ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ጀንበር ሳትጠልቅ ቁጣ ወደ እርቅ ሊለውጥ ይገባል” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዛሬው አስተምህሮአቸው፥ ጀንበር ሳትጠልቅ ቁጣ ወደ እርቅ ሊለውጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ለአስተንትኖአቸው የመረጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከዚህ ቀጥሎ እናነብላችኋለን፥

“ኃጢአትን ግን አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ ለዲያቢሎስም ስፍራ አርስጡት። መራርነት እና ንዴት ቁጣም ጩሄት እና ስድብን ሁሉ ከክፉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” (ወደ ኤፌ.4:26-27 እና 31-32)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ በመቀጠል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከክፉ ሥነ-ምግባር መካከል አንዱ በሆነው በቁጣ ላይ እናሰላስላለን። በተለይ ይህ ክፉ ሥነ-ምግባር ጨለማ የነገሠበት ነው። ከአካላዊ ዕይታ አንጻር ለመለየት በጣም ቀላሉ ነው። በቁጣ የተሞላ ሰው ይህን የቁጣ ስሜት መደበቅ ይከብደዋል፡- ከአካል እንቅስቃሴው፣ ከጠብ አጫሪነቱ፣ ከአተነፋፈሱ፣ ከመገረም እና ከመሸማቀቅ ስሜቱ ማወቅ ትችላለህ።

አጣዳፊ በሆነው መገለጫው ቁጣ ምንም ዕረፍት የማይሰጥ ክፉ ተግባር ነው። ከደረሰበት ግፍ የሚወለድ ከሆነ ወይም ስቃይ እንደደረሰበት ከታመነ ብዙውን ጊዜ የሚፈፀመው ወንጀለኛው ላይ ሳይሆን የመጀመሪያው አሳዛኙ ተጎጂው ነው። በሥራ ቦታ ቁጣቸውን የሚያስታግሱ፣ ረጋ ያሉ እና ቻይ መሆናቸውን የሚያሳዩ፣ ነገር ግን በቤት ውስጥ ለሚስቶቻቸው እና ለልጆቻቸው የማይታገሡ ወንዶች አሉ። ቁጣ እየተስፋፋ የመጣ ክፉ ድርጊት ነው። እንቅልፍ ሊያሳጣን፣ የማመዛዘን ወይም የምክንያታዊነት አስተሳሰብን ሊያጠፋ ይችላል።

ቁጣ ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ሊያበላሽ የሚችል መጥፎ ተግባር ነው። የሌሎችን ሰዎች ልዩነት የመቀበል አቅም ማነስ ይገልፃል። በተለይም የሕይወት ምርጫቸው ከራሳችን ምርጫ ሲለያይ። በአንድ ሰው ክፉ ምግባር ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፥ ሁሉንም አንድ ላይ በማስቀመጥ፣ ቁጣን እና ብስጭትን የሚቀሰቅሰውን ሌላ ሰው ወይም ሌላኛዋ ሴትንም ሊያካትት ይችላል። አንድ ሰው የሌሎችን የድምጽ ቃና፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን፣ የአስተሳሰብ ዜይቤአቸውን እና ስሜታቸውን መጸየፍ ይጀምራል።

የሰዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት ወደዚህ አስከፊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ግልጽነት ይጠፋል። ምክንያቱም አንዱ የቁጣ ባህሪ ነገሮችን በጊዜ ማስታገስ አለመቻል ነው። በእነዚህ አጋጣሚዎች ከነገር በመራቅ እና ዝምታን በመምረጥ እንኳ የስህተቶችን ክብደት ከማቅለል ይልቅ አጉልቶ ያስቀምጠዋል። በዚህ ምክንያት ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት እንደሰማነው፥ የኤፌሶች ክርስቲያኖች ወዲያውኑ ችግሩን እንዲጋፈጡ እና እርቅ እንዲያደርጉ ይመክራቸዋል። ‘በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ’ (ኤፌ 4: 26)። ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ሁሉንም ነገር በሰላም መጨረሱ አስፈላጊ ነው። በቀን ውስጥ አንዳንድ አለመግባባቶች ቢፈጠሩ እና ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው መግባባት ካልቻሉ፥ እራሳቸውን እንደተለያዩ አድርገው ይገነዘባሉ። ሌሊቱን ለዲያብሎስ መስጠት አያስፈልግም። ክፉ ሥነ-ምግባር የራሳችንን እና የሌላውን ሰው ስህተቶች ሁል ጊዜ እንድናስብ በማድረግ ሌሊት ጥሩ እንዳንተኛ ያደርገናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረን ጸሎት ውስጥ፣ ከሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነቶች መጸለይ እናዳለብን ይመክረናል። ግንኙነታችን በችግሮች የተሞሉ ናቸው። በሕይወታችን ሁሉንም ሰው በትክክለኛው መጠን የማንወድ በመሆናችን፥ እኛን ከበደሉን ሰዎች ጋር መነጋገር አለብን። ለአንዳንዶች የሚገባቸውን ፍቅር አንሰጥም። ኃጢአተኞች እና ልናስተካክለው የሚገባን ነገር ያለን በመሆናችን ይቅር ማለትን መማር አለብን። ሰዎች በተቻለ መጠን የይቅርታን ጥበብ ካልተለማመዱ አብረው አይቆዩም። ቁጣ የሚበርደው በበጎነት፣ በልብ ግልጽነት፣ በየዋህነት እና በትዕግስት ነው።

ቁጣ በተመለከተ መነገር ያለበት አንድ ነገር አለ። ቁጣ የጦርነት እና የዓመፅ መነሻ በመሆኑ አሰቃቂ ምግባር እንደሆነ ይነገራል። የኢሊያድ ግጥም የአኪሌስን ቁጣ ማለቂያ የሌለው የከባድ ሐዘን ምክንያት እንደሆነ ይገልጸዋል። ነገር ግን ከቁጣ የሚመነጩ ነገሮች ሁሉ የተሳሳቱ አይደሉም። የማይካድ እና ፈጽሞ ሊካድ የማይገባ የግልፍተኝነት ክፍል በውስጣችን እንዳለ የጥንት ሰዎች በሚገባ ተረድተዋል። ምኞቶቹ በተወሰነ ደረጃ የሚታወቁ አይደሉም። የሕይወት ተሞክሮዎች በመሆናቸው ሊከሰቱ ይችላሉ። ቁጣ ለምን ተከሰተ ማለት አንችልም። ነገር ግን ለዕድገቱ ሁልጊዜ ተጠያቂዎች ነን። አንዳንድ ጊዜ ቁጣን በትክክለኛው መንገድ መወጣት መልካም ነው። አንድ ሰው በፍፁም የማይናደድ ከሆነ፣ ፍትሕ ሲጓደል የማይቆጣ ከሆነ፥ በአቅመ ደካሞች መጨቆን የማይሰማው ከሆነ ሰው አይደለም። ክርስትናውም ዝቅተኛ ነው።

መልካም የሆነ  እና የተቀደሰ ቁጣ አለ። ኢየሱስን በሕይወቱ ብዙ ጊዜ አጋጥሞታል። ስለ ልባቸው ድንዛዜ አዝኖ፥ ዙሪያዉን በቁጣ ተመለከተና ሰውየውን፥ ‘እጅህን ዘርጋ፤’ አለው። እርሱም ዘረጋ፤ እጁም ዳነች (ማር. 3:5)። እርሱ ክፉውን በክፉ አልመለሰም። ነገር ግን በሕይወቱ ውስጥ ይህ ስሜት እንዳለ ይገባው ነበር። በቤተ መቅደስ ውስጥ በነበሩ ነጋዴዎች ላይ ጠንካራ እና ትንቢታዊ ድርጊት ፈጽሟል። ይህን ተግባር በቁጣ ሳይሆን ነገር ግን  ለእግዚአብሔር ቤት ባለው ቅንዓት ነው። “ኢይሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትን እና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበር ገለበጠ፤ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው (ማቴ. 21:12-13)።

በመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ ለፍላጎቶች ትክክለኛውን መለኪያ ማግኘት የኛ ፈንታ ነው። በማስተማር ወደ በጎነት ልንለውጣቸው እንችላለን።"

 

 

31 January 2024, 16:46