ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአውሮፓ የወላጆች ማኅበር (EPA) ተወካዮችን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአውሮፓ የወላጆች ማኅበር (EPA) ተወካዮችን በቫቲካን ሲቀበሉ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ወላጆች ልጆቻቸውን በነፃነት የማስተማር መብት ያላቸው መሆኑን አረጋገጡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የአውሮፓ የወላጆች ማኅበር (EPA) ተወካዮችን ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ ወላጆች ልጆቻቸውን በማስተማር ረገድ የሚጫወቱትን ሚና እና የወደፊት ትውልዶችን ለማስተማር ያላቸው የጋራ ቁርጠኝነት አስፈላጊነት በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወላጆች እምነታቸውን ተከትለው ልጆቻቸውን የማሳደግ እና የማስተማር መብታቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ በየትኛውም ዘርፍ በተለይም በትምህርት ቤት ከእምነታቸው እና ከእሴቶቻቸው ጋር የሚቃረኑ ትምህርቶችን ለመቅሰም መገደድ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

ር.. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከጥቅምት 30 እስከ ኅዳር 1/2016 ዓ. ም. ድረስ በሮም በተካሄደው የአውሮፓ የወላጆች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ለተሳተፉት አባላት ባደረጉት ንግግር፥ በማህበራዊ ሥርዓት ውስጥ የወላጆች መሠረታዊ ሚና በየደረጃው እውቅና ሊሰጠው ይገባል ሲል አፅንዖት ሰጥተዋል።

የጊዜው የባህል አውድ የሚጠይቀው ተግባር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወላጆች የማስተማር ተልዕኮ በጣም አስፈላጊ ተግባር እንደሆነ ጠቁመው፥ በተለይም በዛሬው የባህል አውድ ውስጥ ቢያንስ በአውሮፓ የሥነ ምግባር ርዕሠ ጉዳይ እና በፍቅረ ንዋይ ዘርፍ ተለይቶ እንደሚታወቅ አስረድተዋል።

“ወላጆች ለልጆቻቸው እንደ ጋብቻ እና የቤተሰብ አስፈላጊነት ወይም ልጆችን የእግዚአብሔር ስጦታ አድርገው የመቀበላቸውን ውሳኔ የመሳሰሉ ምርጫዎችን እና የሥነ-ምግባር እሴቶች መልካምነትን ለልጆቻቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል” ብለዋል።

እነዚህ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ወላጆች የትምህርታዊ ተልዕኮ ፍላጎት እንዲኖራቸው መርዳት፣ መደጋገፍ እና ማበረታታት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፥ ይህም ልጆቻቸውን ፍጹም ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለማስተማር ያግዛል በማለት ተናግረዋል።

ጤናማ ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚያግዝ ወሳኝ አስተዋጽዖ

የወላጆች የማስተማር ተልዕኮ ልጆች የሕይወትን ውበት ሲገነዘቡ ውጤታማ እንደሚሆን የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በሕይወት ጉዞ ወቅት በራስ መተማመንን እንደሚያሳድግ እና ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለንን ታላቅ ፍቅር የሚያስገነዝበን መሆኑን ተናግረዋል። ሰው የመሆናችን መሠረት የእግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ከተገነዘብን፥ የሕይወት መልካምነትን፣ ልጅ የመውለድ አስደሳችነትን እና የመውደድ ጥሩነትን በግልጽ እናያለን ብለው፥ “የእግዚአብሔርን ፍቅር ያወቁ ነፃ እና ለጋስ ሰዎችን ማፍራት፥ በስጦታ የተቀበሉትን ለሌሎች በነጻ መስጠት የወላጆች ከፍተኛ የማስተማር ተልዕኮ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

እነዚህ በሙሉ የጤናማ ማኅበረሰብ መሠረቶች እንደሆኑ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ወላጆች እሴቶችን በማስተላለፍ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ እንደሆነ ተናግረው፥ “በሥራ መስክ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች እና በማኅበራዊ አንድነት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ በማድረግ ጠንካራ ዜጎችን መፍጠር የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ልጅን ሥነ-ምግባርን በማስተማር ማሳደግ ለኅብረተሰቡ እውነተኛ አስተዋፅዖን እንደሚያበረክት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ አንድ ወጣት ከሌሎች ጋር ክብርን የተላበሰ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረው ማሰልጠን ማለት፥ ለጋራ ጥቅም ሲባል የኃላፊነት ግዴታን ለመወጣት ዝግጁ መሆን እና ለጋራ ግብ መስዋዕትነት መክፈል ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ከሌለ ልጆች ከሌሎች ተነጥለው ብቻቸው እንደሚያድጉ፥ የጋራ ራዕይ እንደሌላቸው እና የራሳቸውን ፍላጎት እንደ ፍፁም እሴት አድርገው የመቁጠር ልማድ እንደሚኖራቸው ገልጸው፥ ውጤቱም ኅብረተሰብን በማፍረስ እና ድህነት በመጨመር ሰብዓዊነትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚያዳክም አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን ወላጆችን በመደገፍ ያላት ቁርጠኝነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወላጆች እምነታቸውን እና እሴቶቻቸውን ለልጆቻቸው የማስተማር መብታቸውን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ ቤተ ክርስቲያንም ቤተሰቦችን በጥረታቸው ለመደገፍ እና ለመርዳት ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳካት ከሚመለከታቸው ተቋማት ሁሉ ጋር በቅርበት መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ወጣቶችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ ቁርጠኝነትን ለማጠናከር፥ ዓለም አቀፉ የትምህርት ማዕቀፍ በቤተሰብ እና በተለያዩ ግንኙነቶች ላይ ማተኮር እንዲችል በባህላዊ፣ ትምህርታዊ፣ ተቋማዊ እና ሐዋርያዊ ተዋናዮች ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በትምህርት እና በቤተሰብ ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀፍ

የእነዚህ ውጥኖች ዓላማ፣ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ዓለምን እያዳከሙ ያሉትን በርካታ እንቅፋቶችን ማሸነፍ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፥ በትምህርት እና ከሰው ዕውቀት በላይ በሆነው ጥበብ መካከል ያለው ግንኙነት መቋረጥ፥ የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነት መፍረስ እና ማኅብረሰብን ከቤተሰብ መነጠል በሰዎች መካከል የኑሮ አለመመጣጠንን በመፍጠር ወደ አዲስ የድህነት ዓይነቶች እንደሚመራ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የአውሮፓ የወላጆች ማኅበር፥ የወንጌል ምስክርነት በሆነው በቅዱሳን ወላጆች በቅድስት ማርያም እና በቅዱስ ዮሴፍ በመታገዝ የማያቋርጥ መነሳሳትን እና ድጋፍን በማሳየት በተስፋ እንዲራመድ ብርተታትን ተመኝተዋል።

 

13 November 2023, 15:26