ፈልግ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ለተጻፈ መጽሐፍ የመቅድም ጽሑፋቸውን አበረከቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያበረከቱት የመቅድም ጽሑፍ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ዕረፍት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፥ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፥ “ጳውሎስ ስድስተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢር” በሚል አርዕስት ለጻፉት መጽሐፍ የተዘጋጀ እንደሆነ ታውቋል። ይህ መጽሐፍ በውስጡ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2008 እስከ 2014 ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ ምዕዳን ሰብስብ የያዘ ሲሆን፥ የታተመውም በቫቲካን አሳታሚ ድርጅት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቅድም ጽሑፋቸው እንደገለጹት፥ ብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ በጌታችን ዕርገት ዓመታዊ በዓላት ለምዕመናን ያሰሟቸውን ተከታታይ ስብከቶች ለማሳተም በመወሰናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፥ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደተናዘዙት፥ ከዚች አሳዛኝ፣ አስገራሚ እና ድንቅ ምድር በሞት ተለይተው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሄዱበትን ዕለት ለማስታወስ እንደሆነ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በመሆን አገልግሎት የጀመሩበትን 60ኛ ዓመት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. ለማስታውስ መምረጣቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

“ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ‘ሰማዕት’ መቆጠር አለባቸው ብዬ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህን ሃሳብ ለብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ ማካፈላቸውንም አስታውሰዋል።በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ቀይ ወይስ ነጭ የቅዳሴ ልብስ መልበስ እንዳለባቸው እንደ ቀልድ መጠየቃቸውን አስታውሰው፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዲለበስ የተወሰነው ቀይ ቀለም ያለው የቅዳሴ ልብስ መሆኑን ሲገልጹ መጸጸታቸውን አስታውሰዋል።

በእርግጥም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 15/1969 ዓ. ም. ከካርዲናሎች መማክርት እና ከቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አመራሮች ጋር በብርሃነ ልደቱ በዓል ላይ መልካም ምኞት በተለዋወጡበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስድስተኛ፥ “ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በአንዳንድ ገፅታዎች ላይ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥ ወቅቱ መንፈሳዊ ውጥረት የነበረበት፣ በካህናት ውስጥ የሚታይ ችግር እየጨመረ የሄደበት እና በዚያ አውድም “ይህ የእሾህ አክሊላችን ነው” ማለታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቅድም ጽሑፋቸው አስታውሰዋል።

ቤተ ክርስቲያንን መውደድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ በሐዋርያዊ በአስተምህሮአቸው በተደጋጋሚ ካቀረቧቸው ጥሪዎች መካከል አንዱ እንደ ነበር የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ቤተ ክርስቲያንን መውደድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚገናኙበት፣ እርሱን የምናይበት መስታወት እንደሆነ እና አስፈላጊ እንደሆነ ይወስዱት ነበር ብለዋል። “ብቸኛው አስፈላጊ” በማለት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረቡትን ጸሎት ሁላችንም እናስታውሳለን። ብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ ለምዕመናኑ ባሰሙት ቃለ ምዕዳንም ይህንን ልዩ እና ፍጹም የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ለማስመር አስበዋል” ብለዋል።

“ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በጥልቅ የሚያሰላስሉ፣ የወንጌል አስተማሪ እና የኢየሱስ ክርስቶስ እርገት መስካሪ ነበሩ። ኢየሱስ የመረጣቸው የሦስቱ ሐዋርያት አጋር በመሆን ወደ ቅዱስ ወንጌል ክፍል መግባት ይፈልጉ ነበር ማለት እንችላለን። ከዚህም በላይ የቅርብ እና ሚስጢራዊ ፍላጎታቸው ዘወትር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተራራው ላይ መሆን ስለ ነበር ይህም ሕይወታቸው እንዲለወጥ አድርጎታል” ብለዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ።

“እነዚህ የብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ አስተንትኖዎች በመታተማቸው ደስተኛ ነኝ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ምስል ዘወትር እንደሚማርካቸው ገልጸዋል። ከአንዳንድ ንግግሮቻቸው መካከል ለምሳሌ በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ፣ በቅድስት አገር ናዝሬት እንዲሁም በሌሎች አገራት ያሰሙት ንግግሮች መንፈሳዊ ጥንካሬን እንደሰጧቸው እና በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ መልካም ነገሮችን እንዳጎናጸፋቸው በሌሎች አጋጣሚዎች መናገራቸውን አስታውሰዋል። “‘የወንጌል ደስታ’ የሚለው የመጀመርያው ሐዋርያዊ መልዕክቴ እና በጣም ለሚወደው፥ ‘ወንጌልን ማወጅ’ የሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ ሌላኛው ገጽታ እንደሆነ ታስቦ የቀረበ እንደ ነበር የሚታወቅ እውነታ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። “ሁሉም ሰው ልቤ ውስጥ ያለውን ስደግመው ሰምቶኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም  ጣፋጭ እና የሚያጽናና የወንጌል ደስታ እንደሆነ ገልጸው፥ በአርጄንቲና የቦይነስ አይረስ ጳጳሳ በነበሩበት ጊዜ እና ዛሬም የሚደግሙት እውነት እንደሆነ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ ላሳተሙት የቃለ ምዕዳናቸው ስብስብ የተመረጠው አርዕስት ታላቁ የዶሚኒካን ማኅበር የነገረ መለኮት ምሁር የሆኑት አባ ማሪ-ዮሴፍ ጊሎ ከተናገሩት የተወሰደ በመሆኑ እንደሚያደንቁ ገልጸው፥ አባ ማሪ-ዮሴፍ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ትንቢታዊነት፣ መንፈሳዊነት፣ አስተማሪነት፣ ሐዋርያዊነት እና ሚስዮናዊነት ለመግለጽ ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይ እንደጻፉትም አስታውሰዋል። ከዚህ በመነሳትም የመቅድም ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. የሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል በተቃረበበት በዚህ ወቅት፥ ሁሉም ሰው የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድ መሠረታዊ ጽሑፎችን በማንበብ ዝግጅት እንዲያደርግ አደራ ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ አባ ማሪ-ዮሴፍ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መሠረት በማድረግ በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ላይ ለማሰላሰል ያደረጉት ጥረት እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከዚህ አንፃር ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አስተምህሮ በድጋሚ መነበብ፣ መጠናት፣ መመርመር እና መተግበር እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ብለዋል።

በሊጧኒያ መዲና ቪልኒየስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አንድ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል ላቀረቡት ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የታሪክ ምሁራን የሁለተኛ የቫቲካን ጉባኤ ምክር ቤት ለመመስረት 100 ዓመታት ፈጀ” ማለታቸውን በመጥቀስ፥ ልትረዱኝ ከፈለጋችሁ የጉባኤውን የቤተ ክርስቲያን ሠነድ ለሌሎች ለማስተላለፍ በሚያስችል መንገድ ተግባራዊ አድርጉ” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ በማሰብ የወንጌል ደስታ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ እያንዳንዱ የወንጌል ሰባኪ በእግዚአብሔር ቃል እና በሕዝቡ ላይ ማሰላሰል እንዳለበት መጻፋቸውን አስታውሰዋል። በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህ እንደሆነ መግለጽ እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ እና እንዲሁም በቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የምታሰላስል ልትሆን እንደሚገባ እና ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ቃለ ምዕዳንም ይህን እንደሚያበረታታ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመቅድም ጽሑፋቸውን ደምድመዋል።

 

 

18 January 2024, 15:34