ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለቫቲካን ዋና የኦዲት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች መልዕክት ሲያስተላልፉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለቫቲካን ዋና የኦዲት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች መልዕክት ሲያስተላልፉ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሙስናን በከፍተኛ ደረጃ መዋጋት እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሰኞ ታኅሳስ 1/2016 ዓ. ም. የቫቲካን ዋና የኦዲት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ከሠራተኞቹ ጋር ባደረጉት ውይይት ሠራተኞቹ በቅድስት መንበር እና በቫቲካን ከተማ ያለውን የሙስና ተግባር እንዲዋጉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሰኞ ጠዋት ከቫቲካን ዋና የኦዲት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፥ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እራሳቸው ያቋቋሙት መሥሪያ ቤቱ፥ የቅድስት መንበር እና የቫቲካን ከተማ የፀረ-ሙስና ባለሥልጣን ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፥ በቅድስት መንበር እና በቫቲካን ከተማ ንብረቶች ላይ የፋይናንስ ኦዲት እንደሚያደርግ ይታወቃል።

ሙስናን መዋጋት እንደሚገባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጽሕፈት ቤተ ሠራተኞች ባደረጉት ንግግር፥ ከቫቲካን ሙስናን ማስወገድ አስፈላጊ እንድሆነ አሳስበዋል። “በቅድስት መንበር እና በቫቲካን ከተማ አስተዳደር ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች በእርግጥ በእምነት እና በታማኝነት ይሠራሉ” በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ “ነገር ግን ሙስና የሚያባብል እና አደገኛ ስለሆነ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ብለዋል። “ሠራተኞቹ ይህን ጥፋት ለመከላከል ብዙ ጊዜን እንደሚሰጡ አውቃለሁ” ያሉት ቅዱስነታቸው አክለውም፥ “በእያንዳንዱ ድርጊት ፍፁም ግልጽነትን ከምሕረት አስተሳሰብ ጋር ማመጣጠን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቅድስት መንበር ሃብት ላይ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል የቁጥጥር መንገድ እንዲያዘጋጁ በማለት ጠይቀዋል።

ነፃነትን፣ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን እና ሙያዊ ብቃት መጠቀም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በመቀጠል፥ የሦስቱን የኦዲት ቢሮ ዋና ዋና ባህሪያት፥ ነፃነት፣ ለዓለም አቀፍ መርሆች ትኩረት መስጠት እና ሙያዊ ብቃት እንደሆኑ አስረድተዋል። “ጽሕፈት ቤቱ በእርግጥ እራሱን የቻለ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በተዋረድ በሌሎች መሥሪያ ቤቶች የሚመካ አይደለም ብለዋል።

“ጽሕፈት ቤቱ ምንም ዓይነት የዘፈቀደ ድርጊት ከመከወን የራቀ ቢሆንም፥ ይህ ነፃነት ዘወትር በደንብ ወደ ታሰበበት እና በከፍተኛው የበጎ አድራጎት መርህ የተመራ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ “ከቀሪው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ፍትሃዊነትን እና መግባባትን ለማስፈን ምርጥ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መተግበር አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ሙያዊ ብቃት ቁልፍ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በርካታ የጽሕፈት ቤቱ አባላት ለአሥርተ ዓመታት ያካበቱት ከፍተኛ የሥራ ልምድ እንዳላቸው እና ለቀጣይ የሥራ ዘመንም ትምህርት ያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ወቅታዊ መሆን እውነተኛ የሞራል ግዴታ እና ዘርፉ የያዘው ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንደሆነም አስረድተዋል።

ድሆችን ማገልገል እንደሚገባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ፥ ሠራተኞቹ ከሥራቸው የበለጠ ነገር እንዳለ ተናግረው፥ አንዳንዶቹ በመመገቢያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚያገለግሉ እና ይህም መልካም እንደሆነ በመግለጽ፥ ክፍት በሆነ ልብ፣ በቀላል እና ነጻ በሆነ መንገድ እንዲያከናውኑት፥ ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋር ለመነጋገር እና ታሪኮቻቸውን ለማዳመጥ ጊዜን እንዲሰጡ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ሠራተኞቹን በሙሉ አመስግነው፥ ለቤተሰቦቻቸውም ጭምር መልካም የብርሃነ ልደቱ በዓል እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

12 December 2023, 15:48