ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስን በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መካከል ሲያገኟቸው  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስን በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መካከል ሲያገኟቸው  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስ ለጻፉት መጽሐፍ የመቅድም ጽሑፋቸውን አበረከቱ

በቱርክ የጴርጋሞን ከተማ ፓትርያርክ እና የነገረ-መለኮት ምሁር የነበሩት ሟቹ አቡነ ጆን ዚዚየላስ “መጪው ጊዜን ማስታወስ” በሚል ርዕሥ ለጻፉት መጽሐፍ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመቅድም ጽሑፍ አበርክተዋል። ፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ መጽሐፋቸውን ማግኘቴ በመካከላችን በተመሠረተው ወዳጅነት የተነሳ ዛሬም እጃቸውን የመጨበጥ ያህል ይሰማኛል ብለው፥ ከህልፈታቸው በኋላ ለንባብ የበቃው መጽሐፋቸው ርዕሡ እንደሚነግረን፥ እግዚአብሔር ከሚያዘጋጀው መጪው ጊዜ እንደሚፈልቅ ምልክት ሆኖኛል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ለማክበር ወደ ርፕም የመጡትን የቁስጥንጥንያው ፓትርያርክ ልዑካንን በተቀበሏቸው ወቅት እንደ ነበር አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በጊዜው ያደረጉትን ውይይት ሲያስታውሱ፥ “ከጳጳሳት አንድነት እና ከሲኖዶሳዊነት ወግ ጋር በተያያዘ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ምን ያህል መማር እንዳለብን ያረጋገጥኩበት ውይይት ነበር” ብለዋል።

ከፓትርያርክ ጆን ዚዚየላስ ጋር በተከታታይ ባደረጓቸው ስብሰባዎች፣ መጽሐፍ ለማሳተም ዓመታትን ሲጠብቁት ስለ ነበረው የትንሳኤ-ሙታን ነገረ-መለኮት አስተምህሮ ርዕሥን ብዙ ጊዜ ያነሱ እንደ ነበር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስታውሰው፥ ስለ ክርስቲያኖች አንድነት በሚጸልዩበት እና በሚያሰላስሉበት ጊዜም እውነታውን ሲናገሩ፥ “ይህ የሚሆነው በዘመናት መጨረሻ ላይ ብቻ ነው” ይሉ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን እስከዚያው ድረስ በተስፋ ላይ ተስፋ በማድረግ የሚቻለውን ሁሉ በጋራ ማድረግን መቀጠል እንደሚገባ የተናገሩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መጨረሻ ላይ ስለሚሳካ ጥረታችንን በቸልተኝነት መመልከት አይገባም ብለው፥ የፍጥረት ሁሉ ምክንያት የሆነው መጪው ጊዜ ከታሪክ የሚመጣ ሳይሆን ወደ ታሪክ የሚያደርሰን መሆኑን ማመን አለብን ብለዋል። ይህም የጉዞአችን ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን በትንሳኤው እና በሕይወታችን ውስጥ ያሉ አዳዲስ ውበቶችን የሚያስታውሰን መንፈስ ቅዱስ ነው ብለዋል።

ከቀደሙት ስህተቶች በላይ እስረኞች የሚያደርገን ያለፈ ታሪክ ዕይታችን፣ ያልተሳኩ ሙከራዎች፣ ጠቃሚ ያልሆኑ አሉታዊ ምክንያቶች እና አለመተማመን ስለሆኑ ልናስወግዳቸው ይገባል ብለዋል። ወደ ኋላ የምንመለከት ከሆነ በአሉታዊነት ከመባዘን በተጨማሪ የክርስቲያኖችን አንድነት በቅንነት የመፈለግ ጥረታችን በልዩ መንገድ ይደናቀፋል ብለዋል።

የክርስቲያናዊ ባሕላችን እሴቶች በኅብረት ለመጓዝ መንገድ ከመክፈት ይልቅ በምትኩ አጥር የምናቆም ከሆነ፥ ይህ ማለት እሴቶቻችንን የምንተረጉምበት መንገድ ተሳስተን ወይም የፍርሃት እስረኞች በመሆን የራሳችንን ደህንነት ብቻ ለማስጥበቅ የምንሞክር ከሆነ እምነትን ወደ ርዕዮተ ዓለማዊነት ከመቀየር አደጋ ጋር፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁል ጊዜ ሕይወት እና መንገድ፣ የሰላም መንገድ (ዮሐ. 14: 6)፣ የሕብረት እንጀራ እና የአንድነት ምንጭ የሆነበትን እውነት እንረሳለን ብለዋል።

ትንሳኤ-ሙታን የዕለት ተዕለት ሕይወታችን በር እንደሚያንኳኳ፣ ትብብራችንን እንደሚፈልግ፣ ሰንሰለቱን እንደሚፈታ እና ወደ መልካም ጎዳና ለመድረስ የሚደረገውን ጉዞ ነፃ እንደሚያደርገው የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጆን ዚዚየላስ በመጽሐፋቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ስለ መጪው ጊዜ በማሰብ፥ በመጠባበቅ ላይ እንደምትገኝ እና በቅዱስ ቁርባን ቀኖና ውስጥ የሚገኘውን ሥነ-መለኮት በማስታወስ ጽሑፋቸውን እንዳጠናቀቁ ተናግረዋል።

በመጽሐፈ መዝሙር ምዕ. 108:2 ላይ፥ “አምላኬ ሆይ ልቤ ጽኑ ነው፥ እቀኛለሁ፥ በክብሬም እዘምራለሁ” የሚለውን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ጥቅስ ሁሉንም የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር የመጪው ጊዜ ፍላጎት መጮህ እንደሚገባ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረው፥ በውስጣችን ያለውን የብርሃን ጮራ እና ተስፋ ማንቃት እንደሚገባ አሳስበዋል። በእርግጥም እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር እርግጠኞች የምንሆንበት፥ የማናየውን ነገር የሚያስረዳ (ዕብ 11፡1) እንደሆነ አስረድተው፥ የክርስትና ዋና ምልክቱ፥ “ያለ እና የነበረ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ አልፋ እና ኦሜጋ (ራዕይ 1፡8) እግዚአብሔር ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቱርክ የጴርጋሞን ከተማ ፓትርያርክ እና የነገረ-መለኮት ምሁር የነበሩት ሟቹ አቡነ ጆን ዚዚየላስ ለጻፉት መጽሐፍ መግቢያ እንዲሆን ባበረከቱት ጽሑፋቸው ላይ ገልጸዋል።

30 November 2023, 09:03