ፈልግ

2024.01.03 Foto intervista Papa san Francesco

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በጦርነት ዓለም ውስጥ የሰላም ድልድዮችን ገንቡ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአሲዚ በሚገኘው የቅዱስ ፍራንቸስኮስ ገዳም ለሚታተመው ወርሃዊ መጽሔት ቃለ ምልልስ የሰጡ ሲሆን “የዕርቅ እና የይቅርታ ሐዋርያት” እንዲሆኑ በተለይም ደግሞ በአሁኑ ውጥንቅጥ በበዛበት ዓለም ውስጥ የሰላም መሳርያ እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

“በጣም ብዙ ጭካኔ አለ፣ ለዚህም ነው የሰላም ድልድዮች እንዲገነቡ የምጠይቀው!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን የተናገሩት ደግሞ በአዚዚ በሚገኘው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ገዳም አማካይነት ለሚታተመው ሳን ፍራንችስኮ ፓትሮኖ ዲ ኢታሊያ (የጣሊያን ጠባቂ የሆንክ ቅዱስ ፍራንችስኮስ) ለተባለው ወርሃዊ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ነበር የተናገሩት።

በጥር ወር እትም ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በድጋሚ ድልድይ በመገንባት እና ለተቸገሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እጃችንን በመዘርጋት የሰላም መሳሪያ እንድንሆን ጠይቀዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት ዓለም በሁሉም ቦታ ጦርነት ማድረጉን አላቆመም፣ ፍልስጤም እና ዩክሬን ለእኛ ቅርብ ስለሆኑ በደንብ እናያቸዋለን። አሁን ያለንበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነና በፖለቲካ ጉዳዮች ብዙ ሰዎች በእስር ቤት እንደሚገኙም ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገለጹ ሲሆን እንዲህ ያለ ጭካኔ ሲደርስብን የሰላም ድልድዮች መገንባት እንደሚያስፈልገን አበክረው ተናግረዋል። "ድልድዮችን ይገንቡ" ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ማን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር - “ልዩ ቅዱስ፣ ክርስቶስን በተለየ መንገድ የመሰለ” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። እርሱ የትሕትና እና የቸርነት ቅዱስ ነው፣ ራሱን ለሁሉም ሰው ሲያቀርብ ታጋሽ ነው፣ ከማንም ምንም አይጠይቅም። ይህም ቅዱስ ፍራንችስኮስ ጌታን ለመምሰል የመረጠው እንዴት እንደሆነ እና እስከ መጨረሻው እንዳደረገው ጳጳሱ አስረድተዋል።

በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን መንፈስ ቅዱስ በፍራንችስኮስ በኩል ለቤተ ክርስቲያን ሊሰጥ የሚፈልገውን ሥጦታ፡ በጎነትን አጉልተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልካምነት ማለት የጌታ ምስክር መሆን እና ይቅርታ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

 

05 January 2024, 12:47