ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን የካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጣሊያን ካቶሊክ ጋዜጠኞች የሰውን ልጅ ማስቀደም እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሚመራ የካቶሊክ ቲቪ እና ሬዲዮ ስርጭት አውታር ጋዜጠኞችን ሰኞ ጥር 20/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለዋል። ቅዱነታቸው ለጋዜጠኞቹ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያኗ ለችግር ለተጋለጡት እና በማኅበረሰቡ ለተገለሉ ወገኖች ዘወትር ቅርብ መሆኗን መመስከር እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በመገናኛ እና መረጃው ዓለም እየታየ በመጣው የቴክኖሎጂ ዕድገት የካቶሊክ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ወደ ኅብረተሰቡ ዘንድ በመሄድ የተስፋ ብርሃን የማምጣት መሠረታዊ ተልዕኳቸውን መቼም ቢሆን መዘንጋት የለባቸውም ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክት ለጋዜጠኞቹ ያስተላለፉት 25ኛውን የምስረታ በዓላቸውን ለሚያከብሩ የቲቪ2000 እና የ inBlu2000 ለተባሉ በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለሚመሩ የካቶሊክ ብዙሃን መገናኛዎች ሥራ አስኪያጆች እና ሠራተኞች ነው። የሰዎች ግንኙነት እና መረጃ ልውውጥ ሁል ጊዜ በሰው ዘንድ ይገኛል ብለው፥ ታዳሚዎችን በሥራቸው መካከል የሚያግዙ ሦስት ቁልፍ ቃላትን አጉልተው ተናግረዋል።

ሃይልን ያተኮረ የሚዲያ አመክንዮ እና ቅርበት

የመጀመሪያው ቃል በማኅበራዊ ሚዲያ እና በተከታዮቹ መካከል ያለው "መቀራረብ" ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ጋዜጠኞች በቴሌቭዥን ወይም በራዲዮ አማካይነት በየቀኑ ወደ ብዙ ሰዎች እንደሚቀርቡ ገልጸው፥ ደንበኞች መረጃን በማግኘት ከጓደኞቻቸው ጋር አስደሳች ጊዜ የሚያሳልፉ ወይም አዳዲስ እውነታዎችን፣ ልምዶችን፣ ተሞክሮዎችን እና ቦታዎችን ያገኛሉ ብለዋል።

ስለዚህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጣሊያ ካቶሊክ መገናኛ ባለሞያዎች በሰዎች መካከል ትስስር መፍጠርን በመቀጠል ስለ ማኅበረሰባቸው ውበት እና መልካም ነገር እንዲመሰክሩ እና በኅብረተሰቡ የተገፉትን ግንባር ቀደም አድርገው እንዲያሳዩ፣ በማን አለብኝ አስተሳሰብ የሐሰት ዜናን የሚሰራጩ ኃይሎችን ቸል ማለት እንደሚገባ አሳስበው፥ በተለይም በማኅበረሰቡ የተገለሉትን፣ ድሆችን እና በብቸኝነት ሕይወት የሚሰቃዩትን ሰዎች በፍጹም መዘንጋት እንደሌለባቸው አደራ ብለዋል። መቀራረብ ከእግዚአብሔር ባሕርያት መካከል አንዱ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ እግዚአብሔርን እንድናይ የሚያደርጉን ሦስት ነገሮች እንዳሉ፥ እነርሱም እንደ እርሱ ሰዎችን መቅረብ፣ ለሰዎች መራራት እና ዘወትር ይቅር ባይ መሆን እንደሆኑ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጠቀሱት ሁለተኛው ቁልፍ ቃል "ልብ" ሲሆን፥ እውነትን በፍጹም ከልባቸው ማውጣት እንደሌለባቸው አሳስበው፥ እርስ በርስ እንድንቀራረብ የሚያደርገን ልብ ስለሆነ ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከልብ እንደሆነ አስረድተዋል።

ስለዚህም በአዳራሹ የተገኙት በድፍረት በመነሳሳት በማን አለብኝነት የሐሰት ወሬን የሚሰራጩ ኃይሎችን ቸል እንዲሏቸው አደራ ብለዋል። እውነተኛ ልብ ያላቸው ተከራካሪ ወይም ጠበኛ ሳይሆኑ ከሌሎች የተለዩ ለመሆን ድፍረት እንዳላቸው፥ ያላቸውን አመለካከት በሌሎች ለመጫን የሚነሱ ሳይሆን ታማኝ እና የመገናኛ ድልድይ ሰሪዎች ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል። የግንኙነት መንገዶችን ስለሚያመቻቹልን የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎችን እንደ ድልድይ ልናያቸው እንችላለን ብለዋል።

ሃላፊነት

በመጨረሻም ስለ ሃላፊነት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እያንዳንዱ የሰው ልጅ የግንኙነት ዓይነት ተጨባጭ እና እውነታ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብርን በመገንዘብ እና በማሳደግ፣ ለጋራ ጥቅም ትኩረትን በመስጠት የሃላፊነት ድርሻን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“እናንተ የካቶሊክ ሚዲያ ባለሞያዎች ሰብዓዊ ክብርን ለመጠበቅ፣ መረጃን በብቃት ለማቃበል፣ መለያየትን እና አለመግባባትን ለመቃወም የተጠራችሁ መልዕክተኞች ናችሁ” ብለው፥ በምታቀርቧቸው እያንዳንዱ ጽሑፎች፣ በምታዘጋጇቸው እያንዳንዱ ፕሮግራሞች መካከል የሰው ልጅ የሁሉም አገልግሎቶች ማዕከል መሆኑን ሁልጊዜ ማስታወስ ይገባል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለሚመሩ ሁለት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋዜጠኞች ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ የጋዜጠኞች እና የጸሐፊዎች ባልደረባ የሆነው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ደ ሳሌስ ቃል በማስታወስ፥ የሳት2000 እና ራዲዮ inBlu2000 ጋዜጠኞች በቅርበት፣ ከልብ እና በሃላፊነት የሚያበረክቷቸውን የመገናኛ አገልግሎት እንዲቀጥሉበት በድጋሚ ጥሪ አቅርበው፥ "እግዚአብሔርን የምናስደስተው በተግባራችን ትልቅነት ሳይሆን በፍቅር ስለምናከናውነው ነው” በማለት ተናግረዋል።

30 January 2024, 16:48