ፈልግ

በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ 75ኛ ዓመት መታሰቢያ በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ 75ኛ ዓመት መታሰቢያ   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለሰብዓዊ መብት መቆርቆር የማያቆም መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ኅዳር 30/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ካካፈሉት ቃለ ምዕዳን ቀጥለው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት መርተዋል። ቅዱስነታቸው ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባደረጉት ንግግርም፥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መታሰሚያ ቀንን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፥ በዓለማችን ውስጥ በጦርነት ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የተፈረመበትን 75ኛ ዓመት እሑድ ኅዳር 30/2016 ዓ. ም. ሲያከብሩ ባሰሙት ንግግር፥ ድንጋጌውን “በጥበብ የተሞላ የላቀ ዕቅድ ነው” በማለት ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ከተፈረመበት ጊዜ ወዲህ ብዙ እርምጃዎች መወሰዳቸውን፣ ብዙዎቹ አሁንም ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው እና በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ወደ ኋላ የሚመልሱ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰዋል።

"ለሰብዓዊ መብት መከበር ያለው ቁርጠኝነት አያበቃም!" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዕለት ተዕለት ሕይወት እና በተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ለሚሠሩ እና ለሚጥሩት ሰዎች በሙሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል ።

በደቡብ ካውካሰስ ሰላም ተስፋ

ከዛሬዎቹ አርሜኒያ፣ ጆርጂያ እና አዘርባጃን ጋር የሚዋሰነውን የደቡብ ካውካሰስ ግዛትን በንግግራቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ የአርመንያ እና የአዘርባጃን እስረኞች በመፈታታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ በደቡብ ካውካሰስ ሰላም እንዲሰፍን በአርሜኒያ እና በአዘርባጃን መካከል የተካሄደውን አዎንታዊ ተግባር በታላቅ ተስፋ እንደሚመለከቱ ተናግረዋል። በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል በተቻለ ፍጥነት የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ብርታትን ተመኝተዋል።

ለሰላም ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ በጦርነት ለሚሰቃዩ ሕዝቦች በሙሉ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አቅርበዋል። "ወደ ብርሃነ ልደቱ በዓል ስናመራ፥ በእግዚአብሔር እገዛ ለሰላም ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንችላለን ወይ?" በማለት ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ፥ ጥልቅ፣ ታሪካዊ እና ሥር የሰደዱ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውን አምነው፥ ሁሉም ሰው በጥበብ እና በትዕግሥት፥ በሰላም አብሮ ለመኖር የጣሩ ሰዎችን ምሳሌ እንዲከተል አደራ ብለዋል።

በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅ

ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሲቪሎች፣ ሆስፒታሎች እና የአምልኮ ሥፍራዎች ከጥቃት እንዲጠበቁ አሳስበው፣ ታግተው የሚገኙ ሰዎች እንዲፈቱ እና በግጭት ቀጠና ለሚኖሩ ሰዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲረጋገጥ በማለት ጥሪ አቅርበው፥ “የዩክሬን፣ የፍልስጤም እና የእስራኤል ሕዝቦች ስቃይ መርሳት የለብንም" በማለት አክለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ በተባበሩት አርብ ኤምሬቶች ዱባይ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP28) ሊጠናቀቅ መቃረቡን በማስታወስ፥ “የጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ እና የሕዝቦች ደኅንነት ጥበቃን የሚመለከቱ መልካም ውጤቶች እንዲገኙ” በማለት በጸሎት አቅርበዋል።

 

11 December 2023, 16:28