ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያኖች በተሰጣቸው ስጦታ መጠን ወደ ድሆች እንዲቀርቡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ኅዳር 9/2016 ዓ. ም. ለሰባተኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደርጃ የተከበረውን የድሆች ሳምንት ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በተከፋፈለ እና በተጨነቀ ዓለማች ውስጥ ምዕመናን ራሳቸውን ለሌሎች በስጦታነት እንዲያቀርቡ ጠይቀው፥ በዓለማችን ውስጥ በርካታ የተጨቆኑትን፣ የደከሙትን፣ የተገለሉትን፣ በጦርነት የተጎዱትን እና የትውልድ አገራችን ጥለው በመሰደድ ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡ፥ የዕለት እንጀራ የሌላቸውን፣ ሥራ አጥናእና ተስፋ የቆረጡትን ሰዎች ልናስታወሳቸው ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ድህነት፥ የወንጌልን የምስራች በማዳመጥ ምላሽ ልንሰጠው የሚገባን አሳፋሪ ክስተት ነው” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያኖች ያላቸውን በቸርነት ለሌሎች ማካፈልን እና ፍቅርን እንድናበዛ ቅዱስ ወንጌል እንደሚያሳስበን ገልጸው፥ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የድሆች ሳምንት ምክንያት በማድረግ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ራስ ወዳድነትን በመታገል ብዙ ዓይነት ድህነቶችን መቃወም እንደሚገባ ተማጽነው፥ “እግዚአብሔር የሰጠንን ጸጋ እና የእርሱን ጥሪ መደበቅ የለብንም ብለው፥ እግዚአብሔርም መጠየቁ አይቀርም” ብለዋል።

በዓለማችን ውስጥ የሚታዩ ብዙ ቁሳዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ድህነቶችን እናስብ ብለው፥ በከተሞቻችን ውስጥ የሠፈሩ የሕሊና ቁስለኞችን፣ ቤት የደበቃቸው ድሆችን፣ በሕመም ድምጻቸው የታፈነባቸውን፣ በማኅበረሰቡ ግድ የለሽነት የተረሱትን እና የተገለሉትን ልናስታውሳቸው እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

“ስለ ድህነት ስናስብ ትሑትነቱን መርሳት ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ብዙን ጊዜ ድህነት ተደብቆ የማይታይ በመሆኑ ሄደን በድፍረት መፈለግ አለብን ብለዋል። የተጨቆኑትን፣ የደከሙን፣ የተገለሉትን፣ የጦርነት ሰለባ የሆኑትን እና ትውልድ አገራቸው ጥለው በመሸሽ ሕይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡትን ልናስታውሳቸው እንደሚገባ፥ የዕለት እንጀራ የሌላቸውን፣ ሥራ አጦችን እና ተስፋ የቆረጡትን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለውናል። የድኅነት ዓይነቶች ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ሳይሆኑ ብዙ እንደሆኑ እና ድሆችም ብዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ራስን በስጦታነት መስጠት ወይም ካልሆነ በራስ ወዳድነት መኖር

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ አምስት ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ቃለ ም ዕዳናቸውን ያካፈሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ በድህነት ሕይወት በየቀኑ የሚሰቃዩ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን የተነፈጉ እና በሕይወት የሚያቆዩዋቸው መሠረታዊ ነገሮች የሌላቸው እንደሆኑ ተመልክቷል። በማቴ. 25:14-30 ላይ የተጻፈውን የመክሊቶችን ምሳሌ ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መከተል የሚገባን ሁለት መንገዶች እንዳሉ በመጥቀስ፣ የመጀመሪያው “የኢየሱስ ጉዞ” እንደሆነ፥ ጌታው ተለይቷቸው ከመሄዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ንብረቱን እንደሰጣቸው ሁሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ አባቱ ከመመለሱ በፊት መንፈስ ቅዱስን ለሰዎች በስጦታ በመስጠት፥ በዕለት ተዕለት በሚፈጽሙት የግል ተልዕኮ፣ በዓለም ላይ፣ በማኅበረሰብ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሥራ እንዲቀጥሉ ማዘዛቸውን አስታውሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ የተቀበለውን የአገልግሎት ሥልጣን ለራሱ ሳያደርግ ነገር ግን ለሌሎች ሰዎች ጥቅም እንዳዋለው እና ወደ እግዚአብሔር አባቱ ዘንድ ከመመለሱ በፊት በዓለም ላይ ያደረገውን ጉዞ በተግባር ማሳየቱን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

በምሳሌው ላይ እንደተገልጸው፥ ከዕለታት አንድ ቀን ጌታው ወደ አገልጋዮቹ ሲመለስ፥ ከእነርሱ ጋር ሂሳብ ማወራረድ እንደፈለገ ተናግረው፥ ይህ ሁለተኛው መንገድ ወደ እራሳችን የሕይወት ጉዞ እንደሚወስደን ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመገናኘት ወደ ዘለዓለማዊ የሕይወት ደስታ እንዲገባ የሚያደርገን መሆኑን አስረድተዋል።

በሕይወታችን የትኛውን መንገድ እንከተላለን? ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱን ስጦታ ያደረገበትን ወይስ የራስ ወዳድነት መንገድ? ለሌሎችን ክፍት የሆኑ ወይስ የተዘጉ እጆች አሉን? በማለት ጠይቀዋል። ምሳሌው እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዕውቀትን እንደተቀበልን ይነግረናል ብለው፥ ይህም በተለምዶ አነጋገር እንዳንታለል፥ የምንናገረው ስለ ግል ችሎታ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ዘንድ ከመመለሱ በፊት ስለተወን ጸጋዎች መሆኑን አስረድተዋል።

ክርስቲያኖች ሃላፊነትን መውሰድ እናውቅበታልን

ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለሰዎች የተወልን ታላቁ ሃብት፥ የሕይወታችን መሠረት እና የጉዞአችን ጥንካሬ የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነው ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው፥ ምንን መምረጥ እንደሚገባ መጠቀሱን ገልጸዋል። ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን የጸጋ ሃብት በማሳደግ ሕይወትን ለሌሎች ፍቅር መስዋዕት ማድረግ ወይም በተሳሳተ ልብ በፍርሃት ተገድበን ያለንን ሃብት ለሌሎች ሳንሰጥ ድብቀን ለጥቅማችን እና ለምቾታችን ብቻ እናውለዋለን ብለዋል።

እንደ ክርስቲያን እራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፡- በሕይወታችን ውስጥ ስጋት እየፈጠርን እንገኛለን? እምነታችንን ለአደጋ እያጋለጥን እንገኛለን? በአደጋ ወይም በፍርሃት ወስጥ እንደምንወድቅ እናውቃለን? በማለት ቅዱስነታቸው ለምእመናናኑ ግልጽ ጥያቄ አቅርበዋል።

እምነት ከመሬት በታች ተደብቆ መኖር የለበትም

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመክሊቶችን ምሳሌ ለምእመናኑ በማስታወስ፥ የሕይወት ጉዞን በምን መንፈስ እየተጋፈጡት እንደሆነ ለማረጋገጥ ጠይቀው፥ የፍቅር ስጦታን ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሰዎች እራሳቸውን ለሌሎች ስጦታ አድርገው እንዲያቀርቡ የተጠሩ መሆናቸውን ተናግረው፥ በአካባቢያችን ፍቅርን ካላሳደግን ሕይወት በጨለማ ውስጥ እንደምትሞት እና የተቀበልናቸው መክሊቶች ሕልውናም ከመሬት በታች እንደሚቀር በመግለጽ፥ በማቴ. 2530 ላይ፥ “የማይረባውን አገልጋይ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያ ለቅሶ እና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” የሚለውን ጥቅስ አስታውሰዋል።

“የስንቱ ክርስቲያን እምነት ከመሬት በታች ተቀብሮ ይገኛ?” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የፍቅር፣ የምህረት፣ የርህራሄ፣ የደስታን እና የተስፋ ስጦታዎችን ከሌሎች ጋር ለመካፈል የተጠሩ በመሆናቸው፥ በተሰጣቸው ስጦታ እና በአደራ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት በቸርነት ወደ ድሆች ሊቀርቡ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

 

20 November 2023, 16:58