአብሔር አብ ለእኛ ቅርባችን፣ ርኅሩህ እና ለጋስ አምላክ ነው። የእርሱን እውነተኛ መልክ ስናውቅ እምነታችን ይጎለብታል። ከእንግዲህ ወዲያ በቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት ዕቃዎች ማስቀመጫ ክፍሎች ወይም የቃል ክርስቲያኖች ብቻ ሆነን አንቀርም። ይልቁንም የእግዚአብሔርን ተስፋ እና ፈውስ አብሳሪዎች እንድንሆን የተጠራን መሆናችን ይሰማናል።

የእግዚአብሔርን ቅርብነት፣ ርኅራሄውን እና ለጋስነቱን የምንመሰክር ሰዎች እንድንሆን በክርስትና ጉዞአችን ከእኛ ጋር ያለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታግዘን።” 

 

05 February 2024, 16:14