ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከክፉ ውሲባዊ ምኞት በመቆጠብ ንጹህ ፍቅር ሊኖር ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 8/2016 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ጣሊያንን ጨምሮ ከልዩ ልዩ አገራት የመጡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ ተከታትለውታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው አስተምህሮአቸው፥ “ከክፉ የውሲብ ምኞት መጠበቅ እንደሚገና እና ንጹህ ፍቅርን መቀበል እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ለአስተንትኖአቸው እንዲሆን የመረጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናቀርብላችኋለን፥

“ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፤ እርሱም መቀደሳችሁ፥ ከዝሙት መራቃችሁ ነው፤ እያንዳንዳችሁ የራሳችሁን አካል በቅድስናና በክብር እንዴት መቆጣጠር እንደምትችሉ እወቁ፥ ይህን ስታደርጉ ግን እግዚአብሔርን እንደማያቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት መሆን የለበትም” (1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 4:3-5)

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ጥር 8/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ እንደምን አረፈዳችሁ! እኩይ ምግባር እና በጎ ምግባር በሚሉ ርዕሦች የጀመርነውን አስተምህሮ እንቀጥል። የጥንት አባቶች እንደሚያስተምሩን ከሆዳምነት ቀጥሎ ሁል ጊዜ ልብን የሚያታልል ሁለተኛው ፈተና በግሪክ ቋንቋ ‘ፖርኒያ’ ተብሎ የሚጠራው ፍትወተ ሥጋ ነው። ሆዳምነት ምግብን በሚመለከት የሚንጸባረቅ እኩይ ምግባር ቢሆንም፣ ይህ ሁለተኛው ተግባር ግን ከሌላ ሰው ጋር በተያያዘ፣ ማለትም የሰው ልጅ ከሌላ ሰው ጋር የሚኖረው የተመረዘ ግንኙነት ነው። በተለይም በፆታዊ ግንኙነት ውስጥ ያለው የተመረዘ ትስስር ነው።

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ፆታዊ ስሜትን የሚወቅስ ነገር አለመኖሩን ማስተዋል ተገቢ ነው። በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ መኃልየ መኃልይ በሁለት ፍቅረኛሞች መካከል ያለውን ፍቅር የሚናገር ድንቅ ግጥም ነው። ነገር ግን ይህ ውብ የሰው ልጅ ገጽታ ከአደጋ የጸዳ አይደለም። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ጉዳዩን አስቀድሞ በአንደኛው የቆሮንቶስ መልዕክት ውስጥ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእርግጥ በእናንተ ዘንድ ዝሙት እንዳለ ይወራል፤ የዚያ ዓይነት ዝሙት በአይዛብስ እንኳ የማይደረግ ነው። (1ኛ ቆሮ. 5፡1)። ይህ የሐዋርያው ነቀፋ የአንዳንድ ክርስቲያኖች የፆታ ግንኙነትን ጤናማ በሆነ መንገድ አለመያዙን ያመለክታል።

ነገር ግን ሰው በፍቅር የመያዝ ልምድን እንመልከት። ለምንድነው ይህ ምስጢር የሚከሰተው? ለምንድነው በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደዚህ ያለ አስደንጋጭ እና የሚረብሽ ተሞክሮ የሚሆነው? ይህን ማናችንም ብንሆን አናውቅም። በጣም ከሚያስደንቁ የህልውና እውነታዎች መካከል አንዱ ነው። በሬዲዮ የምትሰሟቸው አብዛኞቹ የፍቅር ዘፈኖች ስለዚህ ጉዳይ የሚናገሩ ናቸው፤ ስለሚያበራ ፍቅር፣ ሁልጊዜ ቢፈልጉትም ነገር ግን የማይደርሱት ፍቅር፣ በደስታ የተሞላ ፍቅር ወይም እስከ እንባ ድረስ የሚያሰቃይ ፍቅር።

በእኩይ ምግባር ያልተበከለ ከሆነ በፍቅር መያዝ ከንጹህ ስሜቶች መካከል አንዱ ነው። በፍቅር የተያዘ ሰው ለጋስ ይሆናል። ስጦታዎችን መስጠት ያስደስተዋል። ደብዳቤዎችን እና ግጥሞችን ይጽፋል። ሙሉ በሙሉ በሌላው ላይ በማተኮር ስለ እራሱ ማሰብ ያቆማል። አንድ በፍቅር የተያዘ ሰው ለምን እንዳፈቀረ ብትጠይቁት መልስ የለውም። በብዙ መልኩ የእርሱ ፍቅር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ነው። ያ በጣም ኃይለኛ የሆነው ፍቅር የዋህ ከሆነ ትዕግስት ሊኖረው ይገባል። ፍቅረኛሞች የሌላውን ሰው መልክ በትክክል አያውቁም። በሃሳብ ብቻ ይመለከቷቸዋል። ክብደቱን ወዲያው የማያውቁትን ቃል ለመግባት ዝግጁዎች ናቸው። አስደናቂ ነገሮች የሚበዙበት ይህ የፍቅር መንገድ ግን ከክፉ ነገር የተጠበቀ አይደለም። በምኞት ፈተና የረከሰ ነው። ይህ እኩይ ተግባር ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ አስጸያፊ ነው።

የመጀመሪያው በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ስለሚያበላሽ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ እንደዚህ ያለውን እውነታ ለማረጋገጥ ዕለት ተዕለት የምንሰማው ዜና በቂ ነው። ምን ያህሉ በጥሩ መንገድ የተጀመሩ የፍቅር ግንኙነቶች ወደ መርዛማነት ተለውጠዋል? የሌላውን ንብረት መመኘት፣ አክብሮትን ማጉደል እና ገደቦችን አለማወቅ። እነዚህ ንጽህና የጎደላቸው የፍቅር ሕይወት ናቸው። በጎነት ከፆታዊ ግንኙነት መታቀብ ጋር መምታታት የሌለበት። ይልቁንም ሌላውን ላለመያዝ ከመፈለግ ጋር መምታታት የለበትም። መውደድ ማለት ሌላውን ማክበር ማለት ነው፤ ደስታውን መፈለግ፣ ስሜቱን መንከባከብ፣ የእኛ ባልሆነ አካል፣ ሥነ-ልቦና እና ነፍስ ራስን ማጥፋት ማለት ነው። ስለተሸከሙት ውበት ሊታሰብ ይገባል።

በአንጻሩ ፍትወት በዚህ ሁሉ ላይ ይሳለቃል፣ ይዘርፋል፣ በችኮላ ይመገባል፣ የራሱን ፍላጎት እና ደስታ ብቻ እንጂ ሌላውን ማዳመጥ አይፈልግም። ፍትወት በእያንዳንዱ መጠናናት ላይ ይፈርዳል፣ በምክንያት እና በስሜቶች መካከል ያለውን ውህደት በጥበብ መኖር እንድንችል ሊረዳን አይፈልግም። ፍትወት የሚፈልገው አቋራጭ መንገዶችን ብቻ ነው። የፍቅር መንገድ በዝግታ መጓዝ እንዳለበት አይረዳም። ይህ የትዕግስት መንገድ ከመሰላቸት የራቀ የፍቅር ግንኙነታችንን ደስተኛ እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል።

ነገር ግን ፍትወት አደገኛ የሆነበት ሁለተኛ ምክንያት አለ። ከሁሉም የሰው ልጅ ደስታዎች መካከል ወሲባዊነት ኃይለኛ ድምጽ አለው። ሁሉንም ስሜቶች ያካትታል፤ በአካልም ሆነ በአእምሮ ውስጥ ይኖራል፤ በትዕግስት ካልተገራ፣ በመልካም ግንኙነት መካከል ካልተመዘገበ እና ሁለት ግለሰቦችን ወደ ፍቅር በሚያስገባ ታሪክ ውስጥ ካልወሰደ፥ የሰውን ልጅ ነፃነት ወደሚያሳጣ ሰንሰለት ይቀየራል። ወሲባዊ ደስታ በብልግና ምሥዕሎች ተበላሽቷል። ያለ ትውውቅ እና ያለ እርካታ የሚፈጸም ወሲባዊ ግንኝነት ሱስን ሊያስከትል ይችላል።

ከወሲባዊ ፍላጎት ጋር የሚደረገውን ጦርነት ማሸነፍ የዕድሜ ልክ ጥረት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የዚህ ጦርነት ሽልማት ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በወንድ እና በሴት መካከል ያለውን ፍቅር በፍጥረቱ ላይ የጻፈውን ውበት መጠበቅ ስለ ሆነ ነው። የውበታችንን ታሪክ መገንባት እና ርህራሄን ማዳበር ወደ ፈተና ከመሄድ እና ለሰይጣን ከመስገድ ይሻላል። አገልግሎት ከድል አድራጊነት ይሻላል። ምክንያቱም ፍቅር ከሌለ ሕይወት ብቸኛ ሆኖ ይቀራል።”

 

17 January 2024, 15:23