ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የሐዋርያዊ ቅንዓት ምንጫችን መንፈስ ቅዱስ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር 26/2016 ዓ. ም. በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍልን አቅርበዋል። ይህን አስተምህሮአቸውን ከጣሊያን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች የመጡ ምዕመናንን ጭምሮ ከልዩ ልዩ አገራት የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ተከታትነውታል። በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፥ “የሐዋርያዊ ቅንዓት ምንጫችን መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት ገልጸዋል። ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ለአስተንትኖአቸው የመረጡትን መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“እነርሱም በተሰበሰቡበት ጊዜ ‘ጌታ ሆይ! በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?’ ብለው ጠየቁት። እርሱስም ‘አብ በጋዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትን እና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተእጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤’ አለ” (ሐዋ. 1: 6-8)።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ባለፉት ሳምንታት በቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮዎች፥ ወንጌልን መስበክ ደስታ እንደሆነ እና ይህ ደስታ ለዛሬው ዓለም መነገሩን ተመልክተናል። በዛሬው የመጨረሻ ክፍል የስብከተ ወንጌል አስፈላጊ ባህሪን እንመልከታለን። ስብከተ ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ መከናወኑ አስፈላጊ ነው። በእርግጥ እግዚአብሔርን ለሌሎች መመስከር፣ በደስታ የተሞላ ታማኝ ምስክርነት፣ የወንጌል ምስክርነት ዓለም አቀፋዊነት እና የመልዕክቱ ወቅታዊነት ብቻውን በቂ አይደለም። ያለ መንፈስ ቅዱስ ቅንዓት ሁሉ ከንቱ እና የውሸት ሐዋርያዊነት ነው። ለራሳችን ብቻ ይሆናል እንጂ ፍሬ የለውም።

የወንጌል ደስታ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ፥ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው እና ታላቁ ወንጌላዊ ነው’ የሚለውን አስታውሳለሁ። “ከእርሱ ጋር እንድንተባበር የጠራን እና በመንፈሱ ኃይል የሚመራን፣ በእያንዳንዱ የወንጌል ምስክርነት ሥራ ውስጥ ቀዳሚው ሁልጊዜ እግዚአብሔር ነው” (ቁጥር 12)። የመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚነት ይህ ነው! ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲናገር፥ በእርሻው ዘርን የሚዘራ ሰው፣ ‘ሌሊት እና ቀን ይተኛልም፣ ይነሳልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋል’ ከሚለው ጋር አነጻጽሮታል (ማር. 26-27)። በዚህ ምሳሌ ውስጥ ዋና ገፀ ባህሪው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ በወንጌል ተልዕኮ ውስጥ ቅድሚያን በመውሰድ የአገልግሎት ፍሬው እንዲያድግ ያደርጋል። ይህን ማወቁ እጅጉን ያጽናናናል። ከዚህም በተጨማሪ ሌላ እኩል አስፈላጊነት ያለውን ነገር እንድንገልጽ ያግዘናል። ይኸውም በሐዋርያዊ ቅንዓቷ ቤተ ክርስቲያን እራሷን የምትገልጽ ሳትሆን ነገር ግን ጸጋን፣ ስጦታን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ለሳምራዊቷ ሴት እንደተናገረው፥ (ዮሐ. 4፡10) መንፈስ ቅዱስ በትክክል የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እንድንረዳ ያግዘናል።

ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚነት ወደ ስንፍና ሊገፋፋን አይገባም። በራስ መተማመን ከተሳትፎ እራስን ማግለልን አያጸድቅም። ያለ እንክብካቤ ብቻውን የሚበቅለው ዘር ገበሬው ማሳውን ችላ እንዲል አይፈቅድም። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት የመጨረሻውን ምክር ሲሰጥ፥ ‘ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ’ (ሥራ 1: 8) በማለት ተናግሯል።

እግዚአብሔር ለእኛ ነገረ-መለኮትን የምንተገብርበት ወይም ሐዋርያዊ አገልግሎትን የምንፈጽምበት  መመሪያን አልሰጠንም። ነገር ግን ለwengiel ተልዕኮው የሚያነሳሳ መንፈስ ቅዱስን ሰጠን። በውስጣችን ያለው መንፈስ ቅዱስም የእሱን ዘይቤ ተከትለን ደፋር አገልጋዮች እንድንሆን እና እርሱን እንድንመስል ሁለት ባህሪያትን ሰጥቶናል። እነርሱም የአገልግሎት ዝግጁነት እና ትህትና ናቸው።

የአገልግሎት ዝግጁነት ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለሁሉም ሰው በደስታ እንድንመሰክር ያደርገናል። በሕይወታችን ውስጥ ሃይማኖታዊ አመለካከት እንዳይኖረን የሚያደርግ ይህ ዘመን እና በተለያዩ አካባቢዎች የወንጌል ምስክርነት አስቸጋሪ፣ አድካሚ እና ፍሬ ቢስ የሆነበት ይህ ዘመን ከሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ መራቅ ፈተና ውስጥ ሊያስገባን ይችላል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ምናልባት አንድ ሰው ከችግር የሚያመልጥበትን መንገድ ሊመርጥ ይችላል። ይህ ማለት አንድ ሰው ሁል ጊዜ የሚያደርገውን ነገር በመደጋገም፣ በመንፈሳዊነት ጥሪዎች በመሳብ ወይም የሥርዓተ አምልኮ ማዕከላዊነትን በተሳሳተ መንገድ በመገንዘብ፥ ራስን ለትውፊት ታማኝነት በሚመስሉ ፈተናዎች ሊያጋልት ይችላል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ እነዚህ በሙሉ ለመንፈስ ቅዱስ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የግል አለመርካቶችን የሚያመላክቱ ናቸው። ይልቁኑ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ዝግጁ መሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ደፋር መሆን እና በተልዕኮ መካከል በሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ መትጋት የሐዋርያዊ አገልግሎት ታማኝነት ማረጋገጫዎች ናቸው። “ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እሱን የምንገልጽባቸውን የተሳሳቱ እና አሰልቺ መንገዶችን ማለፍ ይችላል።  በመለኮታዊ ሥራው ያለማቋረጥ ያስደንቀናል። ወደ ምንጩ ለመመለስ እና ወደ ቅዱስ ወንጌል የመጀመሪያው አዲስነት ለመመለስ ጥረት ባደረግን ቁጥር አዳዲስ የአገልግሎት መንገዶች ይከፈታሉ። የተለያዩ የአገላለጽ መንገድ ያላቸውን እና ለዛሬው ዓለም አዲስ ትርጉም ያላቸውን ተጨማሪ የአገልግሎት ተነሳሽነቶችን፣ ምልክቶችን እና ቃላት ማግኘት እንችላለን” (የወንጌል ደስታ ቁ. 11)።

ለወንጌል አገልግሎት ዝግጁ መሆን እና እራስን ትሁት ማድረግ፥ መንፈስ አዱስ ወደ መጀመሪያው የወንጌል ምስክርነት የሚወስደን መንገዶች ናቸው። በእርግጥም ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ እንድናምን የሚያደርገን፣ በሞቱ እና በትንሳኤው፣ ማለቂያ የሌለውን የእግዚአብሔር ምሕረት የገለጠልን እና የሚነግረን የመንፈስ ቅዱስ እሳት ነው” (ivi፣ ቁ. 164)። የመጀመሪያው የወንጌል ምስክርነት ይህ ነው፣ ይህ የሁሉም ስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ እና የቤተ ክርስቲያን መታደስ፣ የጥረቶች ሁሉ ማዕከል መሆን አለበት፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ይወዳችኋል። ሊያድናችሁ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ብርሃን ሊሆናችሁ፣ ጥንካሬን ሊሰጣችሁ እና ነጻ ሊያወጣችሁ በየዕለቱ ጎናችሁ ይገኛል” (ቢድ)።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ እንድንማረክ በየቀኑ እርሱን እንጥራው። እርሱ የማንነታችን እና የአገልግሎታችን ምንጭ ይሁን። የእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን፣ ገጠመኞቻችን፣ ግንኙነታችን እና የወንጌል ምስክርነት መነሻችን ሊሆነን ይገባል። እርሱ ቤተ ክርስቲያንን ያበረታታል፣ ያድሳል። ከእርሱ ጋር ከሆንን መፍራት የለብንም። ምክንያቱም እርሱ ዘወትር ስምምነትን የሚያመጣ፣ ለአገልግሎት ዝግጁዎች እና ትሁቶች እንድንሆን የሚያደርገን፣ ወደ አንድነት የሚመራን፣ ለወንጌል ተልዕኮ የሚልከን፣ ልዩነትን አስወግዶ ወደ አንድነት የሚወስደን አምላክ ነው። ኃይላችን፣ የወንጌል ምስክርነት እስትንፋሳችን፣ የሐዋርያዊ ቅንዓት ምንጫችን ነውና፥ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ናልን!"

 

 

06 December 2023, 16:01