ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ብርሃነ ልደቱን የምንመሰክርበት ታማኝ ድምጽ ሊኖረን ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሑድ ኅዳር 30/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ምንባብ ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን አቅርበዋል። በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ምዕመናን ቅዱስነታቸው ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን፥ ብርሃነ ልደቱን የምንመሰክርበት ታማኝ ድምጽ ሊኖረን እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት ክቡራን አድማጮቻችን፥ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ያቀረቡትን ቃለ ምዕዳናን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ እንደምን አረፈዳችሁ! በስብከተ ገና ሳምንታት ውስጥ ሁለተኛ እሑድ በሆነው በዛሬው ዕለት፥ ከማር. 1፡1-8 ተወስዶ የተነበበው ምንባብ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት አስቀድሞ ስለተናገረው እና ‘በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ’ (ቁ. 3) እያለ ስለሚገልጸው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ይናገራል። ምድረ በዳ ድምጽ የሌለበት እና ባዶ ሥፍራ፥ እነዚህ ሁለቱ ተቃራኒ ምስሎች ቢሆኑም ነገር ግን በመጥምቁ ውስጥ አማካይነት አንድ ሆነዋል።

መጥመቁ ዮሐንስ፥ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር በገቡበት በረሃማ ሥፍራ በሆነው በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ሰበከ (ኢያሱ 3፡1-17)። መጥመቁ ዮሐንስ ይህን ያደረገው፥ ሕዝቡ ሳይረበሽ እግዚአብሔርን እንዲሰማ ብሎ ለአርባ ዓመታት ያህል ሲያስተምር ወደቆየበት ወደ በረሃማው አካባቢ ለመውደስ ስለ ፈለገ ይመስላል። ይህ ሥፍራ ዝምታ የሰፈነበት፣ ለሕይወት ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች የሚገኙበት እና በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ማትኮር ሳይሆን ነገር ግን አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር ያለበት ሥፍራ ነው

ይህ ምክር ዘወትር ጠቃሚ ነው። በሕይወት ጉዞ ‘ብዙ’ ነገሮችን መመኘት ይቅርብን። ምክንያቱም መልካም ሕይወት መኖር ማለት በማይጠቅሙን ነገሮች መሞላት ማለት ሳይሆን፥ ነገር ግን ከመጠን በላይ የሆኑ ነገሮችን ከማሰብ በእግዚአብሔር ፊት አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማትኮር ማለት ነው። ከንቱ በሆኑ ቃላት እና ጨዋታዎች ከመበከል ነጻ መሆናችንን የምናውቀው፥ በጽሞና ጸሎት የአብ ቃል ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ቦታን ስንሰጥ ብቻ ነው። ከፍሬ ቢስ ቃላት እና ትክክለኛ ካልሆነ የብዙሃን መገናኛ እና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መቆጠብ እና አስተዋይነት ወይም በጎ ምግባር በክርስትና ሕይወት ውስጥ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው።

ሁለተኛው ምስል ወደ ሆነው ወደ ድምጽ ስንመጣ፥ ድምጽ የምናስበውን እና በልባችን ውስጥ ያለውን በንግግር የምንገልጽበት መንገድ ነው። ስለዚህም ድምጽ ከዝምታ ጋር የተቆራኘ መሆኑን እንረዳለን። ምክንያቱም መንፈስ የሚናገረውን ካዳመጡ በኋላ የሚያድገውን እና የሚወጣውን ስለሚገልፅ ነው። ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! አንድ ሰው ዝም ማለትን የማያውቅ ከሆነ ጥሩ ነገር መናገርን ላያውቅ ይችላል። ለዝምታ የበለጠ ትኩረት በሰጡ ቁጥር ቃላት ጥንካሬን ያገኛሉ። የመጥምቁ ዮሐንስ ድምፅ ከልምዱ እውነተኛነት እና ከልቡ ንፅህና ጋር የተያያዘ ነው።

በሕይወታችን ውስጥ ዝምታ ምን ቦታ ይኖረዋል? ብለን እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። ምናልባትም ባዶ እና አስጨናቂ ነው? ወይስ ሌሎችን ለማዳመጥ፣ ለጸሎት እና ልብን ከክፋት ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው? ሕይወታችን የተረጋጋ ነው ወይንስ ከመጠን በላይ በሆኑ ነገሮች የተሞላ ነው? ከባድ የሆነውን ነገር መቋቋሙ ወይም ችሎ ማለፉ ከባድ ቢሆንም፣ ለዝምታ፣ ለጥንቃቄ እና ሌላውን የማዳመጥ አስፈላጊነት ዋጋን እንስጥ። ዝምታን የመረጠች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ዝምታ የነገሠበትን ሥፍራ እንድንወድ፣ ብርሃነ ልደቱን የሚመሰክሩ ታማኝ ድምጾች መሆን እንድንችል ትርዳን።”

 

11 December 2023, 16:18