ፈልግ

Immaculate Conception of the Blessed Virgin Mary

“እመቤታችን ቅድስት ማርያም የጸጋ ስጦታችንን ከክፉ ነገር እንድንጠብቅ በአማላጅነቷ ትርዳን!"

የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠርን በምትከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዓርብ ኅዳር 28/2016 ዓ. ም. የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል እየተከበረ ይገኛል። ይህ በዓል ባለፈው አመት በተከበረበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓሉን ለማክበር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እመቤታችን ቅዱስ ድንግል ማርያም የፀጋ ስጦታችንን ከክፉ ነገር እንድንጠብቅ በአማላጅነቷ ትርዳን ማለታቸው ተገልጾ ነበር።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ

በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።

ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”

ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”

ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! እንኳን አደረሳችሁ!

ከሉቃ. 1: 26-38 ተወስዶ የተነበበው የክብረ በዓሉ የቅዱስ ወንጌል ንባብ እኛን ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ በመውሰድ ከመልአኩ ገብርኤል ስለቀረበላት ብስራት ይናገራል። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም እንዲህ ሲል ሰላምታ አቀረበላት፥ አንቺ ጸጋን የተሞላሽ፤ ሰላም ላንቺ ይሁን፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤ (ሉቃ. 1: 28) መልአኩ ገብርኤል ማርያምን በስም አልጠራትም። ነገር ግን በማታውቀው አዲስ ስም፥ ‘ጸጋ የሞላብሽ!’ አላት። ስለዚህም ይህ ስም ከኃጢአት የጸዳች በመሆኗ እግዚአብሔር የሰጣት ስም እና ዛሬ እኛ የምናከብረው ስም ነው።

ቅድስት ማርያም የተደነቀችበትን ነገር እንመልከት፥ ማርያም የራሷን እውነተኛ ማንነት ያገኘችው ከዚያ ጊዜ በኋላ ነበር። በእውነትም እግዚአብሔር ማርያምን ‘ጸጋ የሞላብሽ!’ ብሎ በጠራት ጊዜ ታላቁን ምስጢር ገልጦላታል። ማርያም ቀደም ሲል በጸጋ መሞላቷን አታውቅም ነበር። ተመሳሳይ ሁኔታ በእኛም ላይ ሊደርስ ይችላል። በምን መልኩ ሊደርሰን ይችላል? እኛ ኃጢአተኞች ሕይወታችንን የሞላውን እና ከሁሉ የሚበልጥ መልካም የመጀመሪያ ስጦታn ተቀብለናል። ስለ መጀመሪያው ኃጢአት ብዙ ጊዜ እንናገራለን። ነገር ግን የማናስተውለውን የመጀመሪያ ጸጋን ተቀብለናል።

ይህ የመጀመሪያ ጸጋ የምንለው ለመሆኑ ምንድን ነው? በምስጢረ ጥምቀት የተቀበልነው ጸጋ ነው። ይህን ልናስታውሰው እና አልፎ ተርፎም ልናከብረው ይገባል! እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፥ ይህ በጥምቀታችን ዕለት የተቀበለው ጸጋ አስፈላጊ ነው? የጥምቀት ቀናችንን የምናስታውስ ስንቶቻችን ነን? ቀኑ መቼ ነበር? የማታስታውሱት ከሆነ አባቶችን ወይም እናቶችን ጠይቁ። ምክንያቱም ያች ቀን የታላቁ ጸጋ ቀን ናት፤ የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ ቀን ናት፤ የመጀመሪያ ጸጋ ቀን ናትና። በዚያች ቀን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ወይም ወደ ሕይወታችን ወርዷል። እኛም ለዘላለም የእርሱ ተወዳጅ ልጆቹ ሆነናል። የምንደሰትበት የመጀመሪያ ውበታችን ይህ ነው! በጸጋ መሞላቷን በሕይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ በማወቅ የተገረመች ቅድስት ማርያም ዛሬ እኛም በጸጋ ሙላት እንድንደነቅ ታደርገናለች። በጸጋ መሞላታችንን በነጭ የጥምቀት ልብስ ምሳሌ እንገነዘባለን። ይህ የነጭ ልብስ ምሳሌ ለዓመታት እራሳችንን ካረከስነው ክፉ ነገር ጸድተን፣ ከደረሰብን ክፋት የሚበልጥ በጎ ነገር መኖሩን ያሳስበናል። እግዚአብሔር የሚለንን እንስማ፥ ልጆቼ እኔ እወዳችኋለሁ! ሁል ጊዜም ከእናንተ ጋር ነኝ! እናንተ የምታስፈልጉኝ ውድ ልጆቼ ናችሁ! ሕይወታችሁም ውድ ነው! እግዚአብሔር ለእኛ የሚያስተላልፍልን መልዕክት ይህ ነው። ነገሮች በጥሩ መንገድ ሳይሄዱ ቀርተው ተስፋ ሲያስቆርጡን፣ የሐዘን እና የከንቱነት ስሜት ሲሰማን በጥምቀት የተቀበልነውን የመጀመሪያ ጸጋ እናስታውስ። ከዚያች ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ዘወትር ከእኛ ጋር መሆኑን እንደገና እናስብ።

የእግዚአብሔር ቃል ሌላ አንድ ጠቃሚ ነገር ያስተምረናል፥ ከእግዚአብሔር የተቀብልነውን ጸጋ ተንከባክቦ ማቆየት ዋጋን ያስከፍላል፤ ትግልን ይጠይቃል። ቅዱስ ወንጌልም፣ ማርያም ለእግዚአብሔር በድፍረት ‘አዎን!’ እንዳለች ይነግረናል። በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕ. 3:15 ላይ፥ ‘በአንተ እና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትነድፋለህ።’ በማለት ስለ መጀመሪያው ኃጢአት፣ ስለ ፈታኙና ፈተናዎቹን በመቃወም ስለሚደረገው ጦርነት ይነግረናል። ነገር ግን ይህን ከተሞክሮ አኳያም እናውቀዋለን። ጥሩ ነገር መምረጥ ጥረትን ይጠይቃል፣ ዋጋም ያስከፍለናል። በውስጣችን ያለውን መልካም ነገር ጠብቆ ማቆየት ጥረትን ይጠይቃል። ራሳችንን ለክፉ ነገር አሳልፈን በመስጠት፣ ለጥቅማችን ስንል ተንኮልን በመሥራት፣ ወይም ልባችንን የሚያረክሱ ነገሮችን በመሥራት ወይም በማይጠቅሙ ጎጂ ነገሮች ላይ ምን ያህል ጊዜን አባክነናል። ጸሎት ማድረስን በማቋረጥ፣ በእምቢተኝነት ስንት ጊዜ አሳልፈናል?

ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲያጋጥመን ዛሬ የምሥራች አለን። ኃጢአት የሌለባት በታሪክ ብቸኛዋ ሰው የሆነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመከራችን ሁሉ መካከል ከእኛ ጋር ናት። ቅድስት ማርያም ከሁሉም በላይ ደግሞ እናታችን ናት። እኛም መልካም የሆነውን ለመያዝ ጥረት የምናደርግ በሙሉ በቅድስት ድንግል ማርያም ልንተማመን እንችላለን። ራሳችንን ለማርያም በአደራ እናቀርባለን። ‘እጄን ያዢኝ፣ ምሪኝ፤ ከአንቺ ጋር ስሆን ከክፉ መንፈስ ጋር በማደርገው ውጊያ የበለጠ ጠንካራ እሆናለሁ! ከአንቺ ጋር ስሆን የመጀመሪያውን የጸጋ ሙላት እንደገና አገኛለሁ!’ እንበል። ዛሬም፣ ነገም በየቀኑ እራሳችንን ለማርያም በአደራ እንስጥ። ‘ማርያም ሆይ! ሕይወቴን ላንቺ አደራ እሰጣለሁ፤ የቤተሰቤን፣ የሥራዬን፣ የልቤንና የልፋቴን አደራ ላንቺ አቀርባለሁ። ሕይወቴን ለአንቺ አቀርባለሁ!’ ንጽህት እመቤታችን ማርያም ሆይ! ጸጋችንን ከሰይጣን አደጋ ጠብቀን ለማቆየት አግዢን!” 

ምንጭ፡ የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠርን በምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ሐሙስ ኅዳር 29/2015 ዓ. ም. የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓሉን ለማክበር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ካደረጉ የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

 

08 December 2023, 11:14