ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ተግባራት ማኅበር የተወጣጡ ሕጻናት ጋር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ተግባራት ማኅበር የተወጣጡ ሕጻናት ጋር  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የበርካታ ሕፃናት ሞት ጦርነትን ማስቆም የሚችሉ ሰዎች ልብ እንዲነካ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን ካቶሊካዊ ተግባራት ማኅበር የተወጣጡ ወደ 70 የሚጠጉ ወንድና ሴት ሕጻናትን ታኅሳስ 5/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው በጋዛ፣ በዩክሬን እና በየመን ውስጥ በጦርነት አደጋ የሚሰቃዩ በርካታ ሕፃናትን በማስታወስ፥ በብርሃነ ልደቱ በዓሉ ወቅት የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ እርሱን እንድንወደው የሚጋብዘን መሆኑን አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከማኅበሩ ሕጻናት ጋር የብርሃነ ልደቱን መልካም ምኞት ለመለዋወጥ በተገናኙበት ወቅት ባተላለፉት መልዕክት፥ ዓለም የሚፈልገውን ብርሃን እና ሰላም ማግኘት የሚችለው እግዚአብሔርን በመውደድ እና እርስ በርስ በመዋደድ ብቻ ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመሪዎቻቸው እና በአስተማሪዎቻቸው በመታጀብ ወደ ቫቲካን ለመጡት ሕጻናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓለም በጦርነት ስቃይ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሕዝቦችን በተለይም ሕፃናትን አስታውሰዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን የሚገድለውን የአመጽ ድርጊትን ማቆም

በፍልስጤም እና በእስራኤል መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከሁለት ወራት ወዲህ የተገደሉ ሕጻናትን፥ ከሩሲያ ወረራ በኋላ ዩክሬን ውስጥ የተገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን እና እንዲሁም በየመን ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት የተገደሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትን ጠቅሰዋል።

“በጦርነት ምክንያት ጋዛ ውስጥ የሞቱት ሕጻናት ቁጥር ስንት እንደሆነ የጠየቁት ቅዱስነታቸው፥ ከሦስት ሺህ በላይ እንደሚደርሱ ገልጸው፥ በዩክሬን ከአምስት መቶ በላይ እንደሆኑ፥ በየመንም እንዲሁ በጦርነት ዓመታት ውስጥ የሞቱት ሕጽናት በሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የእነዚህ ሕጻናት ሞት በምላሹ ለዓለም ብርሃን እንድንሆን የሚጋብዘን መሆኑን እና በተለይም ጦርነትን እና አመጽን ማስቆም የሚችሉ የብዙ ሰዎች ልብን እንዲነካ በማለት አሳስበዋል።

እግዚአብሔርን፣ ሰዎችን እና ፍጥረታትን መውደድ

የብርሃነ ልደቱ በዓል የሚሰጠን የእግዚአብሔር ፍቅር አስደናቂ ስጦታ፣ እርሱን እንድንወደው የሚጋብዘን መሆኑን እና በተጨማሪም በወንድማማችነት እና እህታማማችነት እርስ በርሳችን መዋደድ እንደምንችል ይገልጻል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከእግዚአብሔር ፍቅር የሚገኝ ሌላው የፍቅር ስጦታ ፍጥረቱንም ጭምር እንድንወድ የሚጋብዘን መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ መሠረት የጣሊያ ካቶሊካዊ ተግባራት ማኅበር፥ “መኖሪያችን ይህች ምድር ናት” በሚል ርዕሥ ለመረጡት የዘንድሮ መሪ ሃሳብ አድናቆታቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ መሪ ርዕሡ፥ እግዚአብሔር በዙሪያችን ያለውን የተፈጥሮ ውበት እንድንገነዘብ እና እንድናከብረው የሚጠራን መሆኑን ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን ገልጸው፥ በፍጥረታቱ እና በሕዝቦች መካከል በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ፍቅር ማደግ እንደሚገባ እና በዚህም የተስፋ መልዕክት የሆነውን መንገድ በቁርጠኝነት እንዲከተሉ በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የጣሊያን ካቶሊካዊ ተግባራት ማኅበርተኛ የሆኑት ወንድ እና ሴት ሕጻናት፥ በጓደኝነት እና በርኅራኄ ልብ፥ ከፍጥረታት በሙሉ ጋር በመተባበር ለእግዚአብሔር ጥሪ እንዲታዘዙ በማለት አሳስበዋል።

 

 

 

16 December 2023, 15:18