ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሁለት የጣሊያን በጎ አድራጎት ማኅበራት አባላትን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሁለት የጣሊያን በጎ አድራጎት ማኅበራት አባላትን በቫቲካን ሲቀበሉ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የተቸገሩትን መርዳት ከበጎነት በላይ ክብርን መስጠት እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በማኅበረሰብ ውስጥ አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን ለማገዝ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ሁለት የጣሊያን በጎ አድራጎት ማኅበራትን፥ ታኅሳስ 26/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ግለሰቦችን በማኅበረሰብ ዕድገት ውስጥ ማካተት፥ የተፈጥሮ ሃብትን እና የሰዎች ክህሎትን ለጋራ ጥቅም ዓላማ ማዋል አስፈላጊ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ዩክሬንን በድጋሚ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጎርጎሮሳዊውን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት መታሰቢያ በዓል ዋዜማ፥ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በማኅበር ተደራጅተው የተቸገሩትን በመርዳት ላይ የሚገኙ 3,500 ሰዎችን ዓርብ ታኅሳስ 26/2016 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል።   

ቅዱስነታቸው ከአባላቱ ጋር ያደረጉት ግንኙነት፥ ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ ጠቃሚ ቢሆንም ከወዳጅነት ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል፥ ይህ ካልሆነ መላውን ኅብረተሰብ የሚጠቅም የሰው ልጅ ግኑኝነት ማደግ እንደማይቻል ለመግለጽ መልካም አጋጣሚ እንደ ነበር ተመልክቷል።

በጎነትን በተግባር መኖር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አሁን የምንገኝበትን የብርሃነ ልደቱን ሰሞን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ “ድህነታችን ከእርሱ ጋር የምንገናኝበት ልዩ መንገድ መሆኑን ሊያሳየ እግዚአብሔር ፈልጎ ወደ እኛ ቀርቧል” በማለት አስታውሰዋል።  

የዕርዳታ ማኅበሩ የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንዳሉት ገልጸው ቅዱስነታቸው፥ ከኢኮኖሚያዊ ድህነት እስከ ባሕል አስፈላጊነት፥ ብቸኝነትን ከማስወገድ እስከ የስልጠና ዕድሎችን እስከ ማመቻቸት፣ መደበኛውን የገንዘብ እና የምግብ ዕርዳታዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ የእግር ጉዞ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ እና ሙዚቃን የመሳሰሉ በርካታ የዕርዳታ አገልግሎቶች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፥ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ የጻፉትን በመጥቀስ፥ ከህልውና እቅድ በላይ መሄድ የሚችል ዘይቤ ሊኖር እንደሚገባ አስምረውበታል።

“...ከመጀመሪያው ጀምሮ ከቀላል የንግድ ገጽታ በላይ ሸማቹን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰው ልጅ መሠረታዊ ገጽታን በመርዳት ሁሉም ሰው ሌላውን እንዲረዳ፥ በጎነትን በተግባር እየኖረ ፍቅርን መግለጽ ነው” በማለት ተናግረዋል።

እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ልብ፣ አእምሮ እና እጅ በተባበር አለባቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ልብ” ለሚለው ቃል በሰጡት ማብራሪያ፥ “ልብ የእውቀት ምንጭ እንደሆነ እና አእምሮ ብቻውን ሙሉ ዕውቀት ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል።

ያለ ልብ የሰው ልጅ እውቀት ሊኖረው ስለማይችል አእምሮን መጠቀም ይገባል፤ ልብ የሚያስበውን እጅ ያከናውናል፤ ...አእምሮ ከልብ እና ከእጅ ጋር መስማማት እንደሚገባ፥ ልብም ከሥጋ ጋር መዋሄድ እንደሚገባ እና እጅ ልብን እና አእምሮን እንደሚያገለግል መዘንጋት የለባችሁም” ብለዋል።

መተባበር ለሌላው ጠላት ለመሆን ሳይሆን መልካምነትን ለመገንባት ነው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በኅብረት ሥራ ማኅበር እና በፋውንዴሽን ውስጥ ያለውን ሞዴል በጥልቀት በመመልከት ባቀረቡት ገለጻ፥ ግለሰቦችን አንድ የሚያደርገው የጠላትነት ስጋት ሳይሆን የበጎ አድራጎት ግንባታ በመሆኑ ሊመሰገን እንደሚገባ ተናግረው፥ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ መጸለይ ይገባል ብለዋል። 

“በዚህ መንገድ የአንድን ሰው መልካምነት መጠበቅ ማለት አንዳንድ የዘርፉን ጥቅሞች መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ክብሩንም ማሳደግ ማለት እንደሆነ ማስታወስ ይግበል። በዚህ ደረጃ ትልቅ እድል ባላቸው እና በድህነት ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል ያለው ስብሰባ ወደ ተራ በጎ አድራጎትነት ከመቀየር የራቀ እና ዘወትር በጋራ ለማደግ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታን ይፈጥራል።”

ድህነትን ቀርቦ መመልከት እና መረዳት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ወደምንረዳቸውን ሰዎች ዘንድ መቅረብ ማለት ከሌሎች ጋር ተቀራርቦ መኖር ማለት ነው” ካሉ በኋላ የግል ገጠመኛቸውን ሲያስታውሱ፡- ለመናዘዝ የሚመጡ አንዳንድ ሰዎች ምጽዋት ይሰጡ እንደሆነ ወይም አቅመ ደካሞችን ይረዱ እንደሆነ እና የገንዘብ ዕርዳታ በሚያድረጉበት ወቅት ገንዘብ ወርውረው ማለፍ ሳይሆን ችግረኛውን በዓይን መመልከት እና በእጅም መዳሰስ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

በዩክሬን የሚሆነው አሰቃቂ ሁኔታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአዳራሹ ለተገኙት አባላት ቡራኬያቸውን በሰጡበት ወቅት፥ ማኅበራቱ ለሚያበረክቷቸው የዕርዳታ አገልግሎቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በዚህ ወቅት በዩክሬን የሚታየው አሰቃቂ ሁኔታ እጅግ አስፈሪ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማኅበራቱ በቅድስት መንበር የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር ላላቸው ኅብረት እና ለሚያደርጉለት ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት በሃብት እና በክህሎት በመተባበር፥ የእያንዳንዱን ሰው ዕድገት በማካተት ለሁሉም ሰው ጥቅም ማቀድን እንዲቀጥሉበት በማሳሰብ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

06 January 2024, 11:50