ፈልግ

2023.11.01 Papa Francesco intervista Rai 01.11.23

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጦርነት እንዳይባባስ 'ሰብዓዊ ጥበብ' ሊረዳን ይችላል ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጣሊያን የዜና ፕሮግራም Tg1 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ዓለም አቀፍ ግጭቶች የተናገርሱ ሲሆን በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በመዳሰስ ጦርነትን መለማመድ የለብንም በማለት የጦር መሳሪያ ንግድን መውቀሳቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስራኤል እና በፍልስጤም የተቀሰቀሰው ጦርነት ዓለም አቀፋዊ ሊሆን "ይቻላል" ነገር ግን "በሰው ጥበብ" በመታመን ብቻ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለው ያሉ ሲሆን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስተያየት የጣሊያን የዜና ፕሮግራም ዳይሬክተር ጂያንማርኮ ኪዮቺ ረቡዕ ጥቅምት 21/2016 ዓ.ም በኢጣሊያ የብዝሃን መገናኛ RaiUno ላይ በተላለፈው ረጅም ቃለ ምልልስ ላይ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

እስራኤል እና ጋዛ

በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በድጋሚ “እያንዳንዱ ጦርነት ሽንፈት ነው። በጦርነት የምፈታ ነገር የለም። ምንም ነገር የለም በጦርነት የምፈታ፣ ሁሉም ነገር የምገኘው በሰላም፣ በውይይት ነው” በማለት የተናገሩ ሲሆን በመቀጠልም “ቂቡዚም በተባለው ሥፍራ ገብተው ሰዎችን አግተው ወስደዋል፣ ሰዎችን ገለዋል፣ እናም ከዚያ በኋላ የተሰጠው ምላሽ እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስመለስ፣ እነሱን ለማዳን ይሄዳሉ። በጦርነት የአንዱ ጥፊ ሌላውን ያስቆጣል። አንዱ ጠንካራ ሌላው ደግሞ የበለጠ ጠንካራ ነው፣ እናም እንደዚያው ይቀጥላል። ጦርነት ሽንፈት ነው። እንደ አንድ ተጨማሪ ሽንፈት ተሰማኝ። አብረው መኖር ያለባቸው ሁለት ህዝቦች ናቸው። በዛ ጥበብ የተሞላ መፍትሄ፡- ሁለት ህዝቦች፣ ሁለት ግዛቶች። የኦስሎ ስምምነት፡ ሁለት በግልፅ የተከፋፈሉ መንግስታት እና ኢየሩሳሌም ልዩ ደረጃ ያላት" መሆን ይኖርባታል ማለታቸው ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈውን ሳምንት የሰላም ጸሎት በማስታወስ ዓለም “በጣም ጨለማ ሰዓት” ውስጥ እንዳለች በድጋሚ ተናግረዋል። አክሎም “አንድ ሰው በግልፅ የማሰላሰል ችሎታን ማግኘት አይችልም እና በጨለማው ሰዓት ጨምረ እናገራለሁ ጦርነት በዚህ ሰዓት አንድ ተጨማሪ ሽንፈት ነው። ካለፈው የዓለም ጦርነት ወዲህ እ.አ.አ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን፣ ጦርነቶቹ ስላላቆሙ፣ አንዱ ከሌላው ሽንፈት በኋላ እንዲህ ነበር የቀጠለው። ግን አሁንም በጣም አሳሳቢው ችግር የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ ነው። በእዚህ ረገድ የምፈሰውን ኢንቨስትመንቶችን የተረዳ አንድ ሰው በስብሰባ ላይ ያገኘሁት ሰው ዛሬ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ኢንቨስትመንቶች የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች መሆናቸውን ነግሮኛል” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጋዛ ውስጥ ለሚገኙ ሃይማኖት ተቋማት ጋር በየቀኑ በስልክ እንደምነጋገሩ ተናግረዋል። “በየቀኑ በእዚያ የሚገኘውን ግብፃዊ ረዳት ቆሞስ ከሆኑት ወደ አባ ዩሱፍን እደውላለሁ እናም እንዲህ ይሉኛል፣ ‘በቁምስና ውስጥ 563 ሰዎች፣ ሁሉም ክርስቲያኖች እና አንዳንድ ሙስሊሞች አሉን። የእማሆይ ቴሬዛ ማሕበር አባላት ደናግላን የምንከባከቧቸው የታመሙ ልጆች አሉ። በዚህች ትንሽ ደብር 563 ሰዎች አሉ! በየቀኑ ከእነርሱ ጋር ለመሆን እሞክራለሁ። ለጊዜው እግዚአብሔር ይመስገን የእስራኤል ወታደሮች ያንን ደብር ያከብራሉ” ሲሉ ነግረውኛል ብለዋል።

ጦርነት እና ፀረ-ሴማዊነት

“አስታውሳለሁ” ያሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “በጵጵስናቸው መጀመሪያ ላይ በጣም አስቸጋሪው ጊዜ በሶሪያ ውስጥ እንዲህ ባለው ኃይል ጦርነቱ የተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር፣ እናም ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ባሉበት አደባባይ ላይ የጸሎት ተግባር አደረግሁ፣ ምንጣፋቸውን ተሸክመው መጥተው ከምጸልዩ ሰዎች ጋር ጸልዬ ነበር። ይህ በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ለኔ ያ ጦርነት መጥፎ ነገር ነበር፣ ግን ከዚያ ይህን መናገር ጥሩ አይደለም፣ ጦርነትን አትለማመዱት፣ በምያሳዝን ሁኔታ  መልመድ አልነበረብንም” ብለዋል።

ልፈጠር የምችለውን ዓለም አቀፋዊ መሻሻል በተመለከተ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የብዙ ነገሮች እና የብዙ ህይወት መጨረሻ ይሆናል። የሰው ጥበብ እነዚህን ነገሮች የምያቆም ይመስለኛል። አዎ የምቻልበት ሁኔታ አለ ግን... ይህ ጦርነት እኛን የምነካው እስራኤል፣ ፍልስጤም፣ ቅድስት ሀገር፣ ኢየሩሳሌም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ነው። ነገር ግን [በጦርነት] ላይ የምትገኘው የዩክሬን ጉዳይ እኛንም ይነካናል፣ ምክንያቱም በአቅራቢያችን የምገኝ ነውና፣ ነገር ግን እኛን በቀጥታ የማይነኩ ሌሎች ብዙ ጦርነቶች አሉ: የመን፣ ምያንማር ከሮሂንጊያዎች ጋር በምያደርጉት ግጭት ሰማዕታት ናቸው። ዓለም በጦርነት ውስጥ ናት፣ ነገር ግን የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪው ከጀርባው ነው ያለው” በማለት ቅዱስነታቸው በቁጭት ተናግረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ጸረ-ሴማዊነት ተናግሯል፣ እሱም “በምያሳዝን ሁኔታ ተደብቆ ይቆያል” ያሉ ሲሆን እንዲሁም “ለምሳሌ እዚህም እዚያም ወጣቶች አንድ ነገር ሲያደርጉ ማየት ትችላለህ። እውነት ነው በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ከባድ ነው፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ፀረ-ሴማዊ የሆነ ነገር አለ፥ እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ የተካሄደውን እልቂት ማየት ሁልጊዜ በቂ አይደለም፣ በእዚያ ወቅት ስድስት ሚሊዮን ሰዎች ተገድለዋል፣ ተባርረዋል፣ እናም ይህ ጉዳይ አሁንም ቢሆን አላለፈም። በምያሳዝን ሁኔታ ግን አሁንም ጸረ-ሴማዊነት አሁንም አለ። እንዴት እንደምገለጽ አላውቅም እና ምንም ማብራሪያ የለኝም፣ የማየው እና የማልወደው እውነታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በዩክሬን ውስጥ ያለው ግጭት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የሰላም ተነሳሽነት ላይ ስለ ዩክሬን ምላሽ ሲጠየቁ፡ “የዩክሬን ሕዝብ አስባለሁ፣ ዛሬ ልንፈርድባቸው አይገባም። የዩክሬን ህዝብ ሰማዕት የሆኑ ህዝቦች ናቸው፣ በስታሊን ጊዜ በጣም ከባድ የሆኑ ስደትዎች ነበሩ። ሰማዕት የሆኑ ህዝቦች ናቸው። ስለዚህ እና ስለ አስከፊው ሰማዕትነት የመታሰቢያ መጽሐፍ አነበብኩ፣ በጣም አስፈሪ ነበር ... ብዙ መከራ የደረሰበት ህዝብ ነበር እና አሁን ምንም ነገር ያ አሰቃቂ ተግባር እንዲያንሰራራ ሊያደርግ ይችላል። ተረድቻቸዋለሁ እናም ፕሬዚዳንት ዘሌንስኪን በቫቲካን ተቀበልኩኝ፣ ይገባኛል ግን ሰላም ያስፈልጋል። ጦርነት አቁሙ! ለትንሽ ጊዜ ቆም አድርጉና የሰላም ስምምነትን ፈልጉ፣ ስምምነቶች ለዚህ ትክክለኛ መፍትሄ ናቸው። ለሁለቱም ተፋላሚዎች!” ሲሉ ተናግረዋል።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በሁለተኛው ቀን በሮም ከተማ ወደ ሩሲያ ኤምባሲ ሄድኩኝ ፣ እዚያ መሄድ እንዳለብኝ ተሰማኝ ፣ እናም ምንም ዓይነት ጥቅም ካለው ወደ ፑቲን ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ አልኩ ። እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሩሲያ ኤምባሲ ጋር ጥሩ ውይይት አደረግሁ። አንዳንድ እስረኞች መኖራቸውን ስሰማ ወደ ኤንባሲው ሂጄ  እንዲፈቱ በጠየኩት መሰረት አስፈትቻቸዋለሁ፤ አንዳንዶቹንም ከአዞቭ ነፃ አውጥተዋል። ባጭሩ ኤምባሲው ነፃ የምወጡትን ሰዎች በማስፈታት ረገድ ራሱን በሚገባ አቀናጅቷል። ንግግሩ ግን እዚያ ቆመ። በዚያ ቅጽበት ላቭሮቭ እንዲህ ሲል ጽፎልኛል: 'መምጣት እንደ ፈለክ ሰምቻለሁ አመሰግናለሁ ነገር ግን አስፈላጊ አይደለም' ብሎ ጽፎልኛል፣ ወደ ሁለቱም ቦታዎች መሄድ እፈልግ ነበር" ግን አልተቻለም ሲሉ ቅዱስነታቸው ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሴቶች

“እዚህ ቫቲካን ውስጥ በሥራ ቦታ ብዙ ሴቶች አሉ። ለምሳሌ፣ የቫቲካን ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ ሴት፣ መነኩሲት ናቸው፣ እና ገዥው የበለጠ ሁለንተናዊ ሚና አለው፣ ነገር ግን ኃላፊነት የተሰጣቸው እርሳቸውን ናቸው።  በኢኮኖሚው ምክር ቤት ውስጥ ስድስት ካርዲናሎች እና ስድስት ምዕመናን አሉ፣  ከእነዚህ ስድስት ምዕመናን መካከል አምስቱ ሴቶች ናቸው። ከዚያም የገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን ሕይወት የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሴት ናቸው፣ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገትን የሚመለከተው የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሴት ናቸው፥ ኤጲስ ቆጶሳትን የምመርጠው ኮሚሽኑ ውስጥ ሦስት ሴቶች አሉ፣ ምክንያቱም ሴቶች እኛ ያልተረዳናቸውን ነገሮች ስለሚረዱ፣ ሴቶች ለሁኔታው ልዩ የሆነ ደመ ነፍስ ስላላቸው እና እነርሱን ማሳተፍ ያስፈልጋል። ሴቶች በቤተክርስቲያን መደበኛ ሥራ ውስጥ መካተት አለባቸው ብዬ አምናለሁ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሴቶችን ሹመት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡- “በዚያ የነገረ መለኮት ችግር አለ እንጂ የአስተዳደር ችግር አይደለም። ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላሉ፤ ገዥም ሊኖርህ ይችላል፣ ምንም ችግር የለም። ነገር ግን በነገረ መለኮት አስተምህሮ ከአገልግሎት እይታ አንጻር ሲታይ የተለያዩ ነገሮች ናቸው-የቅዱስ ጴጥሮስ መርህ፣ እሱም የስልጣን ሁኔታን የምገልጸው መርህ፣  እና የማሪያን መርህ እሱም በጣም አስፈላጊ የሆነው ቤተክርስቲያን ሴት ስለሆነች፣ ቤተክርስቲያን ሙሽራ ናት፣ ቤተክርስቲያኗ ወንድ አይደለችም፣ ሴት ናት - ይህንን ለመረዳት የነገረ መለኮት አስተምህሮ ያስፈልጋል - እና የሴት ቤተክርስቲያን እና የሴቶች ኃይል በቤተክርስቲያን ውስጥ አለ።  ቤተክርስቲያን ከወንዶች አገልጋዮች የበለጠ ጠንካራ እና አስፈላጊ ነች። ማርያም ከጴጥሮስ ትበልጣለች ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ሴት ነች። ነገር ግን ይህንን ወደ ተግባራዊነት መቀነስ ከፈለግን ጣዕም እናጣለን” ብለዋል።

ሲኖዶስ እና በድንግልና መኖር

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲኖዶሳዊነት ላይ በተካሄደው ሲኖዶስ በኋላ ይፋ የሆነው ውጤት “አዎንታዊ” ነበር። "ስለ ሁሉም ነገር በፍጹም ነፃነት ተነጋገርን ነበር" ሲሉ ተናግረዋል። "ይህ ደግሞ የሚያምር ነገር ነው። እናም የመጨረሻውን ሰነድ ማዘጋጀት ተችሏል፣ በዚህ ሁለተኛ ክፍል ለሚቀጥለው የጥቅምት ክፍለ ጊዜ መጠናት አለበት፣ እንደ ቤተሰቡ ይህ ደግሞ በሁለት ደረጃዎች ያለው ሲኖዶስ ነው። በጉባኤው መጨረሻ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ይፈልጉት የነበረው የሲኖዶሳዊ ሥርዓት ላይ በትክክል እንደደረስን አምናለሁ ምክንያቱም የምሥራቃዊው ቤተ ክርስቲያን በሌላ በኩል ይዛ የቆየችው የምዕራቡ ዓለም ሲኖዶሳዊ ይዘት የምዕራብ ቤተክርስቲያን እንደጠፋ ስለተገነዘበ ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በቤተክርስቲያን ውስጥ እና ከውጪ የሚደርስ ግፍ

በቃለ ምልልሱ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ሥራ እየቀጠሉ መሆኑን አስረድተዋል። “ብዙ ‘ማጽዳት’ ተከናውኗል። ሁሉም የጥቃት ጉዳዮች ያሳስቧቸዋል እና እንዲያውም አንዳንዶቹ ከሮማ ኩሪያ አባረዋል። በዚህ ረገድ የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ደፋር ነበሩ። ያንን ችግር በራሳቸው እጅ ወስደው ብዙ እርምጃዎችን ወስደው እንዲጨርሱ ለእኔ አስረክበዋል። ይህ ይቀጥላል። በሕሊና፣ በፆታዊ ጥቃት ወይም በሌላ ማንኛውም ነገር በደል መታገስ የለበትም። ከወንጌል ጋር ይቃረናል፣ ወንጌል አገልግሎት እንጂ በደል መፈጸሚያ ነገር አይደለም እና ብዙ ኤጲስ ቆጶሳት ጾታዊ ጥቃትን በማጥናት ጥሩ ሥራ የሠሩ ነገር ግን ሌሎችንም [የጥቃት ዓይነቶችን] አይተናል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ምንም እንኳን ቤተክርስቲያን በሕጻናት ላይ የሚቃጣውን ጾታዊ ጥቃት በመዋጋት ረገድ ብዙ ብታደርግም “አሁንም ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ” አምነዋል።

በጣም አስቸጋሪው ጊዜ

ሊቀነ ጳጳሱ የጵጵስናቸው ጊዜ በጣም አስቸጋሪው ወቅት ምን እንደሆነ ሲጠየቁ፣ “ምናልባት የሶሪያን ጦርነት መቃወም ሲገባኝ ከባድ እና ከባድ ነበር… ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር፣ በጣም ከባድ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ነገር አልተለማመድኩም ነበር፣ እናም [እንዲሁም] ስህተት የመሥራት እና ጉዳት የማድረስ ፍራቻ ነበር። አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። አንዳንድ ቀላል ወይም በጣም ቀላል ያልሆኑ አፍታዎችም ነበሩ። ነገር ግን ጌታ ሁል ጊዜ ረድቶኛል፣ ወይም ቢያንስ ትዕግስት እንዲኖርኝ፣ ችግሮችን ለመፍታት በትዕግስት እንድጠብቅ ብርታት ሰጠኝ” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግሯል።

ምን እንደሚያስፈራቸው ሲጠየቁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ትንንሽ ፍርሃቶች አሉኝ። ይህ ወይም ያ ይከሰታል እያልኩኝ እጨነቃለሁ። በቅድስት ሀገር ያለው ጦርነት ያስፈራኛል። የእነዚህ ሰዎች ይህ ታሪክ እንዴት ያበቃል? ነገር ግን በጌታ ፊት ተፈትቷል። ፍርሃቱ ይጠፋል ማለት አይደለም። ነገር ግን እንደ ሰው ሆነው ይቀራሉ። መፍራት ጥሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ዱባይ ለ COP 28 እሄዳለሁ"

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ‘የፓርቲዎች ኮንፈረንስ’ ወይም በእንግሊዘኛው ምጻረ ቃል ‘COP’ በመባል የሚታወቀው ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የአለም መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እና የአገር አስተዳዳሪዎችን ያሰባስባል።

ቅዱስነታቸው በሚቀጥለው ወር በዱባይ ለሚካሄደው ስብሰባ ላይ ይገኛሉ ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “አዎ ዱባይ እሄዳለሁ። ከሕዳር 21 እስከ ሕዳር 23/2016 ዓ.ም በምካሄደው ስብሰባ ላይ ለመካፈል የምሄድ ይመስለኛል። እዚያ ለሦስት ቀናት እቆያለሁ። አስታውሳለሁ ወደ ስትራስቦርግ፣ ወደ አውሮፓ ፓርላማ በሄድኩበት ጊዜ፣ እና ፕሬዚዳንት ሆላንድ እኔን ለመቀበል የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሴጎሌን ሮያልን ልከውኛል። እሷም “በአየር ንበረ ለውጥ ላይ ይሆነ ነገር እያዘጋጀህ ነው? ብላ ጠይቃኝ ነበር፣ ከፓሪስ ስብሰባ በፊት ማድረግ አለብህ’ አለችኝ። ከእዚያም ለአንዳንድ ሳይንቲስቶችን ደወልኩ፣ እነርሱ በፍጥነት ተንቀሳቅሰዋል። በላቲን ቋንቋ 'Laudato sí' (ውዳሴ ለአንተ ይሁን) የተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት ይፋ ሆነ፣ ከፓሪስ ጉባሄ በፊት ይፋ ሆነ። እናም በፓሪስ የተደረገው ስብሰባ ከሁሉም የበለጠ ጥሩ ነበር። ከፓሪስ በኋላ፣ ሁሉም ወደ ኋላ ሄደ፣ እናም በዚህ ውስጥ ወደፊት ለመራመድ ድፍረት ይጠይቃል” ሲሉ ቅዱስነታቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

እምነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እምነዎ ተናውጦ ያውቃል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እምነትን በማጣት ረገድ ይህ አለተፈጠረም፣ ነገር ግን ስሜቱ ባለመሰማቱ እና በጨለማ መንገዶች ውስጥ የምሄድ ከመሰለኝ -ጌታ የት አለ? - እያልኩኝ በመጠየቅ ጌታ እንደተደበቀ እንደ ሆነ ይሰማኛል፣ እሱ የት ነው ያለው? ወይም ከእርሱ ርቄ ወደ ኋላ የምሄድ ይመስለኛል። ጌታ ሆይ ወዴት ነህ? እያልኩኝ እጠይቃለሁ፥ እናም ለምን ይህን አታስተካክለውም? እያልኩኝም እጠይቃለሁ፣ ጌታ በውስጤ ሲያናግረኝ ይሰማኛል፣ ምክንያቱም እኔ አስማተኛ ዘንግ የለኝም ይለኛል። ጌታ ማንድራክ [አስማተኛው] አይደለም፣ አይ። እሱ ሌላ ነገር ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ "ከማራዶና እና ከሜሲ መካከል ፔሌን እመርጣለሁ" አሉ

በመጨረሻም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከሁለቱ ታላላቅ የአርጀንቲና እግር ኳስ ተጫዋቾች ማራዶና ወይም ሜሲ የትኛውን እንደሚመርጡ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ሦስተኛውን እላለሁ፡ ፔሌን” እመርጣለሁ በማለት መልሰዋል።

02 November 2023, 19:01