ፈልግ

የዩክሬይን እና የሩስያ ጦርነት ቀውስ የዩክሬይን እና የሩስያ ጦርነት ቀውስ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት የተጎዱ ሰዎች ሐዘን የዓለም መሪዎች ልብን ሊነካ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በዓለማችን ላይ እየታየ ባለው መጠነ ሰፊ የጭካኔ ድርጊት በማዘን በመካከለኛው ምስራቅ እና በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ. ም. ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የሞቱትን በጸሎት ስናስታውስ፣ ምድራችንን በደም በሚያረክሰው ጦርነት የተገደሉትን በርካታ ሲቪሎችን እና ተከላካይ የሌላቸውን ሰዎች እናስታውስ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት፥ ጣሊያን ውስጥ የጦርነት ሰለባዎችን ለማስታወስ ጥር 23/2016 ዓ. ም. የሚከበረውን ብሔራዊ ቀን ምክንያት በማድረግ ነው። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ የጦርነት ተጎጂዎች ሐዘን እና ለቅሶ የመሪዎችን ልብ በመንካት ወደ ሰላም እንዲያመሩ ያድርግ” ሲሉ አክሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ "ታሪኮችን ስናነብ በጦርነት ውስጥ ምን እየተከሰተ እንዳለ እና ብዙ የጭካኔ ተግባራት እንደሚፈጸሙ እንገነዘባለን ብለው፥ “እግዚአብሔር የሚጨክን ሳይሆን ዘወትር የዋህ በመሆኑ ከእርሱ ዘንድ ሰላምን እንለምን” ብለዋል።

የሰላም ግንባታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ቀደም ብለው ከፖላንድ ለመጡት ነጋዲያን እና ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፥ “አዲሱን ዓመት የጀመርነው በዓለማችን፣ በአገራችሁ፣ በቤተሰባችን እና በልባችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በመጋበዝ ነው” ብለዋል።

"ሰላም የሚገነባው በእውነት ላይ ሲመሠረት ብቻ መሆኑን ማስታወስ ይገባል" ሲሉ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። "ለጋራ ጥቅም በመጨነቅ፣ ቁጣን ማስወገድ እና የጋራ ይቅር ባይነት አሁን ባለንበት ዘመን ፍቅርን ለመገንባት ያግዛል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥቅምት 29/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በእስራኤል እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ሲያሰሙ ቆይተዋል። በዩክሬንም እንደዚሁ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፥ በየሳምንቱ በሚያቀርቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ምዕመናን ለሰላም እንዲጸልዩ በማለት ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

 

31 January 2024, 17:04