ፈልግ

የደቡብ ኮሪያ መንፈሳዊ ነጋዲያን ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስጦታን ባበረከቱላቸው ወቅት የደቡብ ኮሪያ መንፈሳዊ ነጋዲያን ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ስጦታን ባበረከቱላቸው ወቅት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለ60 ዓመታቱ የቫቲካን እና የደቡብ ኮሪያ ግንኙነት እግዚአብሔርን አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የኮሪያ ሪፐብሊክ እና ቅድስት መንበር በመካከላቸው የመሠረቱት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ለኮሪያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ሁለቱ ወገኖች የወዳጅነት ግንኙነታቸውን እና ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ሰላም እና ዕርቅ በጋራ እንደምሠሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለደቡብ ኮሪያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (C.B.S.K) ፕሬዝዳንት ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ማትያስ ሪ ዮንግ-ሁን በላኩት መልዕክት ከልብ የመነጨ መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፥ በደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፥ ያላቸውንም መንፈሳዊ ቅርበት አረጋግጠውላቸዋል።  

ደቡብ ኮሪያ እና ቫቲካን በመካከላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የጀመሩት እንደ ጎርጎሮሳዊው በ1963 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል። ከዚያም ከቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጋር በተፈጠረ የጠበቀ ግንኙነት፥ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊው በ1984 እና በ1989 ዓ. ም. ሁለት ጊዜ ደቡብ ኮሪያን እንደጎበኟት እና በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስድስተኛው የእስያ አኅጉር የወጣቶች ቀን በተከበረበት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2014 ዓ. ም. ጎብኝተዋት እንደ ነበር ይታወሳል።

በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ሰላም እንዲሰፍን በጋራ መሥራት

የደቡብ ኮሪያ እና የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ሰኞ ታኅሳስ 1/2016 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ሴኡል በሚገኘው ማይኦንግዶንግ ካቴድራል ውስጥ ብጹዕ አቡነ ሪ ዮንግ-ሁን በመሩት የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተከብሮ መዋሉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በኮሪያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ በሆኑት በሊቀ ጳጳስ አቡነ ፈርናንዶ ዱርቴ ባሮስ ሬይስ በኩል በላኩት መልዕክታቸው፥ ደቡብ ኮሪያ እና ቅድስት መንበር በመካከላቸው ያለውን የወዳጅነት ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ሰላም እና ዕርቅ እንዲመጣ በጋራ እንደሚሠሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የደቡብ ኮሪያ ካቶሊክ ማኅበረሰብ ላገኘው ብዙ ፀጋዎች እናመሰግናለን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን የደቡብ ኮሪያ ብጹዓን ጳጳሳት በቅዱስ ቁርባን በኩል ካቀረቡት ምስጋና ጋር በማገናኘት እንደጻፉት፥ በተለይ ለወንጌል መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና የደቡብ ኮሪያ ማኅበረሰብ ለደህንነቱ ላበረከተው አስተዋፅዖ ምስጋናን ልንሰጥ እንችላለን" ብለው፥ መልካም ተግባራቸው ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራቱን እንደሚቀጥል በመተማመን፥ በተለይም ለተገለሉት፣ ለድሆች እና ተስፋ ለሌላቸው ሰዎች እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የ2014 (እ.አ.አ) ሐዋርያዊ ጉብኝት አስደሳች ትዝታዎች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደ ጎርጎሮሳዊው በ2014 ዓ. ም. በደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት እና በተለይም የኮሪያ ሰማዕታትን ይፋ ያደረጉበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በማስታወስ፣ “ሰማዕታቱ ኢየሱስ ክርስቶስን በመውደዳቸው እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማስፋፋት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሕይወታቸውን በዚህ ምድር ላይ በማሳለፋቸው ያበበች እና የደመቀች ቤተ ክርስቲያን ፍሬ የዘሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በደቡብ ኮሪያ ሊከበር የሚጠበቀው የዓለም ወጣቶች ቀን

እንደ ጎርጎሮሳዊው በ2027 ዓ. ም. የሚከበረውን የዓለም ወጣቶች ቀንን በጉጉት እንደሚጠብቁት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶቹ በበዓሉ ላይ ለመገኘት ሲዘጋጁ ክቡር የሆነውን ምስክርነታቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስጠትን እንዲቀጥሉ ጸሎታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ቀጣዩን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አስተናጋጅ እንድትሆን የተመረጠችው የደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል መሆኗ ይታወቃል። ደቡብ ኮሪያ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልን እንደ ጎርጎሮሳውዊው በ1995 ዓ. ም. ካስተናገደች ፊሊፒንስ ቀጥላ ሁለተኛዋ የእስያ አገር እንደምትሆን ታዉቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገሪቱን “ለኮሪያ ሰማዕታት፣ የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የጸጋ እና የሰላም ቃል ኪዳን በማቅረብ ቡራኬያቸውን ሰጥተው መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

12 December 2023, 15:59