ፈልግ

እስራኤል ጥቃት የፈጸመችባቸው የራፋ ነዋሪዎች እስራኤል ጥቃት የፈጸመችባቸው የራፋ ነዋሪዎች 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሰላምን ማስፈን የሰው ልጅ ሁሉ ኃላፊነት መሆኑን ገለጹ

እሑድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. ሳምንታዊ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖአቸውን ከተከታተሉ በኋላ የእኩለ ቀኑን የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበው ለመመለስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ንግግራቸው በጦርነት ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን በድጋሚ በጸሎታቸው በማስታወስ፥ ሰላምን ማስፈን የመላው የሰው ልጅ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዚህ አጋጣሚም አዲስ ዓመታቸውን ለማክበር ዝግጅት ላይ ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መልካምን ተመኝተው ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። ቅዱስነታቸው እንደዚሁም በቅርቡ የሚከበር ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን እና የጸረ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን መኖሩን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ እሁድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. ካቀረቡት የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባሰሙት ንግግር፥ ትኩረታቸውን በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ጦርነቶች በሞቱት እና በሚሰቃዩት ሰዎች ላይ በማድረግ መላው የሰው ልጅ ሰላምን በመገንባት ረገድ ሃላፊነት እንዳለው አስረድተዋል። ለሕዝቦች በሙሉ የእግዚአብሔር ቡራኬ እንዲደርሳቸው ጸሎት አቅርበው፥ ከምን ጊዜውም በላይ በርካታ የዓለማችን ክፍሎች በአደጋ ላይ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ምዕመናን ለሰላም እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል። ይህም የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የመላው የሰው ልጅ ኃላፊነት እንደሆነ እና “ሁላችንም ሰላምን በርኅራኄ እና በድፍረት መንፈስ ለመገንባት እንተባበር!” ብለዋል። “በተለይ በዩክሬን፣ በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ በጦርነት ለሚሰቃዩ ሰዎች የምናቀርበውን ጸሎት እንቀጥል” በማለት ተማጽነዋል።

በዩክሬን ጉዳት የደረሰበት የካርኪቭ ክልል ቤተ ክርስቲያን
በዩክሬን ጉዳት የደረሰበት የካርኪቭ ክልል ቤተ ክርስቲያን

የአዲስ ዓመትመልካም ምኞት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትኩረታቸውን በምሥራቅ እስያ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ በማድረግ፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች የጨረቃን አዲስ ዓመት ቅዳሜ የካቲት 2 እንደሚያከብሩ ገልጸዋል። በዓሉ እርስ በርስ መተሳሰብን እና መዋደድን የሚለማመዱበት አጋጣሚ እንደሚሆን ያላቸው ተስፋ በመግለጽ የአክብሮት ሰላምታቸውን ልከዋል። እንዲሁም ለእያንዳንዱ ሰው የማይገሰስ ክብርን በመስጠት አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለመፍጠር አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።

ቻይና ውስጥ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ
ቻይና ውስጥ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ

ጣሊያን ውስጥ የሚከበር ብሔራዊ ሕይወት ቀን

ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ የካቲት 26 ጣሊያን ውስጥ የሕይወት ቀን የሚከበርበት ዕለት እንደሆነ በማስታወስ ለዘንድሮ በዓል የተመረጠው መሪ ርዕሥ፥ “የሕይወት ኃይል ይገርመናል!” የሚል እንደሆነ አስታውሰዋል። “ርዕዮተ ዓለማዊ ራዕዮች እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት፣ አቅመ ደካሞች እንኳ ቢሆን ትልቅ ዋጋ እንዳለው እና ለሌሎችም ማበርከት እንደሚችል በድጋሚ እንድናውቅ ያግዛሉ” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን እና ስለ ጸረ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ያለው ግንዛቤ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጪውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን ለማክበር እና በጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ግንዛቤን ለማግኘት ከተለያዩ አገራት ወደ ሮም ለመጡ ወጣቶች ልዩ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በጥር 30 የሚከበረው ዓለም አቀፍ ቀን በባርነት ተገዝታ የነበረችው ሱዳናዊት ቅድስት ጆሴፊን ባሂታ ዓመታዊ በዓል ዕለት እንደሆነም አስታውሰዋል። “በዚህ ጊዜም ቢሆን ብዙ ወንድሞችና እህቶች በውሸት ቃል ተታልለው ለብዝበዛ እና ለበደል ይጋለጣሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “አስደማሚውን ዓለም አቀፍ የሰው ልጅ ዝውውርን ለመዋጋት ሁላችንም አንድ ላይ እንሁን” ብለዋል።

በባርነት ተይዛ የነበረችው ሱዳናዊት ቅድስት ጆሴፊን ባሂታ
በባርነት ተይዛ የነበረችው ሱዳናዊት ቅድስት ጆሴፊን ባሂታ

በማዕከላዊ ቺሊ የተከሰተው የሰደድ እሳት ቃጠሎ

በማዕከላዊ ቺሊ በተከሰተው የሰደድ እሳት የተጎዱትን በጸሎታቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በዚህች አገር በደረሰው ከባድ የእሳት አደጋ የሞቱትን እና የተጎዱን ሰዎች ምዕመናን በጸሎታቸው እንዲያስታውሳቸው አደራ ብለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባት ቺሊ ውስጥ በተቀሰቀሰ የደን ቃጠሎ በትንሹ 51 ሰዎች ሞታቸው ተነግሯል። የአገሪቱ ባለሥልጣናቱ የአደጋውን ክብደት ግምት ውስጥ በማስገባት የተጎጂዎች ቁጥር በመጪዎቹ ሰዓታት ውስጥ ሊጨምር እንደሚችል ሰግተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚመለከተው የሰዓት እላፊ ገደብ የተጣለባቸውን ማርጋ ማርጋ እና ቫልፓራይሶ አውራጃዎች እንደሆነ ታውቋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ 92 የሚጠጉ የእሳት ቃጠሎዎች የተከሰቱ ሲሆን እስካሁን በ43,000 ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል።

የእሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው የቺሊ ሕዝቦች
የእሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰባቸው የቺሊ ሕዝቦች

በሰላም የጉዞ ላይ የሚገኙ የተስፋ ነጋዲያን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሑድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ፥ “በሰላም ጉዞ ላይ የሚገኙ የተስፋ ነጋዲያን” በሚል ርዕሥ በቅድስት መንበር የገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም የሐዋርያዊ ሕይወት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀውን ስብሰባ ለመካፈል ከ60 በላይ አገሮራት ለመጡት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው ፍቅራቸውንም ገልጸውላቸዋል።

05 February 2024, 16:24