ፈልግ

2023.11.07 Meeting Cop28UAE

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፡ ለ COP28 ጸሎት እንደሚያደርጉ እና ላውዳቶ ሲ' የድርጊት መድረክ ምስጋና አቀረቡ!

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ‘የፓርቲዎች ኮንፈረንስ’ ወይም በእንግሊዘኛው ምጻረ ቃል ‘COP’ በመባል የሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል የአለም መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እና የአገር አስተዳዳሪዎችን ያሰባስባል። ተደራዳሪዎቹ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (ዩኤንኤፍሲሲሲ)፣ የኪዮቶ ፕሮቶኮል እና/ወይም የፓሪስ ስምምነትን የፈረሙ መንግስታትን ያጠቃልላል። በሲቪል ማህበረሰብ፣ በግሉ ዘርፍ፣ በአለም አቀፍ ድርጅቶች እና በመገናኛ ብዙሃን በሺዎች የሚቆጠሩ ተወካዮች በተገኙበት የሚከናወን ኮንፈረንስ ነው COP።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 02/2016 ዓ.ም እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከምዕመናን ጋር ካደረጉ በኋላ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልዕክት ለአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤን ለመስጠት እና ለማበረታታት ዓላማ ላለው በላቲን ቋንቋ ‘ላውዳቶ ሲ' በአማርኛው “ውዳሴ ለአንተ ይሁን” የተሰኘው እርሳቸው ይፋ ያደረጉት ጳጳሳዊ መልዕክት የድርጊት መርሃግብር መድረክ የሁለት ዓመት ዝክረ በዓል መከበሩን የገለጹ ሲሆን እናም በዱባይ የሚካሄደውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሁሉም በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ ጠይቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ እለት እንደ ተናገሩት ከሆነ ከሁለት አመት በፊት የላውዳቶ ሲ የድርጊት መርሃ ግብር መድረክ ለአካባቢ ጥበቃ ጠቃሚ መሳሪያዎችን የሚያቀርብ የጋራ ቤታችን እንድንከባከብ የሚያነሳሳን መሆኑን አስታውሰዋል። በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልማት አገልግሎት በሚሰጠው ጽሕፈት ቤት ተነሳሽነት በሚከናወነው አውደ ርዕይ ቤተክርስቲያን ለሥነ-ምህዳር ቀውስ ተጨባጭ ምላሾችን እንድታዳብር የሚያግዝ የጋራ ቦታ ይሰጣታል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላውዳቶ ሲ በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክት እና በተለይም በቅርቡ በላቲን ቋንቋ “Laudate Deum” ‘እግዚአብሔርን አወድሱት’ በተሰኘው የአከባቢ ጥበቃን በተመለከተ ይፋ ያደረጉት ጳጳሳዊ መልእክት ይገኝበታል።  

የላውዳቶ ሲ የድርጊት መርሃ ግብር መድረክ መመሪያ ይሰጣል፣ ድርጊቶችን ይጠቁማል እንዲሁም ለቤተሰቦች፣ ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለሀገረ ስብከት፣ ለትምህርት ተቋማት፣ ለጤና ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ ሰራተኞች፣ የንግድ ድርጅቶች እና የሃይማኖት ማህበረሰቦች የጋራ ቤታችንን ለመንከባከብ ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ ይሰጣል።

"በዚህ ተነሳሽነት የተቀላቀሉትን አመሰግናለሁ እናም በሥነ-ምህዳር ለውጥ ጎዳና ላይ እንዲቀጥሉ አበረታታቸዋለሁ" ሲሉ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ገልጸዋል።

በመቀጠልም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "በቅርቡ በዱባይ ለሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ COP28 ጸሎት እናድርግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ COP28 የአለም መሪዎችን እ.አ.አ ከኅዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 ድረስ በዱባይ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመሰብሰብ የአለም ሙቀት መጨመርን ለመገደብ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ተፅእኖዎች ለመቀነስ በፖሊሲዎች ላይ ስምምነት ይደረግ ዘንድ እንጸልይ” ማለታቸው ተገልጿል።

በጉባኤው ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን ቅዱስነታቸው እ.አ.አ በታህሳስ 2/2023 ቀን ንግግር ያደርጋሉ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እ.አ.አ ከታህሳስ 1 እስከ ታህሳስ 3 ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ይጓዛሉ። በ COP28 ላይ ከመገኘት በተጨማሪ የግል የሁለትዮሽ ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ፣ እናም የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ተጨባጭ ስራዎችን ለማነሳሳት የተነደፈውን "የእምነት ድንኳን" ኤግዚቢሽን ላይ እንደ ሚሳተፉም ይጠበቃል።

13 November 2023, 14:37