ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኖትርዳም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶችን በቫቲካን ተቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኖትርዳም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶችን በቫቲካን ተቀበሉ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለኖትርዳም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶች ምስጋና አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ 25ኛውን የጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤያቸውን በሮም ለማካሄድ የመጡትን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ኖትርዳም” እህቶችን ሰኞ ኅዳር 3/2016 ዓ. ም. በቫቲካን አቀባበል አድርገውላቸዋል። የእህቶች ማኅበር በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር ሥራው ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች እንዲታይ ላደረገው አገልግሎቱ አመስግነዋል። ቅዱስነታቸው ለማኅበሩ አባላት ባሰሙት ንግግር፥ ለቤተ ክርስቲያን በሚያበረክቱት አገልግሎት የወንጌልን ደስታ በፍሬያማነት በመመስከር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሌሎች እንዲታይ ማድረግን እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማኅበራቸውን 25ኛ ጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤያቸውን በሮም ላካሄዱት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ኖትርዳም” እህቶች፥ ሰኞ ኅዳር 3/2016 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት የማበርታቻ መልዕክት፥ ገዳማውያቱ ለቤተ ክርስቲያን በተለይም በትምህርት እና በመንፈሳዊ ዘርፍ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ በሆነች በብጽዕት ቴሬዛ፥ ጀርመን ውስጥ ባቫርያ ግዛት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1833 ዓ. ም. የተመሠረተው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ኖትርዳም” የትምህርት ቤት እህቶች ዓለም አቀፍ ማኅበር (SSND) በአሁኑ ወቅት ወደ 2,000 የሚጠጉ ገዳማውያት እህቶች እንዳሉት ታውቋል። ማኅበሩ በአምስቱም አህጉራት በሚገኙ 30 አገራት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ አገልግሎታቸውም የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየሰበኩ በኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ ተካፋይ መሆን ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማኅበሩን ዓላማ በማስታወስ ለገዳማውያቱ ባሰሙት ንግግር፥ የማኅበራቸው መሥራች በሆነች የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ ብጽዕት ቴሬዛ ትሩፋት በመነሳሳት አገልግሎታቸውን እንደምትቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የብጽዕት ቴሬዛ ብጽዕና መታሰቢያ በዓል የሚከበረው የማኅበራቸው ጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤ በሚገባደድበት ዓርብ ኅዳር 7/2016 ዓ. ም. መሆኑን አስታውሰው፥ ዕለቱ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ባለፈው ጊዜ ለሰጣቸው እና አሁን ለሚሰጣቸው በረከት የሚያመሰግኑበት እና የጉባኤያቸውን የወደፊት ጉዞ ለይተው የሚያቁበት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ ብጽዕት ቴሬዛ

“የብጽዕት ቴሬዛ ሕይወት የሚለውጥ የእምነት ኃይል፣ አዳዲስ መንገዶችን ለመገንባት ድፍረትን የሚሰጥ እና ወጣትቶችን ለማስተማር ያለውን ቁርጠኝነት የሚገልጽ ነበር” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል። “የእርሷ ራዕይ፣ ሙሉ የሚባል፣ መንፈስን የሚንከባከብ፣ ሩህሩህ፣ ኃላፊነት የሚሰማው እና ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ባደረጉ አባላት በኩል የትምህርት እውቀት ማስተላለፍን ያካትታል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ ብጽዕት ቴሬዛ ከዚህም በላይ ቅዱስ ቁርባንን የማኅበሩ መሠረት በማድረግ የድህነት ሕይወትን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለማቅረብ መወሰኗን ገልጸው፥ የማኅበሩ አባላትም የእርሷን ፈለግ በመከተላቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የአኗኗሩ እና የተግባር መንገድ

የማኅበሩ ጽኑ መሠረት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶች ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ወንጌልን ለመመስከር፣ በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር ሥራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሌሎች እንዲታይ ማድረጉንም ተናግረዋል።

እህቶች ቅዱስ ወንጌልን ለረጅም ጊዜ ሲመሰክሩ በመቆየታቸው አመስግነው፥ የምንኩስና ሕይወት ትንቢታዊ ገጽታን ተቀብለው የኢየሱስ ክርስቶስን የአኗኗር ዘይቤ ሕያው መታሰቢያ በመሆን፥ ይህም ከእግዚአብሔር አብ ጋር ቃል ሥጋ ሆኖ በተገናኘበት መንገድ አገልግሎታችሁን ለሰው ልጅ በሙሉ ለማቅረብ መወሰናችሁ ለጌታ ራሳችሁን በስጦታ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእርሱ ስም ለማገልገል የመብቃታችሁ ምልክት ነው” ብለዋል።

ደፋር ምስክሮች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመነኮሳቱ የሚያስተላልፉትን መልዕክት በመቀጠል፥ በብዙዎች መካከል መለያየት ባለበት በዚህ ወቅት በኅብረት ደፋር የወንጌል ምስክሮች ሆነው እንዲቀጥሉ አደራ ብለው፥ የወንጌል ደስታን በተለይም በትምህርታዊ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዴት በብቃት መመሥከር እንደሚችሉ መገንዘብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ ገዳማውያቱ ላደረጉት ጉብኝት እና ጸሎት አመስግነው፥ የቤተ ክርስቲያን እናት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትጠብቃቸው እና እንድትረዳቸው፥ እንዲሁም የመንገዳቸው ትክክለኛ መሪ እንድትሆናቸው ጸሎታቸውን አቅርበው፥ በቫቲካን ለተኙት እና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት እህቶች በሙሉ ልባዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋቸዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኖትርዳም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኖትርዳም የትምህርት ቤት አገልጋይ እህቶችን በቫቲካን ሲቀበሉ
14 November 2023, 16:25