ፈልግ

2024.01.03 Udienza Generale

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጦርነት እብደት ነው በማለት በግጭቶች የተጎዱትን ሰዎች ያስታውሳሉ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፍልስጤም፣ በእስራኤል፣ በዩክሬን እና በስደት ላይ ለነበሩት የሮሂንጊያዎች በትጥቅ ግጭት ሰለባ ለሆኑት ጸሎት ሲያደርጉ በጃፓን የመሬት መንቀጥቀጥ እና የአውሮፕላን ግጭት ሰለባ ለሆኑት አጋርነታቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለማችን ሰላም እና በጦርነት ሰለባዎች እፎይታ እንዲሰጣቸው ጸለዩ፣ "ጦርነት እብደት ነው" እና ሁልጊዜም ለሰው ልጅ "ሽንፈት" መሆኑን አስታውሰዋል።

ለጦርነት ሰለባዎች ጸሎት አደረጉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ በቅርቡ በተጀመረው 2024 ዓ.ም ላይ ባደረጉት የመጀመሪያው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ለምእመናን ንግግር ባደረጉበት ወቅት በፍልስጤም እና በእስራኤል ስላለው አደጋ እና በዩክሬን ስላለው ጦርነት ጸሎቶት እንዲደረግ ጠይቀዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን በተለያዩ የአለም ክፍሎች በጦርነት የተጎዱትን ወገኖቻችንን ማስታወስ አለብን በማለት በተለይ በስደት ላይ ያሉትን የሮሂንጊያ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዳንረሳ ጠይቀዋል።

ልባችንን እንክፈት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከፖላንድ ለመጡ ምዕመናን ንግግር ባደረጉበት ወቅት ምእመናን በጦርነትና በድህነት ምክንያት በጉዞ ላይ ያሉትን ሰዎች እንዲያስታውሱ ጋብዘው እግዚአብሔር “ለድሆች፣ ለስደተኞችና ለጦርነት ሰለባዎች ፍላጎት የሚጠነቀቅ ልብ ይስጠን ዘንድ ጸለዩ።

"በወላዲተ አምላክ በማርያም አማላጅነት ጌታን የሰላም ስጦታ እንዲሰጠን እለምናለሁ እና ከልቤ እባርካችሃለሁ! ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ማነኛውም ዓይነት ጦርነት እና ግጭት ይወገድ ዘንድ ተማጽነዋል።

ለጃፓን የመሬት መንቀጥቀጥ ተጎጂዎች እርዳታ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በኋላ በጃፓን በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ለተጎዱ ሰዎች ጸሎት አቅርበዋል ፣በቶኪዮ በአውሮፕላን ግጭት የነፍስ አድን ሠራተኞችን አስታውሰዋል ።

በአዲሱ አመት የመሬት መንቀጥቀጥ የሟቾች ቁጥር ወደ 64 ከፍ ብሏል፣ ነገር ግን ሁኔታው በጣም ያልተረጋጋ ነው። የጃፓን የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አደጋን ተከትሎ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል። የመሬት መንቀጥቀጡ በአዲስ አመት እለት በኖቶ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ከፍተኛ ውድመት በማድረስ በመሬት ንዝረት መሳርያ አቆጣጠር 7.6 በሆነ መጠን መከሰቱ ይገመታል።

ማክሰኞ፣ የጃፓን አየር መንገድ ኤርባስ የመሬት መንቀጥቀጥ ለተከሰቱ አካባቢዎች የድንገተኛ አደጋ እቃዎችን ከጫነ የባህር ዳርቻ ጥበቃ አውሮፕላን ጋር በመጋጨቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት የባህር ዳርቻ ጥበቃ አባላት መካከል አራቱን ገድሏል። ሁሉም 379 የጃፓን አየር መንገድ ተሳፋሪዎች እና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በፍጥነት ከእሳት አደጋ በመውጣት በፍጥነት በማምለጥ በህይወት ተርፈዋል።

የቶኪዮው ሊቀ ጳጳስ ታርሲሲየስ ኢሳኦ ኪኩቺ በመሬት መንቀጥቀጡ ለተጎዱት የአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ቤተክርስቲያኗ ከካሪታስ ጃፓን ጋር በጋራ የሚሰራ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ድጋፍ ሰጪ ቡድንን አቋቁማለች።

04 January 2024, 09:20