ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ምስጢረ ጥምቀታችን እኛን የእግዚአብሔር ልጆች አድርጎናል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዘንድ ታኅሳስ 28/2016 ዓ. ም. የተከበረውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል መታሰቢያን በማስመልከት፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን፥ በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ “ምስጢረ ጥምቀታችን እኛን የእግዚአብሔር ልጆች አድርጎናል!” በማለት ተናግረዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በዕለቱ ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት እናከብራለን (ማር. 1፡7-11)። ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በዮርዳኖስ ወንዝ ነው። አጥማቂው ዮሐንስ ሰዎች በጥምቀት ኃጢአታቸውን ትተው ለመለወጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ በመሆኑ ‘መጥምቁ’ ተብሎ ይጠራል። የመንጻት ሥርዓትን ያከናውናል። ሥነ-ሥርዓቱ እንደሚለው፥ ሕዝቡ በባዶ እግሩ እና ነፍሱ፥ በትሕትና እና በቅንነት ልብ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቁ ይሄዳሉ። ኢየሱስም ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደ። ከተጠመቀ በኋላም አገልግሎቱን ጀመረ። በዚህም ወደ እኛ ኃጢአተኞች ዘንድ ለመቅረብ እና ሊያገኘን እንደሚፈልግ አሳየ።

በዚያው ቀን አንዳንድ ያልተለመዱ ነገሮች ይከሰታሉ። መጥምቁ ዮሐንስም ያልተለመደ ነገር ተናገረ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉም ጋር እኩል መስሎ መገኘቱን በአደባባይ አምኖ፥ 'ነገር ግን ከእርሱ ይልቅ ኃያል የሆነው (ቁ. 7) በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል' ሲል ተናገረ (ቁ. 8)። ያን ጊዜ ሰማያት ተከፈ፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በኢየሱስ ላይ ወረደ (ቁ. 10) የእግዚአብሔር አብ ድምፅ ከላይ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- ‘የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል’ የሚል ድምጽ ከሰማይ ተሰማ (ቁ. 11)። ይህ ሁሉ በአንድ በኩል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሲገልጥልን፥ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚያደርገን ጥምቀታችን ይናገረናል።

በጥምቀት አማካይነት ወደ እኛ የሚመጣው፣ የሚያነጻን፣ ልባችንን የሚፈውስ፣ ልጆቹ፣ ሕዝቡ፣ ቤተሰቡ እና የመንግሥተ ሰማይ ወራሾች የሚያደርገን እግዚአብሔር ነው (የካቶሊክ ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1279)። እግዚአብሔርም ወደ እኛ በመቅረብ ከእኛ ጋር ይሆናል። የጥምቀት ቀናችንን ማስታወስ እና ቀኑንም ማወቁ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ለዚህም ነው። ሁላችሁንም እጠይቃችኋለሁ። እያንዳንዳችሁም ‘የተጠመቅሁበትን ቀን መቼ ነው’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። የማስታውሱ ከሆነም ወደ ቤታችሁ ስትመለሱ፥ ጥምቀት ምን እንደሆነ ጠይቁ። ከዚያም ላለመርሳት እና የጥምቀታችሁ ቀን አዲስ የተወለዳችሁበት ቀንና በጸጋ ሕይወት የተወለዳችሁበት ቀን ነው። ስለ ጥምቀት እግዚአብሔርን እናመስግን። ወላጆቻችን ለጥምቀት ስላደረሱን እግዚአብሔርን እናመስግን። ምስጢራቱን ለሰጡን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ የክርስትና አባት፣ የክርስትና እናት እና መላው ክርስቲያን ማህበረሰብ እግዚአብሔርን እናመስግን። አዲስ ልደት ቀን በመሆኑ የጥምቀት ቀናችሁን አክብሩ።

እራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡- በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በውስጤ ያለውን ታላቅ ስጦታ በሚገባ አውቃለሁ? እንደ ተወዳጅ ልጁ የሚያየኝ የእግዚአብሔር ብርሃን በሕይወቴ ውስጥ እንዳለ አምናለሁ? ጥምቀታችን በማስታወስ እግዚአብሔርን በውስጣችን እንቀበለው።

ይህንንም እኛን በሚወደን እና ከእኛ ጋር ሊሆን የሚፈልገውን የእግዚአብሔር ጸጋ በማስታወስ፥ እንዲህ በማለት የሚከተለውን የመስቀል ምልክት ማድረግ እንችላለን። የመስቀል ምልክት ይህንን የሚያስታውሰን በመሆኑ አንድ ላይ፥ በስመ አብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ እንበል። የልደት ቀናችሁ የጥምቀት ጸጋ የተቀበላችሁበትን ቀን የሚያስታውስ በመሆኑ ዕለቱን አትርሱት።

የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ እግዚአብሔር በውስጣችን የሚሠራውን ድንቅ ነገር እንድናከብር እና እንድንቀበለው ዘወትር ትርዳን።”

 

08 January 2024, 16:25