ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመጡ ልዑካንን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የመጡ ልዑካንን በቫቲካን ተቀብለው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ እምነት እና አገልግሎት በቅርብ የተሳሰሩ መሆናቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ በዱባይ ከሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ብለው፥በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኝ የዱባይ ጉሩ ናናክ ዳርባር ሲክ ልዑካን ቡድን አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። በመልዕክታቸው አባላቱ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚያደርስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነውን አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ በማለት ምክራቸውን ለግሠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ውስጥ ከሚገኝ የጉሩ ናናክ ዳርባር ሲክ መስጊድ እና ከሌሎች አገራት መጥተው በሮም ስብሰባቸውን ያካሄዱ ልዑካን ቡድን አባላት ቅዳሜ ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር፥ “እምነት እና አገልግሎት በቅርበት የተሳሰሩ እና ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ የሚያደርጉ ናቸው” በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ላይ ለመገኘት፥ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በመጭው ታኅሳስ ወር መጀመሪያ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ለመጓዝ ዕቅድ የያዙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት ወር 2019 ዓ. ም. በሃይማኖት መሪዎች መካከል በተካሄደው ጉባኤ ላይ ለመገኘት ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ተጉዘው የሰባዓዊ ወንድማማችነት እና የአብሮነት ሠነድ ፈርመው ከተመለሱት ጋር ይህ ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን ይጠበቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ የመጀመሪያው ር. ሊ. ጳጳሳት እንደሚሆኑ ታውቋል።

በእምነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት

ቅዳሜ ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. ጠዋት የልዑካን ቡድኑን በቫቲካን የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤታቸው በሆኑ አገራት ውስጥ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች በሚያቀርቡት በእምነት ላይ በተመሠረተ አገልግሎት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉት አገልግሎቶች በእምነት ለመኖር እና ለኅብረተሰቡ መልካም አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ይመሰክራሉ ብለው፥ በተለይም ራሳቸውን ከማኅበረሰቡ ጋር ለማዋሃድ በሚፈልጉበት ወቅት በማንነታቸው ጸንተው እንዲቆዩ አሳስበዋል።

በሰዎች መካከል እርስ በርስ የመገናኛ ድልድይን ለመገንባት፣ ድሆችን፣ ችግረኞችን እና ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን ለማገልገል ላደረጉት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸው፥ ይህን በማድረጋቸው ሕይወታቸው የሚባረክበትን እና የሚበለጽግበትን መንገድ እንደሚገነዘቡ ገልጸው፥ "እንደምታውቁት ሁሉ እምነት እና አገልግሎት በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው” በማለት አስረድተዋል።

ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ እውነተኛ መንገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፣ “የልኡካኑ ቅዱስ መጽሐፍ ጉሩ ግራንት ሳሂብ እንደሚናገረው፥ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደው እውነተኛው መንገድ የሚገኘው ለሰዎች በሚሰጥ አገልግሎት ላይ ነው” በማለት ተናግረው፥ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ፥ “ተርቤ አብልታችሁኛል፣ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፣ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፣ ታርዤ አልብሳችሁኛል፣ ታምሜ ጠይቃችሁኛል፣ ታስሬ ጐብኝታችሁኛል (ማቴ. 25፡35-36) የሚለውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል አስታውሰዋል።  

በአገልግሎታቸው መባረክ

"በመካከላችን ድሆች ለሆኑት እና በኅብረተሰቡ ለተገለሉት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎት መስጠት፥ የራሳችንን ትንሽነት እንድንገነዘብ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንድንቀርብ ያደርገናል" ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለልዑካን ቡድኑ ቡራኬያቸውን ከመስጠታቸው በፊት ባቀረቡት ጸሎት፥ “አገልግሎት ዘወትር የአኗኗር ዘይቤያቸው ሆኖ እንዲቀጥል፥ ወንድማማችነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትህን እና የሰላም መንፈስን በማጎልበት፥ ለሚያገለግሏቸው ሁሉ በረከት ይሁናቸው!” በማለት ጸሎታቸውን አሳርገዋል።

13 November 2023, 15:17